Thursday, June 27, 2013

ከሓላፊነቱ የታገደው ‹አባ› ጳውሎስ ከበደ ከአስተዳዳሪነቱ ተነሣ

ላለፉት ስምንት ዓመታት ለመዝባሪ እና የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አቀንቃኝ ቡድኖች/ግለሰቦች ሽፋን በመስጠት፣ የምሥራቅ ሐረርጌ ሀ/ስብከትን በአጠቃላይ የሐረር ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት በተለይ ሲያውክ የቆየው መልአከ ጽዮን ‹አባ› ጳውሎስ ከበደ ከአስተዳዳሪነቱ መነሣቱ ተገለጸ፡፡
ርምጃው የተወሰደው በዛሬው ዕለት ሲኾን የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በጉዳዩ ላይ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ጋራ ከመከሩ በኋላ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ በተሰጠ ውሳኔ መኾኑ ተገልጧል፡፡
‹አባ› ጳውሎስ በደብሩ አስተዳዳሪነት ከተሾመበት ፲፱፻፺፰ ዓ.ም ጀምሮ ለለየላቸው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ግለሰቦች፣ ለእነርሱ በተላላኪነት ለሚያገለግሉ ሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን የመድረክ አገልግሎት ዕድል በመስጠት ለብዙዎች መሰናከል ኾኖ ቆይቷል፡፡
ከግንቦት ወር መጨረሻ አንሥቶ ደግሞ የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ለቁጥጥር ያሸገውን የሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤትና ሙዳይ ምጽዋት በመከፋፈት፣ በአምሳያው ያደራጀውን የዘረፋና ኑፋቄ ቡድን በማሰማራት የደብሩን ሀብት በግላጭ ሲመዘብር ሰንብቷል፤ ከዚህም በላይ የደብሩ አስተዳደር ከሀ/ስብከቱና ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ማእከላዊ መዋቅር እንደተለየና ለማንም እንደማይታዘዝ በማወጅ በሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ላይ መጠነ ሰፊ የዐመፅ ቅስቀሳ ለማካሄድ ሲዘጋጅ እንደነበር ታውቋል፡፡
የቤተ ክህነታችን ብስልና ጥሬ! በፈጸሙት ጥፋትና ክሕደት የሕግ ተጠያቂነት ሳይሆን ከቦታ ወደ ቦታ ማዘዋወርን እንደ መፍትሔ የሚወስደው ቤተ ክህነታችን ከሐረር ደብረ ሣህል ቅ/ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን እልቅና ያነሣውን ‹አባ› ጳውሎስ ከበደን፣ የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አበምኔት አድርጎ ነው የሾመው!!!
ምንጭ: ሐራ ዘተዋሕዶ
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment