![]() |
| ግራኝ መሀመድ አልጋዚ |
ከግዛት መስፋፋት ባለፈ፤ ከፍተኛ የሰው ሕይወት መጥፋት፤ ለብዙዎች ከእምነት መፈናቀል (በግዴታ ሃይማኖት መቀየር) እንዲሁም
ለዘመናት የተከማቹ በዋጋ የማይገመቱ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ቅርሶች መውደም ዋናኛ ምክንያት ሆኗል። የወረራው መጠን-ሰፊነትና
አጥፊነት የኢትዮጵያን ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ገጽታ ለዘለቄታው የለወጠው ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንና
በምእመናኗ ላይ ጥልቅ የታሪክ ጠባሳ ጥሎ አልፏል። ለአሕመድ ግራኝ ጦርነት መነሻ የሆኑ ምክንያቶች የአሕመድ ግራኝ ጦርነት
ድንገት የተከሰተ ሳይሆን የዘመናት ቅራኔዎች ውጤት ነው።
የታሪኩ መጀመሪያ የሚመነጨው ከ 7ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የእስልምና
እምነት በቀጠናው መስፋፋትና የቀይ ባሕር የንግድ እንቅስቃሴ መዳከም ለአክሱም መንግሥት ውድቀት አንድ ምክንያት ሆነው ከቀረቡበት
ወቅት ጀምሮ ነው። ከ 9ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ ደግሞ፤ በክርስቲያን መንግሥት ደቡብ ምሥራቃዊ አቅጣጫ የተመሠረቱት እስላማዊ
ሱልጣኔቶች (Principalities) በሂደት እያደጉ መጥተው ከፍተኛ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተጽዕኖ ማሳደር ጀመሩ።በተለይም ከ
13ኛው እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን ባለው የሰሎሞናዊ ሥርወ-መንግሥት ዘመን፤ በደጋው ክርስቲያን መንግሥትና በቆላማው ሙስሊም
ሱልጣኔቶች መካከል የነበረው ግንኙነት በፉክክርና በግጭት የተሞላ ነበር። የዚህ ፍልሚያ ዋናው መንስኤ በወቅቱ የነበሩ የንግድ
መስመሮችን የበላይነት የመያዝ ፍላጎት ነው። በተለይም 'የዘይላ' ወደብ ከአፍሪካ የውስጥ ግዛቶች የሚመጡ ምርቶች ለዓለም ገበያ
የሚቀርቡበት ቁልፍ ስልታዊ ማዕከል በመሆኑ፤ ይህንን የንግድ መስመር ለመቆጣጠር የሚደረገው ሽኩቻ በሁለቱ ኃይሎች መካከል
ለማያቋርጥ ደም መፈሰስ እንደ ዋና መነሻ ሆኖ አገልግሏል። የዐፄ ዐምደ ጽዮን (1306—1336) ዘመነ መንግሥት ለኢትዮጵያ
ክርስቲያን መንግሥት የመስፋፋት ጊዜ ነበር።
በዚህ ወቅት በመካከለኛው ደጋማ ቦታዎች ይገኙ የነበሩ በርካታ ሙስሊም ሱልጣኔቶች
በንግሡ ሥር እንዲገብሩ መደረጋቸው፣ ለሰሎሞናዊው ግዛት ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ የበላይነት ጽኑዕ መሠረት ጥሏል። ይሁን እንጂ ይህ
ፍጹም የበላይነት በሱልጣኔቶቹ ዘንድ የነፃነት ጥምና የዐመፅ ጥቃት ፍላጎትን እያቀጣጣለ መጣ። በ14ኛው ክፍለ ዘመን የኢፋት
ሱልጣኔት መሪ የነበረው ሐቅ አድ-ዲን፣ በክርስቲያኑ ግዛት ላይ ተከታታይ ወረራዎችን በመሰንዘር እስከዚያው አልፎ አልፎ ይነሡ
የነበሩ ግጭቶችን ወደ የተቀናጀ ወታደራዊ ዘመቻ ቀየራቸው። ይህ እንቅስቃሴ በ16ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በአዳል ሱልጣኔት
ገዢ በማህፉዝ ቢን ሙሐመድ አማካኝነት የበለጠ ተጠናከረ። ማህፉዝ የክርስቲያኑ ሠራዊት በጾም ምክንያት የሚደክምበትን የዐቢይ ጾም
ወቅት በመጠበቅ ስልታዊ ጥቃቶችን በመሰንዘር ይታወቃል።
በ1512 ዓ.ም ማህፉዝ በመንገደኛው ገብረ እንድርያስ እጅ መገደሉ
ለጊዜው እንቅስቃሴውን ቢያቀዘቅዘውም፤ የእማም አሕመድ (ግራኝ) ሥልጣን መያዝ ግን የዚህ የቆየ ግጭት ከፍተኛውና የመጨረሻው
ምዕራፍ ሆኖ ተመዝግቧል። በቀጣይነት የኦቶማን ቱርኮች መመጣት በኢትዮጵያ ይካሄድ የነበረውን ጦርነት ወደ ዓለም አቀፋዊ መልክ
ቀይሮታል። ቆስጠንጥንያን የተቆጣጠረው የኦቶማን አመራር፤ ግዛቱን ወደ አፍሪካ ቀንድ ለማስፋፋት ካለው ስልታዊ ፍላጎት አንጻር
ለአሕመድ ግራኝ ወታደራዊ ድጋፍ መስጠት ጀመረ። የኦቶማኖች ዘመናዊ ጦር መሣሪያና የቴክኒክ ድጋፍ፣ በእማም አሕመድ የሚመራው
ሠራዊት በክርስቲያኑ መንግሥት ላይ ወሳኝ ድል እንዲቀዳጅ ከማድረጉም በላይ፤ ታሪክን ለለወጠው መጠን-ሰፊ ወረራ ዋናኛ መነሻ
ሆኗል። በዚህም ምክንያት 16ኛው ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በእስልምና ወረራ ምክንያት እጅግ አስከፊ
ጉዳት የደረሰባቸው ጥቁር ወቅቶች አንዱ ሆኖ ይመዘገባል።
በዚህ የፈተና ዘመን አብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል በሰይፍ ማስፈራራት
እምነቱን እንዲቀይር ተደርጓል፤ ጥንታዊ የጸሎት ቦታዎችና ገዳማት ወድመዋል፤ ምእመናንም ለስደትና ለከፍተኛ መከራ ተዳርገዋል።
በተለይም በዐፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በታሪኳ "ግራኝ" ተብሎ በሚታወቀው በአሕመድ ኢብን
ኢብራሂም የጦር ዘመቻዎች ምክንያት ለማንነትና ለህልውናዋ አስጊ የሆነ ታላቅ መከራን አስተናግዳለች። ሙሉ ስሙ አሕመድ ኢብን
ኢብራሂም አል-ጋዚ በመባል የሚታወቀው አሕመድ ግራኝ፤ መቀመጫውን በሐረርና በአካባቢው ባደረገው የአዳል ሱልጣኔት ላይ መሪነትን
ተቆጣጠረ። በዋነኛነት ከሶማሌና ከአፋር ተዋጊዎች የተወጣጣውን፡ በየመኑ እንዲሁም በኦቶማን አጋሮች የተጠናከረው ሠራዊቱ፣
ከ1519 እስከ 1535 ዓ.ም ባሉት ዓመታት በክርስቲያኑ መንግሥት ላይ ከደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ የማያቋርጥ ጥቃቶችን ሰንዝሯል።
አሕመድ ግራኝ ከዐረብ ምሁራን መነሣሣትን ያገኘ ሲሆን፡ በዐረቢያና በመካከለኛው ምሥራቅ ከነበሩ የኦቶማን አዛዦች ወታደራዊ ድጋፍ
ማግኘቱ በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ የሙስሊም ማኅበረሰቦችን እንዲያስተባብር አግዞታል። ይህ ወረራ ኢትዮጵያን ለውድቀት አፋፍ
ያደረሳት ሲሆን፤ በሀገሪቱ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ገጽታ ላይም ዘላቂ ተጽዕኖ ጥሎ አልፏል። ለአሕመድ ግራኝ አስከፊ ጦርነቶች
መነሣት በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ዐረብ ፋቂህ የግራኝን ጂሃድ የመጀመሪያዎቹ የእስልምና ወረራዎች በመቀጠል፤ እስላማዊ
መንግሥትን ለመሠረት የተደረገ ጥረት አድርጎ ይገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ለእስልምና መስፋፋት እንደ ትልቅ እንቅፋት
ስትታይ ቆይታለች። ምንም እንኳን በቀይ ባሕር ብቻ ተለይታ ለዐረብ ባሕረ ገብ መሬት በጣም ቅርብ ብትሆንም፤ ሀገሪቱ እስልምናን
ሙሉ በሙሉ ተቀብላ አታውቅም። ብዙ ሙስሊሞች ኢትዮጵያን መጥፋት የሚገባት «የከሐዲዎች ሀገር» አድርገው ይመለከቷት ነበር፤
ሀገሪቱ ወደ እስልምና ከተለወጠች መላውን የአፍሪካ አህጉር ለመለወጥ መንገድ ይከፍታል ብለውም ያምኑ ነበር። ይሁን እንጂ
ኢትዮጵያን በእስልምና እገዛዝ ሥር ለማምጣት የተደረጉ ተደጋጋሚ ሙከራዎች በመጨረሻ ሳይሳኩ ቀርተዋል።
ቀሲ መንግሥቱ
ጎበዜ(ዶ/ር)
[የኢኦተቤ የሦስት ሺህ ዘመናት ጉዞ ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ]
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:
Post a Comment