- ምልአተ ጉባኤው 18 የመነጋገሪያ አጀንዳዎችን ለይቶ ውይይቱን ቀጥሏል
ምልአተ ጉባኤው በዋናነት ከሚነጋገርባቸው ጉዳዮች ውስጥ፡-
- ቤተ ክርስቲያኒቱ በመሪ ዕቅድ መመራት እንዳለባት የታመነበት በመኾኑ መሪ ዕቅዱ ‹‹ተዘጋጅቶ ሲቀርብ›› ተመርምሮ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡
- የሕገ ቤተ ክርስቲያን እና ቃለ ዐዋዲ ማሻሻያ ረቂቆች በኮሚቴው ቀርበውና ተደምጠው ተጨማሪ ሐሳብ ይሰጥባቸዋል፤
- በቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደርና ሙስና ችግሮች ላይ ‹‹መጠነ ሰፊ›› ውይይት ተደርጎ ውሳኔ ይተላለፋል፤ በጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያዎችና ድርጅቶች፣ በሁሉም አህጉረ ስብከት መዋቅሮች ሙስናን የመከላከያውና መቆጣጠርያው አግባብ ከሚያሰፍነው ጥብቅ ሥርዐት አንጻር አጀንዳው አነጋጋሪና አከራካሪ እንደሚኾን ይገመታል፡፡
- የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የጠ/ቤ/ክህነት ዋና ሥ/አስኪያጅ ምርጫ ይካሄዳል፤ በበቂ የሰው ኀይልና በበጀት ተደግፎ በሦስት ዴስኮች እንዲደራጅና የራሱ ወርኃዊ መጽሔት እንዲኖረው የተወሰነለት የውጭ ግንኙነት መምሪያ አዲስ ሓላፊና ሊቀ ጳጳስ ይሾምለታል፤ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የቅድሚያ ግምት የተሰጣቸው ቢኾንም ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስና ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ይጠበቃሉ፤
- ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌምን ጨምሮ አባቶች እንዲመደቡባቸው የሚያስፈልጉና ችግር ያለባቸው አህጉረ ስብከት ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፤ በአጀንዳው የተጠቀሱት አህጉረ ስብከት÷ የአዲስ አበባ፣ የትግራይ ማእከላዊ ዞን አክሱም፣ የሐዋሳ ቡርጂና ቦረና ብቻ ናቸው፡፡ በሰሜን ወሎና ዋግ ኽምራ የቅዱስ ላሊበላ ደብርና ሌሎች ወረዳዎች አስተዳደርከሙስናና ጎጠኝነት፣ በድሬዳዋና ምዕ. ሐረርጌ፣ በምሥራቅ ጎጃም፣ በዋሽንግተን ዲሲና ካሊፎርኒያ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ከኑፋቄና ጎጠኝነት ጋራ የተያያዙ የካህናትና ምእመናን አንገብጋቢ ጥያቄዎችስ?
- የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደር ልማት ድርጅት አዲስ አሠራርን ተመርምሮና ተጣርቶ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡
ከሌሎች የምልአተ ጉባኤው አጀንዳዎች፡-
- የቀድሞው ፓትርያሪክ ንብረትን በተመለከተ ውሳኔ መስጠት፤
- ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ (ቀድሞ በሰሜን አሜሪካ የካሊፎርኒያ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ) አስመልክቶ የቀረበውን ጽሑፍ በንባብ ሰምቶ መወሰን፤
- የቀጣይ የቋሚ ሲኖዶስ አባላትን መመደብና በጽሑፍ የሚቀርቡ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የዝውውር ጥያቄዎችን መወሰን የሚሉት ይገኙበታል፡፡
በምልአተ ጉባኤው አጀንዳ ያልተካተቱና ሊታዩ የሚገባቸው ወቅታዊ ጉዳዮች፡-
- የአንድ ዓመት ጊዜ ገደብ የተሰጠው የፌዴራል ጉዳዮች ሚ/ር የሃይማኖትና እምነት ተቋማት ምዝገባ መመሪያ ረቂቅበተመለከተ ከቤተ ክርስቲያናችን አሐዳዊነት፣ ነባራዊነትና ሉዓላዊነት አኳያ የሚኖረን አቀባበል፤
- የቅዱሳት መካናት /ገዳማትና አድባራት/ ይዞታና ክብር መጠበቅ ከመንግሥት ሰፋፊ የልማት ፕሮጀክቶች /በጣና በለስ የተቀናጀ ስኳር ልማት ፕሮጀክት፣ የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት. . ./ አንጻር እንዲሁም የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ግልጽ ጥፋት /በመዝባዕ ገዳም/
- በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የትምህርት አስተዳደሩ ብቃትና አግባብነት ባላቸው ሓላፊዎችና ዲኖች እንዲመራ፣ አስተዳደሩ ከሙስናና ብልሹ አሠራር የጸዳ እንዲኾን ደቀ መዛሙርቱ ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች በተመለከተ ኮሚቴው /ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ሦስት፣ ከመንግሥት ሁለት አባላት የተውጣጡበት/ ያቀረበውና በዋናነት ሦስት ነጥቦችን የያዘው የመፍትሔ ሐሳብ፤ ከዚሁ ጋራ በተያያዘ የጠ/ቤተ ክህነቱ ትምህርትና ሥልጠና መምሪያ ለመንፈሳዊ ኮሌጆቻችን፣ የካህናት ማሠልጠኛዎቻችንና የአብነት ት/ቤቶቻችን አመራርና ድጋፍ ለመስጠት ያለው ብቃት፤
ተጨማሪ ዜናዎችን ይከታተሉ፡፡
ምንጭ: ሐራ ዘተዋሕዶ
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment