- የኮሌጁ የደቀ መዛሙርት ም/ቤት ችግሩ በአስቸኳይ እንዲጣራ ከኹለት ወራት በፊት ያስገባው ደብዳቤ ለተጠርጣሪ ደቀ መዛሙርት ሽፋን በሚሰጠውና ተጠርጣሪዎችን በቢሮው እየጠራ በሚያበረታታው የአስተዳደር ዲኑ ያሬድ ክብረት ተቀብሮ መቆየቱ ተገልጦአል፡፡
- በቅ/ሲኖዶስ ከተወገዙ ግለሰቦችና ፕሮቴስታንታዊ ድርጅቶች የኑፋቄ አስተምህሮና ተልእኮ የሚሰጣቸው ኅቡእ አንቀሳቃሾችትኩረታቸውን በአዲስ ገቢ ደቀ መዛሙርት ላይ አድርገዋል፤ በመምህራን ምደባ ተጽዕኖ እስከመፍጠር፣ በነግህ ጸሎት ቤት ተራ ወጥቶላቸው ለስብከተ ወንጌል የሚመደቡ ቀናዒ ደቀ መዛሙርትን በማሸማቀቅ መርሐ ግብሩን እስከማስተጓጎልና መደበኛ የትምህርት ክፍለ ጊዜዎችን በጋጠ ወጥነትና በአካዳሚያዊ ነጻነት ስም እስከማወክ የደረሱት ኅቡእ አንቀሳቃሾቹ፣ ከየአህጉረ ስብከቱ ተልከው የመጡበትን የኮሌጁን ትምህርት በክፍል ተገኝተው በመደበኛነት አይከታተሉም፤ ቤተ መጻሕፍቱንማ ጨርሶ አያውቁትም!!
- በተጠርጣሪነት ክትትል ከሚደረግባቸው ኻያ ያህል የስም ደቀ መዛሙርት መካከል የድምፅ፣ የጽሑፍና የሰው ምስክሮች የቀረቡባቸው ዐሥር ተማሪዎች፡- ጥበቡ ደጉ(፬ኛ ዓመት ከደብረ ማርቆስ)፣ መለሰ ምሕረቴ(፬ኛ ዓመት ከራያና ቆቦ)፣ ያሬድ ተስፋዬ(፫ኛ ዓመት ከሃላባ)፣ ኤርሚያስ መለሰ(፫ኛ ዓመት ከባሌ)፣ ታቦር መኰንን(፫ኛ ዓመት ከወሊሶ)፣ በኃይሉ ሰፊው(፫ኛ ዓመት ከቤንች ማጂ)፣ ተመስገን አዳነ(፪ኛ ዓመት ከሐዋሳ)፣ ይስፋ ዓለም ሳሙኤል(፫ኛ ዓመት ከሰቆጣ)፣ ገብረ እግዚአብሔር ተስፋ ማርያም(፫ኛ ዓመት ከአሶሳ)፣ ሀብታሙ ወልድ ወሰን(፫ኛ ዓመት ከወለጋ) ናቸው፤ የኑፋቄ ተልእኳቸውና ማስረጃዎቹ ከየስማቸው ዝርዝር በአንጻሩ ሰፍሯል፡፡
- ከተጠርጣሪ ደቀ መዛሙርት መካከል የአጫብር አቋቋም ዐዋቂ ነው የተባለው መሪጌታ ጥበቡ ደጉ የደቀ መዛሙርት ም/ቤት አባል ሲኾን በፈረንሳይ ለጋስዮን ገነተ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን በስብከተ ወንጌል እያገለገለ እንደሚገኝ ተዘግቧል፤ ግለሰቡ በግልጽ በሚናገረው ኑፋቄው፣ ‹‹እያንዳንድህ የበላኸውን ትፋ! ያለነው በጫካ ውስጥ ነው፤ ክርስቶስን ለማወቅ ካለንበት ጫካ መውጣት አለብን፤ መስቀል ዕንጨት ነው፤ ስግደት ለእግዚአብሔር ብቻ ነው፤ ለመልአክ የምሰግደው ተገልጦ ሲታየኝ ብቻ ነው፤ ለማርያም የጸጋ ስግደት የሚለው በመጽሐፍ ቅዱስ የቱ ላይ ነው፤›› በሚል ግልጥ ኑፋቄ የቤተ ክርስቲያንን የነገረ ድኅነትና ክብረ ቅዱሳን አስተምህሮ በመጋፋት ይታወቃል፡፡
- በኤቲክስና ሶሲዮሎጂ መምህሩ ተሾመ ገብረ ሚካኤል ‹‹ታዲያ ለምን ኤቲክስ ትማራለኽ?›› በሚል የተጠየቀው መለሰ ምሕረቴ፡-‹‹ኢየሱስ አማላጅ ነው፤ በጸጋው ድነናል፤ ሥራ(ምግባር) አያስፈልግም፤›› በማለት ይታወቃል፡፡ ያሬድ ተስፋዬ፡- በነግህ ጸሎት ቤት ነገረ ማርያምንና ክብረ ቅዱሳንን ማእከል አድርገው የሚያስተምሩ ቀናዒ ደቀ መዛሙርትን ትምህርት አስቁሞ ከመድረክ እንዲወርዱ በማስገደድ፤ ተመስገን አዳነ፡- አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ‹‹የተሻለ ሥልጠና የምታገኙበት ቦታ አለ›› በሚሉ የጥቅም ማባበያዎች እየመለመሉ በመውሰድ፣ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ትራክቶችንና መጽሐፎችን በኅቡእ በማሰራጨት፤ ‹‹እኔ የመንግሥት የደኅንነት አካል ነኝ፤›› የሚለው ታቦር መኰንንና ገብረ እግዚአብሔር ተስፋ ማርያም ቀናዒ ደቀ መዛሙርትን ‹‹ማኅበረ ቅዱሳንና ፖሊቲከኞች ናችሁ›› እያሉ በማስፈራራት፣ መምህራን በምደባቸው እንዳያስተምሩ በውጤት አሰጣጥ ያኮረፉ ተማሪዎችን ለዐመፅ በማነሣሣት፣ በክፍል እያስተማሩ በሚገኙ መምህራን ላይ ከውጭ በር በመቀርቀርና በማንጓጠጥ፣ ዋናው ዲን የኮሌጁን ማኅበረሰብ በመንፈስ ለማስተሳሰር የጀመሯቸውን ጥረቶች (በጋራ እንደማስቀደስና እንደመመገብ ያሉ) በመቃወም በተለያዩ ስልቶች ወንጅሎ ለማስነሣት በሚፈጽሟቸው ሤራዎች ይታወቃሉ፡፡
- ኅቡእ አንቃሳቃሾቹን እየመለመሉና ከኮሌጁ ውጭ በተለያዩ መንደሮች እያደራጁ ተልእኮና ጥቅም በመስጠት ወደ ኮሌጁ መልሰው ከሚያሰማሩት ግለሰቦች መካከል፡- በ፲፱፻፺፩ ዓ.ም. በቅ/ሲኖዶስ ተወግዞ ከሰዋስወ ብርሃን ቅ/ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የተባረረው ግርማ በቀለ፣ በግንቦት ፳፻፬ ዓ.ም. በቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተወገዘው አሸናፊ መኰንን፣ የታገደው ጥቅመኛና ጥራዝ ነጠቅ ተላላኪ አሰግድ ሣህሉ በዋናነት ተጥቅሰዋል፤ ከኮሌጁ ተመርቀው ምደባ ቢሰጣቸውም በአዲስ አበባ ተቀምጠው የማደራጀት ሥራውን የሚመሩትም አሳምነው ዓብዩ፣ ታምርአየኹ አጥናፌ፣ አብርሃም ሚበዝኁ፣ ጋሻው ዘመነ፣ ‹አባ› ሰላማ ብርሃኑ፣ እሸቱ ሞገስና በድሬዳዋ የሚገኘው በረከት ታደሰ እንዲኹም በኮሌጁ የድኅረ ምረቃ ትምህርት በመከታተል ላይ የሚገኙት አእመረ አሸብርና ደረጀ አጥናፌ የተባሉ ግለሰቦች ናቸው፡፡
- የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደር በጽሑፍ፣ በድምፅና በሰው ምስክሮች ተደግፈው የቀረቡ ማስረጃዎችን ከቅዱሳት መጻሕፍት፣ ከትምህርተ ሃይማኖትና ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አንጻር ለመመልከት የሚያግዙትን ሦስት መምህራን መርጦ ዛሬ ምርመራውን ይጀምራል፤ የተመረጡት መምህራን፡- የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ታሪከ ሃይማኖት መ/ር ፍሥሓ ጽዮን ደመወዝ፣ የሥርዓተ ቅዳሴ መ/ር ሐዲስ ትኩነህና የትምህርተ ሃይማኖትና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን መ/ር ዶ/ር ሐዲስ የሻነህ ናቸው፡፡
- ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስና ዋና ዲኑ ቀሲስ ኸርበርት ጎርደን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ተላላኪዎች ጉዳይ ተጋልጦ እንዲመረመር በጽናት የተንቀሳቀሱ የደቀ መዛሙርት ም/ቤት አባላትንና ብዙኃኑን ደቀ መዛሙርት በከፍተኛ አባታዊና የሓላፊነት ስሜት ተቀብለው እያበረታቱ ናቸው፡፡
- * * *
- ‹‹በጣት የሚቆጠሩ ውሱን ተማሪዎች ከኮሌጁ ውጭ በሚሰጣቸው ተልእኮ ፕሮቴስታንታዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ በአካዳሚያዊ ነጻነት ስም የፕሮቴስታንት አስተምህሮ እያሰራጩ ይገኛሉ፡፡ በዚኽም ተባባሪ ለማግኘትና በፕሮቴስታንት ሳንባ የሚተነፍሱ ደቀ መዛሙርት ለማብዛት በተለይም አዲስ በሚገቡ የመጀመሪያ ዓመት ደቀ መዛሙርት ላይ መደናበር በመፍጠር ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሱ ናቸው፡፡ ከዐሥር በማይበልጡ ተማሪዎች የተነሣ አንጋፋው ኮሌጃችን ‹የፕሮቴስታንት ኾኗል፤ መናፍቃንን እያፈራ ነው› እየተባለ ሲሰደብና ቤተ ክርስቲያናችን ኪሳራ ሲደርስባት በዝምታ መመልከት ጉዳቱ የከፋ ነው፡፡›› /ጥያቄዎቻቸው ለኹለት ወራት በአስተዳደር ዲኑ በየሰበቡ የታገተባቸው ደቀ መዛሙርቱና የም/ቤት አባላቱ ለዋና ዲኑ ያስገቡት የአቤቱታ ደብዳቤ/
- ‹‹ኮሌጁ የሚቀበላቸውን አዳዲስ ተማሪዎች አመላመል በጥብቅ ዲስፕሊን መመሪያውን ጠብቆ በጥራት ቢኾን፤ ከመተዳደርያ ደንቡ ውጭ የሚንቀሳቀሱ መምህራንና ሠራተኞች ኹኔታ በማጣራት የዲስፕሊን ርምጃ ቢወሰድ፤ ቅዱስ ሲኖዶስ የኮሌጁን አጠቓላይ የሥራ ሪፖርት በማዳመጥ ለደካማ ጎን መስተካከልና ለጠንካራ ጎኑ ማበረታቻ የሚሰጥበት የክትትል ሥርዓት ቢኖረው፤›› /የ፳፻፭ ዓ.ም. የአስተዳደሩንና የደቀ መዛሙርቱን ውዝግብ የመረመረው አጣሪ ቡድን ለፓትርያርኩ በመፍትሔነት ካቀረበው ሪፖርት/
- ‹‹ለቤተ ክርስቲያኒቱ ኮሌጆችና የካህናት ማሠልጠኛዎች የመምህራን አመራረጥና አመዳደብ፣ የደቀ መዛሙርት አመራረጥና አቀባበል ላይ ብርቱ ጥንቃቄ አለመደረጉና በየጊዜውም የትምህርት ክትትልና ቁጥጥር ማነስ ለችግሩ መከሠት ምክንያት ይኾናል ተብሎ ይገመታል፡፡ ስለኾነም ወደፊት በቤተ ክርስቲያናችን ኮሌጆችና የካህናት ማሠልጠኛዎች የመምህራን አመዳደብና የደቀ መዛሙርት አቀባበል ላይ ብርቱ ጥንቃቄና ትኩረት እንዲደረግ፤›› /8 የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ድርጅቶችና 16 ግለሰቦች የተወገዙበትን ጉዳይ ያጣራው የሊቃነ ጳጳሳትና ሊቃውንት ጥምር ጉባኤ በግንቦት ፳፻፬ ዓ.ም. ለቅ/ሲኖዶስ አቅርቦት የነበረው የውሳኔ ሐሳብ/
- ‹‹የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በኮሌጆቻችን የሚገኙትን ተማሪዎች መቆጣጠርና መከታተል አስፈላጊ መኾኑን በአጽንዖት በመወያየት ደቀ መዛሙርቱ ከየአህጉረ ስብከታቸው ተመርጠው ሲላኩ የቤተ ክርስቲያን ልጆች መኾናቸውና የሃይማኖታቸው ጥንካሬ ታይቶ ወደ ኮሌጆቻችን ሊላኩ ይገባል በማለት እያንዳንዳቸው አህጉረ ስብከት ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጉባኤው ተነጋግሯል፤ መምህራንም የሚሰጡት ትምህርት በኮሌጆቻችን ሓላፊዎች እየተገመገመ ትምህርቱ እንዲሰጥ ኾኖ ትምህርቱ ኑፋቄ ያለበት ከኾነ ደረጃውን ጠብቆ ለምልዓተ ጉባኤው እንዲቀርብ ጉባኤው ወስኗል፡፡›› /በ8 የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ድርጅቶችና 16 ግለሰቦች ላይ ውግዘት ያስተላለፈው የግንቦት ፳፻፬ ዓ.ም. ቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ/
ተጨማሪ መረጃዎችን ይከታተሉ
ምንጭ: ሐራ ዘተዋሕዶየተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment