Tuesday, February 3, 2015

በዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም የተቀሰቀሰው እሳት በቁጥጥር ሥር ዋለ

  • ቃጠሎው ለአትክልት ልማት ከተደረገ ምንጣሮ ጋራ የተያያዘ መኾኑ ተጠቁሟል
daga-estifanos-church00በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት በዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም ደን ውስጥ ዛሬ፣ ጥር ፮ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ከረፋዱ 4፡30 ላይ የተቀሰቀሰው እሳት በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገለጸ፡፡
ቃጠሎው በቁጥጥር ሥር የዋለው ከቀኑ በ9፡00 ገደማ ሲኾን ይኸውም ከቤተ ክርስቲያኑ በግምት ከመቶ ሜትር ባነሰ ርቀት ላይ በደረሰበት ኹኔታ ነው ብለዋል – እሳቱን በማጥፋት የተራዱ የዐይን እማኞች፡፡
የዳጋ እስጢፋኖስን ጨምሮ ከሌሎች የደሴቱ ገዳማት የመጡ መነኰሳት፣ የአቅራቢያው ነዋሪዎች፣ ከባሕር ዳር ከተማ በጀልባ ተጓጉዘው የደረሱ አገልጋዮችና ምእመናን፣ የክልሉ መስተዳድር ተወካዮችና የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሓላፊዎች፣ የባሕር ዳር ዙሪያ ፖሊስና የምዕራብ እዝ ኃይሎች በጋራ ቃጠሎውን በማጥፋት ከፍተኛ የጋራ ርብርብ ማድረጋቸው ተገልጧል፡፡

የቃጠሎው ትክክለኛ መንሥኤ እስከ አኹን በይፋ ባይረጋገጥም፣ መሬቱን ለጌሾ ልማት ዝግጁ ለማድረግ በአንድ የገዳሙ መነኰስ የተለኰሰው እሳት በአቅራቢያው በብዛት በሚገኙት የሐረግ ተክሎችና ሸምበቆዎች መቀጣጠሉ እንደኾነ ማኅበረ መነኰሳቱን ያነጋገሩ የዐይን እማኞች ገልጸዋል፡፡
በገዳሙ ከሚገኙት ታላላቅ አገር በቀል ዛፎች ይልቅ በብዛት ተቃጥለው የሚታዩትም የሐረግና የሸምበቆ ተክሎቹ ናቸው - ‹‹አንድ አባት ጌሾ የሚያለሙበት አካባቢ ሐረግ ነበር፤ እርሱን ለማቃጠል ሲለኩሱት እሳቱ አሸንፎ ወጣ፤ ለማጥፋትም ከመነኰሳቱ አቅም በላይ ኾነ፡፡››
በአኹኑ ወቅት በስፍራው ከሚታየው ጢስና ረመጡ ጨርሶ መጥፋቱን ለማረጋገጥ ከሚደረግ እንቅስቃሴ በቀር የእሳት ቃጠሎው በገዳሙ ቤቶችና በቤተ ክርስቲያኑ ላይ ጉዳት ሳያደርስ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ ከዓይን እማኞች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፤ አንድ ሄሊኮፕተርም በገዳሙ ዙሪያ ቅኝት ሲያደርግ መስተዋሉ ተዘግቧል፡፡
በጣና ሐይቅ ውስጥ ከደቅ ደሴት በስተምሥራቅ የሚገኘው የዳጋ እስጢፋኖስ የደሴት ገዳም የተመሠረተው በ፲፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ (በ፲፪፻፷፰ ዓ.ም.) ሲኾን መሥራቹም የዐፄ ይኩኖ አምላክ ወንድም አቡነ ኂሩተ አምላክ ናቸው፤ የተገደመውም በዐፄ ይኩኖ አምላክ እንደኾነ የገዳሙ አበው ይተርካሉ፡፡
image-31
በበርካታ ጥንታውያን የብራና መጻሕፍት ማእከልነቱ የሚታወቀው ዳጋ እስጢፋኖስ÷ የመሥራቹ የአቡነ ኂሩተ አምላክ መቋሚያ፣ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ የተሣለች የእመቤታችን ምስለ ፍቁር ወልዳ ሥዕል፣ ብዛት ያላቸው የወርቅ፣ የብርና የነሐስ መስቀሎች ጨምሮ የዐፄ ዳዊት፣ የዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ፣ የዐፄ ሱስንዮስ፣ የዐፄ ፋሲልና ሌሎች ነገሥታት አዕፅምት፤ ዘውዶች፣ አልባሳት፣ ሰይፍና ጎራዴ የመሳሰሉ የነገሥታቱ የክብርና የወግ ዕቃዎች ተጠብቀው ይገኙበታል፡፡
daga Estifanos Church.gif
የማኅበረ መነኰሳቱ ዋነኛ መተዳደርያ በተለያየ መንገድ ከሕዝብ የሚገኘው ድጋፍ ቢኾንም ቡና፣ ጌሾ፣ ሙዝና ፓፓዬ የመሳሰሉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በማምረትም የገዳሙን አገልግሎት ይደጉማሉ፡፡

Source: Hara Zetewahedo

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment