Friday, May 24, 2013

ኦርቶዶክሳዊ መምህር


ከታምራት ፍሰሐ
"በሃይማኖት ብርኖሩ፥ እራሳችሁን መርምሩ" ፪ኛ ቆሮ. ፲፫ ፥ ፭

ይድረስ ኦርቶዶክሳዊ ምላሽ አዘጋጅተው በልዩ ልዩ መንገድ ለህዝብ ለሚያደርሱ ኦርቶዶክሳውያን መምህራን

         ብዙወች መምህራን ተብለው ይጠሩ ዘንድ ይሾማሉ፡ አንዳንዶቹ ስለመልካም ግብር አንዳንዶቹም ስለዋዛ ፈዛዛ ብዙወች መምህራን ተብለው እንዲያስተምሩ ወደ ምእመናን ይላካሉ ፡አንዳንዶቹ ከመንፈስ ቅዱስ አንዳንዶቹ ከዲያቢሎስ አንዳንዶቹ መምህራን ከማስተማራቸው አስቀድመው ለራሳቸው ጥበብን ይማሯታል፡ ይተረጉሟታል ይኖሯታል አንዳንዶች ግን ያልገባቸውን ጥበብ ለሌሎች ሊያስረዱ ይደክማሉ፡፡

        ኦርቶዶክሳዊ መምህር ግን ሿሚው መንፈስ ቅዱስነው አብነቱ ክርስቶስ ነው ህብረቱ ከቅዱሳን ጋር ነው ስለዚህም ክብሩ ልዩ ነው የንጉስ ባለሟል ስለንጉሱ ሲባል የከበረ እንደሆነ ሁሉ ኦርቶዶክሳዊውም መምህር ስለርትእት ንፅህት ክብርት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክቡር ነው ፡፡ መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን እንደሚያፈራ ሁሉ መልካሚቱ ዛፍ ቤተክርስቲያን የምታፈራው መምህርም እንዲሁ መልካም ነው ፡፡

        ለኦርቶዶክሳዊው መምህር አብነቱ ክርስቶስ ነው፡ ክርስቶስ ቅን እንደሆነ እርሱም ቅን ነው ክርስቶስ የዋህ እንደሆነ እርሱም የዋህ ነው ክርስቶስ ሁሉን እንደወደደ እርሱም ሁሉን ወዳጅ ነው ክርስቶስ ለሁሉ እንደደከመ እርሱም ለሁሉ የሚደክም ነው ቀድሞ አይቆጣም ቀድሞም አይፈርድም ነገር ግን ሁሉን በፍቅር ይገዛል ዋዛ ፈዛዛ አይናገርም ምፀትና ስላቅም አያበዛም

       ለኦርቶዶክሳዊው መምህር ህብረቱ ከቅዱሳን ጋርነው ምግባሩ የቀና መንገዱም የሰመረ ነው አካሄዱ አስተማሪ አለባበሱም ሰባኪ ነው ለቅድስና ይተጋል ከሃጢአትይርቃል እዩኝ እዩኝ አይልም ብርሃንን ግን ለብሶ ለሁሉ ይታያል አብሉኝ አጠጡኝ አይልም ሲያበላ ሲያጠጣ ግን ይታያል፤ መምህርነቱ ለሁሉም ነው ውሎው ግን ከድሆች ዘንድ ነው ዝነኛ ነው ነገር ግን ስጋዊ ሃብቱ ጥቂት ነው ኦርቶዶክሳዊው መምህር የሰው ሁሉ ስርአት አስተማሪ ነው እርሱም ግን የስርአት ተገዢ ነው ድምፁ የለሰለሰ ነው ነገር ግን ለሁሉ የሚሰማ ነው

       ኦርቶዶክሳዊው መምህር በማንም ላይ የስድብና የስላቅ ቃል አይናገርም ስህተትንም በስህተት አያርምም ለሚሰድቡት ይፀልያል እንጂ ቤተክርስቲያን የሁሉ እናት እንደሆነች እርሱም የሁሉ እንደሆነ የተገነዘበ ነው አይሁዳዊ የለ አረማዊ ክርስቲያን የለ እስላም ሁሉን በአግባብ ያስተናግዳል፡ ሁሉን በፍቅር ያናግራል፡፡ በተለይም ከተዋህዶ ውጭ ላሉት ያዝናል ያስባል ይደክማል እንጂ በእነርሱ አይሳለቅም፡፡ ክቡር ክርስቶስ የወደደው የሰው ፍጥረት ሁሉ ክቡር እንደሆነ ያከብራል እንጂ በዋዛ ፈዛዛ የማይገባ ንግግርን አያበዛም፡፡

      ኦርቶዶክሳዊው መምህር የቤተክርስቲያን ጠበቃ ነው ዶግማ ቀኖናዋን ሊያፈርሱ ከታጠቁት ጋር ሳይዘናጋ እምነቱን ይጠብቃል ስህተታቸውን ይገልጣል ነገር ግን በስህተታቸው አያላግጥም በአውደ ምህረትም የማይገባ ዘለፋን አያበዛም የምህረትን ወንጌል ያበስራል እንጂ ሩቅ ያሉትን በማስደንገጥ የበለጠ አያርቅም ይልቅስ የራቁትን በፍቅር ይጠራል እንጂ፤ ልባቸው በኑፋቄ የሻከረን በትህትና ያለዝባል እንጂ፡፡

       ኦርቶዶክሳዊው መምህር ከገንዘብ ፍቅር በእጅጉየተለየ ነው ወንጌልን በገንዘብ እንዳይሽጣት እርሱ ፆሙን ያድራል ክርስቶስን እንደይሁዳ በገንዘብ አሳልፎ እንዳይሰጥም በአግባብ በመጠን በንቃት ይኖራል ይህ አለም ድልድይ እንደሆነ አብዝቶ ስለዚህች አለም መጨነቅ ከንቱ እንደሆነ በአንደበት በግብር ይሰብካል እንጂ እርሱ በዚህ የዲያቢሎስ ወጥመድ አይያዝም፡፡ ይወድቃል ነገር ግን ቶሎ ይነሳል የንስሃም ፍሬ ስለማፍራት ይደክማል   

      በዚህ ጊዜ ማነው ኦርቶዶክሳዊው መምህር? እውቀትን ከትህትና ጋር ያስተባበረ? ፍቅርን ከተግሳፅ ጋር ያስተባበረ? እምነትን ከምግባር ጋር ያስተባበረ? ከገንዘብ ፍቅርየራቀ ወደክርስቶስ የቀረበ ማነው? ተዋህዶ ግን ይህን ሰው ትናፍቃለች፡፡
በታምራት ፍስሐ

እግዚአብሔር አምላካችን ለሁላችንም አስተዋይ ልቦናን ያድለን፡፡ አሜን፡፡

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

1 comment: