- የቁጥጥር እና የፋይናንስ ሓላፊዎች የትምህርት ዝግጅት እና ልምድ ዝቅተኛ ነው
- በቆጠራዎች የሚዘረፈው የሙዳይ ምጽዋት ገንዘብ ቢሯቸው ድረስ ይመጣላቸዋል
- የቤተሰብ ጉባኤ በሚመስለው የቁጥጥር ክፍሉ ስብሰባ የዘረፋ ስልቶች ይቀመራሉ
- ትኩረቱን ወደ ከፍተኛ ግዥዎችና ፕሮጀክቶች ለማዞር እስከ መምከር ተደርሷል
- እነኃይሌ ኣብርሃ እንዳሉት፣ ‹‹ንቡረ እድ ኤልያስን የተማመነ ምን ይኾናል!››
/ከሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች/
‹‹ባለቤቷን የተማመነች በግ ላቷን ውጪ ታሳድራለች›› እንዲሉ በአኹኑ ወቅት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሒሳብ እና በጀት እንዲኹም በቁጥጥር አገልግሎት ዋና ክፍሎች በኩል ከሕግ፣ ከመርሕ እና ከሥነ አመክንዮ ውጭ ብዙ ሕገ ወጥ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ፡- በአድባራት የደመወዝ እና የአበል ክፍያ ጭማሪ፤ በክብረ በዓል እና በወርኃዊ የአብያተ ክርስቲያን የሙዳይ ምጽዋት ቆጠራ እና የንብረት ሽያጭ ጨረታ ወቅት የሚሠሩ ሙስናዎች ልክ እንደ ሕጋዊ መብት በግልጽ እተፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ ለዛሬው፣ ለቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት ወሳኝ ስለኾነው የፈሰስ(ፐርሰንት) ጉዳይ እንመልከት፡፡
የሀገረ ስብከቱ የፐርሰንት አሰባሰብ፤
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የገቢ መጠን ከሌሎች አህጉረ ስብከት በተለየ ኹኔታ ከፍተኛ ነው፡፡ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤትም ከፍተኛውን ገቢ የሚያገኘው ከአ/አበባ ሀ/ስብከት ነው፤ ነገር ግን የገቢ አሰባሰቡንና የሒሳብ አያያዙን የሚመሩት ሰዎች ከዘመናዊው የሒሳብ ዕውቀትና ልምድ አንጻር ያላቸው ሞያ እጅግ ዝቅተኛ ከመኾኑም በላይ ከገዳማትና ከአድባራት ሓላፊዎች ጋር በተለያዩ የዘረፋ ስልቶች የሚመመሳጠሩ እና በሌብነት የተደራጁ ናቸው፡፡
የሒሳብና በጀት ዋና ክፍሉ እና የቁጥጥር አገልግሎት ዋና ክፍሉ ከነባለቤታቸው በገቢያቸው ከፍተኛ ከኾኑ ከዐሥር የሚበልጡ ገዳማት እና አድባራት በሙዳይ ምጽዋት ቆጠራ ወቅት ከሚዘረፈው ገንዘብ ላይ ቢሯቸው ድረስ ድርሻቸው የሚመጣላቸው ናቸው፡፡ ከ15 ጊዜ በላይ በተለያዩ አድባራት እየተዘዋወረ ለ17 ዓመት የሠራው ዋና ሥራ አስኪያጁ የማነ፣ የቆጠራ ወቅት ዘረፋውን በውል የሚያውቀው ከመኾኑም በላይ‹‹የተነቃበት›› እንደኾነና ወደ ከፍተኛ ግዥዎች እና ልማት የሚል ቅጽል ወደተለጠፈባቸው ፕሮጀክቶች ትኩረት መደረግ እንዳለበት እስከ መምከር ደርሷል፡፡
የሒሳብና በጀት እንዲኹም የቁጥጥር አገልግሎት ሓላፊዎች በሥራቸው ዕውቀት ብቻ ሳይኾን ፍጹም ታማኝነት የጎደላቸው ናቸው፡፡ በአኹኑ ወቅት ሀገረ ስብከቱ ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ በወቅቱ መሰብሰብ ሲገባው ያልተሰበሰበ ከ113 ሚልዮን ብር በላይ በገዳማትና አድባራት የተከማቸ የፈሰስ ዕዳ ስለመኖሩ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤትም ኾነ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ጽ/ቤት በማስረጃ ይታወቃል፡፡ ለምን በወቅቱ አልተሰበሰበም? እንዴት ይህን ያክል ብር ሊከማች ቻለ? ተሰብሳቢዎች (receivables) ከሚሰበሰቡበት ስሌት አንጻርስ ምን የተነደፈ ስልት አለ? የሚሉትን መመዘኛ እና መፈተሻ ጥያቄዎችን እናነሣለን፡፡
የሀገረ ስብከቱ የሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ሓላፊነት የተሰጣቸው ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ፣ ገዳማቱ እና አድባራቱ የመክፈል አቅም እና ፍላጎት ስለሌላቸው ያልተሰበሰበው 113 ሚልዮን ብር ይሰረዝላቸው የሚል ምክረ ሐሳብ(ፕሮፖዛል) ይዘው መቅረባቸው አሳዛኝና የእርሳቸውን የአየር በአየር የዘረፋ ስልት ለመሸፈን የተቀመረ መንገድ ነው፡፡
ለምን እንዳልተሰበሰበ የቁጥጥር አገልግሎቱ ሲመልሱ፣ ‹‹እኔ ሥራዬን ሠርቼ ሪፖርት አድርጌአለኹ፤ መከታተል እና መሰብሰብ የሒሳብ ክፍሉ የሥራ ድርሻ ነው›› ብለዋል፤ ከተጠያቂነት የመሸሻ ምላሽ ነው፡፡ ይህን የታዘቡ ሌሎች የሀገረ ስብከቱ የሥራ ሓላፊዎችም በወቅቱ፣ ‹‹ኤልያስ መች ሥራ ይሠራል፤ የእርሱ ሥራ ሌላ ነው›› በማለት የፈሰስ ዕዳው እንዲሰረዝ በቀረበው ፕሮፖዛል አዝነዋል፡፡
የአየር በአየር ዘረፋ፤
የአየር በአየር ዘረፋ የቁጥጥር አገልግሎቱ ሓላፊ ለረጅም ጊዜ ያካበተው የአዘራረፍ ስልት ነው፡፡ በክብረ በዓላት እና በወርኃዊ ገቢዎች ወቅት በቁጥጥር አገልግሎቱ የተመረጡ ሰዎች ከሀገረ ስብከቱ ይላካሉ፡፡ ለዚኽም የቁጥጥር ክፍል ሓላፊው ባለቤት የኾኑት ወ/ሮ የባሕር ሙዝ ገብረ ሚካኤል ተመራጯ ሚሽን አስፈጻሚ ናቸው፡፡ መቼስ ከክፍለ ከተማ ወደ ዋናው ጽ/ቤት በዝውውር የመጡት በተለየ የሞያ ብቃት ሀገረ ስብከቱን ይረዳሉ ተብሎ ሳይኾን ለዚኹ ተግባር ተመልምለው እንደኾነ ይታመናል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ በሀገረ ስብከቱ ሦስት ባልና ሚስት፣ ሦስት የአጎት እና የአክስትማማቾች ልጆች፣ ኹለት በጋብቻ የተሳሰሩ ቡድኖች በተቀናጀው የዘረፋ ስልት አሉበት፤ በክፍለ ከተማም እንዲኹ ማጣራት ይቻላል፡፡ አንዳንድ ጊዜም በቁጥጥር አገልግሎቱ ቢሮ የሚደረገው ስብሰባ፣ የቤተሰብ ጉባኤ የሚመስል ሲኾን አዲስ የአዘራረፍ ስልቶች ቅመራና ዕቅድ፣ አስተያየት እና አካሔድ በሚል ስም ይቀየሳል፤ ሌሎችም አሉ፡፡
የቁጥጥር ልኡካኑ በወቅቱ ገንዘብ እና ንብረት አስቆጥረው፣ በሞዴል 64 ገንዘቡን በ19 ንብረቱን አስገብተውና ደረሰኝ አስቆርጠው የሀገረ ስብከቱም ድርሻ 20 ፐርሰንት ታውቆና ለባንክ ገቢ ኾኗል ተብለው ይመጣሉ፡፡ እዚኽ ጋር ነው እንግዲኽ የቁጥጥር አገልግሎቱ እና የሒሳብ ክፍሉ ጫዎታውን የሚጫወቱት፡፡
20 ፐርሰንት ፈሰስ በወቅቱ ለሀገረ ስብከቱ አይገባም
የቁጥጥር አገልግሎቱ ክፍሉ እያወቀ እና እንደገባ በማስመሰል ዝም ይላል፡፡ የበጀት እና ሒሳብ ክፍሉም እያወቀ የቀረበለትን የውሸት የገቢ ሰነድ ደብቆ ይይዘዋል፤ ነገር ግን በገቢ አይመዘገብም፤ ምናልባት ኦዲተር በድንገት ከመጣ ለመጠባበቂያ መኾኑ ነው፡፡ ገንዘቡን ራሳቸውና ወዳጆቻቸው/የሥራ ተባባሪዎቻቸው ይነግዱበታል፡፡ በገዳማትና በአድባራት ያሉ የሚመለከታቸው ክፍሎችና እኒኽ የረጅም ጊዜ የዘረፋ ጓደኛሞች አለአግባብ በሕገ ወጥ መንገድ ይበለጽጉበታል፡፡
ሰኔ ሲመጣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚላኩት ኦዲተሮችም ሌሎች ጉዳዮችን የመመርመርና እውነቱን የማሳወቅ አቅም ያንሳቸዋል፤ የሚያስመድቧቸውም እነርሱ ናቸውና የቀረቡትን ሰነዶች በፈረደበት ካልኩሌተር ደምረውና ቀንሰው ይሔዳሉ፡፡
ልብ ሊባል የሚገባው ነገር፣ በወቅቱ ከሀገረ ስብከት በሚላኩ የቁጥጥር ልኡካን የሀገረ ስብከቱ ድርሻ 20 ፐርሰንት በእነ ወ/ሮ የባሕር ሙዝ ከገባ፤ የገቢው ኹኔታም የቁጥጥር አገልግሎቱ ሚስት እና ሌሎች አጋሮቹ ያመጡለትን ሪፖርት ለበጀት እና ሒሳብ ዋና ክፍሉ ሪፖርት ካደረጉ ገንዘቡ የት ገባ? ምክንያቱም ገንዘቡ ለቁጥጥር ለሚሔዱ ልኡካን አበል ተከፍሎ ቁጥጥር ተደርጎበታል፡፡ ስለዚኽ በወቅቱና በጊዜው ገቢ እንደሚደረግ ከታወቀ ይህን ያኽል ውዝፍ የቤተ ክርስቲያን ሀብት እንዴት ሊከማች ቻለ? አየርባየር ማለት ይህ ነው፡፡ ይህን የውጭ ኦዲተሮች ቢመለከቱት በቢሊዮን ደረጃ ጉድለት እንደሚገኝ አያጠራጥርም፡፡ የአራዳ ጊዮርጊሶቹ እነኃይሌ ኣብርሃ፣ ‹‹ንቡረ እድ ኤልያስን የተማመነ ምን ይኾናል››እንዳሉት እኛም በመግቢያችን ባለቤቷን የተማመነች በግ ላቷን ውጪ ታሳድራለች የሚለውን የአበው ብሂል አውስተናል፡፡
ሊቀ ጠባቡ ኤልያስ ተጫነ እና ሊቀ መሠሪው ገብረ መስቀል ድራር በአኹኑ ወቅት ሚልየነር የኾኑት፣ ያለተቆጪና ቀጪ እንደልባቸው የሚዝናኑት ሃይ ባይና ጠያቂ በሌለው በዚኽ ዓይነቱ መዋቅርና አሠራር ነው፡፡ ዘረፋው በሕዝብ ሀብት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እስከኾነ ድረስ መንግሥትስ ለምን ጣልቃ አይገባም? መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም የሚለው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ኦርጂናል የትርጉም ፅንሰ ሐሳብ በዶግማው/በመሠረታዊው የሃይማኖት አስተምህሮ ነው፡፡
ዕዳ ይሰረዝ የሚለው ፕሮፖዛልም ብዙ ሕገ ወጥ ሰነዶችን ለማጥፋት እና በአየር ላይ የተበላው ገንዘብ እንዲወራረድ የተነደፈ መንገድ ነው እንጂ በዘመናዊው የሒሳብ አሠራር ስልት ያልተሰበሰቡ(receivables) የሚሰበሰቡበት መንገድ እኮ አለ፡፡ ለምን አይታይም? አይመረመርም? እኒኽ ልሙድ ቀሳጥያን ለ17 ዓመታት አብረው ሲሠሩ ከኖሩት ሥራ አስኪያጅ ጋር ዶልተው በሞያዊነትም በሥነ ምግባርም ከእነርሱ የተሻሉ ሓላፊዎችን በሕገ ወጥ ዝውውር እና በእግድ ከሀገረ ስብከቱ ያገለሏቸው፣ ይህን የሌብነት ተግባር ከሕግ እና ከአስተዳደር አግባብነት አኳያ በመመርመር ሊያጋልጡብን ይችላሉ ብለው በመገመት ሊኾን እንደሚችል ይታመናል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ይፈርዳል ብለን እናምናለን፡፡
የሚመለከተው ክፍል፣ ተሰደብን ወይም ተዘለፍን በሚል እልክ ከመወጠር እና በቤተ ክርስቲያን ንብረትና ሀብት ላይ ቸልተኝነት ከማሳየትየጉዳዩን ትክክለኛነት መርምሮ በፍጥነት ሞያዊ እርማት መስጠት ይገባዋል እንላለን፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡
ይቆየን፡፡
source: https://haratewahido.wordpress.com/የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment