- በሀ/ስብከቱ የአቡነ ሕዝቅኤል አስተዳደር ሙስናና ጎጠኝነት ባስነሣው ቀውስ ተዘፍቋል
- የሊቀ ጳጳሱ ዘመዶች ከደብር እልቅና እስከ ዕቅብና በከፍተኛ ደመወዝ ተቀጥረዋል
- ሊቀ ጳጳሱ ሥራ አስኪያጁን ያገዱበት ርምጃ የሀ/ስብከቱን አድባራት ተቃውሞ ቀስቅሷል
- ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ በታገዱት ሥ/አስኪያጅ ምትክ ለመመደብ ከሊቀ ጳጳሱ ጋራ እየተሸማገሉ መኾናቸው ተሰምቷል
- ፓትርያሪኩ እግዱ ተነሥቶ ሥ/አስኪያጁ ወደ ሓላፊነታቸው እንዲመለሱና የእግዱ አግባብነት እንዲጣራ ለጠ/ቤ/ክህነቱ ጽ/ቤት የሰጡት መመሪያ አልተፈጸመም፤ ዋ/ሥ/አስኪያጁ እግዱን ለማስፈጸም ዳተኛ ሲኾኑ ሊቀ ጳጳሱ ደግሞ ላልተገባ ርምጃቸው ድጋፍ ለማግኘት የሀ/ስብከቱን አጥቢያ አብ/ክርስቲያን ሓላፊዎች ነገ ስብሰባ ጠርተዋል
- አቡነ ሕዝቅኤል በዕጩነት በቀረቡበት የስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ ድጋፍ ነፍገውኛል ያሏቸውን እየተበቀሉ ነውን?
የጥቅምት 2005 ዓ.ም ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በአራት አህጉረ ስብከት እንዲከፈል ሲወስን በሀ/ስብከቱ የተንሰራፋውን የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግር በዘላቂነት እንደሚፈታው በመታመኑ ነበር፡፡ ምልአተ ጉባኤው ስለ ውሳኔው ያወጣው መግለጫ ቃል የሚከተለውን ይላል፡-
በቅ/ሲኖዶስ የተቋቋመው ኮሚቴ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ችግር ለመፍታት አጥንቶ ያቀረበውን ጥናታዊ ጽሑፍ የመረመረው የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በጥናቱ መሠረት የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በአራት አህጉረ ስብከት ቢከፈል ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ቅርበት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚችል ከመኾኑም በላይ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አካባቢ የሚታየው የአስተዳደር ችግር በዘላቂነት እንደሚፈታው በመታመኑ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በምሥራቅ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን፣ በደቡብ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት እንዲደራጅ ወስኗል፡፡
የምልአተ ጉባኤውን ውሳኔ አስመልክቶ የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ከብዙኀን መገናኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ በወቅቱ በሰጡት ምላሽ÷ ‹‹አቤት ባዩ በዛ፤ ጩኸት በዝቷልና ሁሉም በአካባቢው እንዲስተናገድ በሊቃውንትም በአባቶችም ተጠንቶ ቀጠሮ ተይዞበት የቆየ ነው፤›› ብለው ነበር፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት አራቱን የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት የሚመሩ ሁለት ሊቃነ ጳጳሳት በምልአተ ጉባኤው፣ ሥራ አስኪያጆችና ጸሐፊዎች በቋሚ ሲኖዶሱና ቋሚ ሲኖዱሱን ለማጠናከር በተመረጡት ሰባት ብፁዓን አባቶች ተመድበው ነበር፡፡ ይኹንና ከኅዳር ወር መጀመሪያ አንሥቶ ተግባራዊ በኾነው የአዲስ አበባ በአራት አህጉረ ስብከት መደራጀት አድባራትና ገዳማት መልካም አስተዳደር አግኝተዋልን? የተንሰራፋው ሙስናና ብልሹ አሠራር ተወግዷልን?
ምላሹ ግልጽ ነው፤ ለውጡ የቅርጽ እንጂ የይዘትም ባለመኾኑ ተጠያቂነትና ግልጽነት የሰፈነበት መልካም አስተዳደር ላም አለኝ በሰማይ ኾኗል፤ የዘመድ አዝማድ አሠራሩና ጎጠኝነቱ አልተገታም፤ ሞያና ሞያተኛው አልተገናኘም፡፡
አሁንም ሹመት፣ ቅጥር፣ ዕድገትና ዝውውር እየተፈጸመ የሚገኘው በውድድርና በፍትሐዊነት ሳይኾን በኔትወርኪንግ /በደላሎች እና አቀባባዮች/ ነው፤ ለደብር እልቅና በአነስተኛ ግምት እስከ ብር 80,000፣ ለጸሐፊነት እስከ ብር 30,000፣ ለስብከተ ወንጌል ክፍል ሓላፊነት ሳይቀር እንደ ደብሩ ገቢ ከብር 10,000 – 15,000 ይጠየቃል፡፡ መዝገብ በሚያውቀው ደመወዝ ከቶም የማይታሰበውን መሬት መያዝ፣ ሁለት ቤት መሥራት፣ የግልም የንግድም መኪኖችን መሸመት ብርቅ አይደለም፡፡
አዲስ አበባ የመንበረ ፓትርያሪኩ መቀመጫና የሁሉም አህጉረ ስብከት ማእከል በመኾኑ ያለውን ቅምጥ አቅም ያህል፣ ይቅርና በመልካም አስተዳደር (ቅጥር፣ ዕድገት፣ ዝውውር) በቅጽ አሟላልና በፐርሰንት አሰባሰብ እንኳ የአህጉረ ስብከቱ ሁሉ አርኣያ ሊኾን አልቻለም፡፡
ይህ አህጉረ ስብከት ቀድሞም÷ ብር 64,000 እጅ መንሻ ሲቀበሉ (አንዱን በደብር እልቅና ለማሾም፣ የደብሩን የሰበካ ጉባኤ ምርጫ ለማጸደቅ፣ የካህናቱንና ሠራተኞችን በጀት ለማጸደቅ) እጅ ከፍንጅ የተያዙት የቀድሞው ምክትል ሥራ አስኪያጅ ርእሰ ደብር በሪሁ አርኣያበሙስና ወንጀል ከመጠየቅ ይልቅ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ትምህርትና ሥልጠና መምሪያ በምክትል ሓላፊነት በማዘዋወር በጎጠኝነት ከተጠያቂነት የማራቅ ሥራ የተሠራበት ነው፡፡
ይህ አህጉረ ስብከት ቀድሞም÷ በአድባራትና ገዳማት በልማት ስም ጉብኝት ሲያካሂዱ ከብር 30 – 50 ሺሕ እየተቀበሉ፣ በታወቁ የጥቅም አቀባባይ ደላሎቻቸው ቅጥር፣ ዕድገትና ዝውውር እየፈጸሙ የቆዩት፣ ከሁሉም በላይ በ2004 ዓ.ም የበጀት ዓመት በቀረበው ሪፖርትከብር ስድስት ሚልዮን በላይ ጉድለት የተገኘባቸው የሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣ ለዓመታት ድኻውን እየበደሉ ፍርድ እያጓደሉ ተቋማዊ ለውጥን የማምከን ሚናቸውን ሲጫወቱ ወደኖሩበት ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅነት ያለአንዳች ተጠያቂነት የተዘዋወሩበት ነው፡፡
በዚህ አህጉረ ስብከት÷ ርእሰ ደብር በሪሁን በሰንዳፋ፣ ንቡረ እድ ኤልያስ በሰንዳፋና በሌሎች ከሁለት ባላነሱ የከተማ ቦታዎች በገንዘብም በዐይነትም እየዘረፉ ስለሠሯቸው የመኖሪያና የንግድ ቤቶች፣ ስለወሰዱት የቤተ ክርስቲያን መሬቶች የጠየቃቸው የለም፡፡
ዛሬም÷ አዲስ አበባ ለአራት አህጉረ ስብከት ከተከፈለ በኋላ ሙስናው፣ ጎጠኝነቱና ብልሹ አሠራሩ በሰሜንና ምሥራቅ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት መጠነኛ መሻሻል ቢያሳይም በደቡብና ምዕራብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ግን ተባብሶ መቀጠሉ ነው የተዘገበው፡፡ በተለይምበምዕራብ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት በአስከፊ ደረጃ የተስፋፋው የጎጠኝነትና ሙስና ተግባር በቀጥታ ከሊቀ ጳጳሱ ጋራ የተያያዘና በእርሳቸው ዙሪያ የሚያጠነጥን እንደኾነ መገለጹ ሊቀ ጳጳሱን በሚበዛው ምስጉን አቋማቸው የሚያውቋቸውን ብዙዎች አሳዝኗል፡፡
በሀ/ስብከቱ ሥር የሚገኙ 33 ያህል አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አስተዳደሮች ግንቦት 12 ቀን 2005 ዓ.ም ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ እንዳስገቡት የተዘገበው ባለአራት ገጽ አቤቱታ እንደሚጠቁመው÷ ከጠቅላላው የሀ/ስብከቱ 21 የክፍል ሓላፊዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች መካከል 13 ያህሉ ከሊቀ ጳጳሱ ጋራ በአንድ ይኹን በሌላ መንገድ የቅርብ ዝምድና ያላቸው የአካባቢ ተወላጆች ናቸው፡፡ ፊት በአዲስ አበባ አድባራትና በትውልድ ቦታቸው ከብር 300 – 400 በማይበልጥ ደመወዝ ይሠሩ የነበሩ የሥጋ ዘመዶቻቸው በታላላቅ አድባራትከዐቃቢነት እስከ ዋና ጸሐፊነትና አስተዳዳሪነት በከፍተኛ ደመወዝ ተቀጥረዋል፤ በደብር እልቅና የሚገኙ ቀራቢዎቻቸው (ለምሳሌ፡- በጠሮ ቅድስት ሥላሴ) ከደመወዛቸው ወጪ ከፍተኛ አበል (እስከ ብር 2600) እንዲከፈላቸው ተወስኖላቸዋል፤ በዚህም መንገድ በተዘረጋ የጎጠኝነትና ጥቅመኝነት ሰንሰለት በተለይ ግራር ደብረ ዐባይ በሚባለው አካባቢ የሚገኘው የቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን በየሳምንቱ ከ5 – 12,000 ብር በብፁዕነታቸው ስም ይባክናል፤ ሊቀ ጳጳሱም ‹‹የልማት አባት›› እያሉ ሸልመዋቸዋል፡፡ የጋዜጠኝነት ልምድ የሌለውን ዘመዳቸውን በቀድሞው የሀ/ስብከቱ ማኅተምና ፕሮቶኮል ደብዳቤ በሀ/ስብከቱ ልሳን ኆኅተ ጥበብ ጋዜጣ ላይ በምክትል አዘጋጅነት አስቀጥረዋል፡፡
‹‹ሁሉ ቤቱን ሠርቶ እኔ ብቻ ቀርቻለኹ›› በማለት ማማረር ጀመረዋል የሚባሉት ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ከዚህ ቀደም÷ ‹‹ለጳጳስ ቍሪት/ንብረት የለውም – ጎመን የሚዘራበት፣ ሽንኩርት የሚተክልበት፤ ንብረቶቹ ምእመናን ናቸው›› በማለታቸው የተደሰቱባቸው ወገኖችበቡራዩና በሰሚት(?) በሚገኙ የከተማ ቦታዎች ቤት እየሠሩ የመኾናቸው ወሬ ሲሰሙ ‹‹ኧረ ምን ሊኾናቸው›› ብለው ማዘናቸው አልቀረም፡፡ ‹ሥራውን›ም የሀ/ስብከቱ ሓላፊዎች እንዲያስተባብሩላቸው ያዝዟቸዋል ተብሏል – ልክ እነንቡረ እድ ኤልያስ ‹‹አምስቱ ከለባት›› የሚባሉትን የደብር አለቆች፣ ጸሐፊዎች፣ ሒሳብ ሹሞች፣ ቁጥጥሮችና ገንዘብ ያዦች ቢያጆ አሸዋና ሲሚንቶ እያስገለበጡ እንዳሠሩት ማለት ነው፡፡
ሊቀ ጳጳሱ ለቤት ሥራው እንዲተባበሯቸው ከሚያገብሯቸው የሀ/ስብከቱ ሓላፊዎች አንዱ ሥራ አስኪያጁ መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራው ናቸው፡፡ በሀ/ስብከቱ የሰፈነውን የሙስናና የዘመድ አዝማድ አሠራር ወደ ዐደባባይ አውጥቶ አነጋጋሪ ያደረገው አጋጣሚ፣ ሊቀ ጳጳሱ የምዕራብ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ በመኾን በቋሚ ቅ/ሲኖዶስ ውሳኔ የተመደቡትን መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይን ባለፈው ሳምንት፣ በቁጥር 765/4/05 በቀን 07/09/2005 ዓ.ም ከሓላፊነታቸው ከማገዳቸው ተያይዞ ተነሥቷል፡፡
የእግዱ ምክንያት ‹‹ከሊቀ ጳጳሱ ዕውቅና የተሠሩ ሥራዎች ናቸው››ቢባልም ከሊቀ ጳጳሱ ዕውቅና ውጭ አንዳችም ነገር አለመፈጸማቸውን ነው አባ ኅሩይ ሲናገሩ የሚደመጡት፡፡ ‹‹እርሳቸው ያልመሩትን ሥራ አልሠራኹም፤›› የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፣ በሀ/ስብከቱ የተሰገሰጉና የጥቅም ሰንሰለት የዘረጉ ‹‹የሊቀ ጳጳሱ ቤተሰቦች›› በሊቀ ጳጳሱ ስም የሚፈጽሙትን ሕገ ወጥ ተግባር እንዲጠነቀቁበት ገልጠው መናገራቸው ከበደል እንደተቆጠረባቸው ያስረዳሉ፡፡
በሥራ አስኪያጅነት የተመደቡት በቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ እንደኾነ ያስታወሱት መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ፣ ከሓላፊነት የታገዱበት ርምጃ በራሱ ‹‹አቡነ ሕዝቅኤል በሌላቸው ሥልጣንና ሓላፊነት›› የወሰዱት ነው፡፡ በመኾኑም‹‹ይህ ዐይነቱ አሠራር ለቤተ ክርስቲያኗና ለእምነታችን አደጋ ኾኖ ከመገኘቱም ባሻገር በታማኝነትና በቅንነት ለማገልገል ለቆሙና ለሚቆሙ ሰዎች የሞራል ስሜት የሚያሳጣ ስለሆነ ያለሥልጣንና ያለሕግ የተጻፈብኝ ደብዳቤ ይነሣልኝ›› ሲሉ በሊቀ ጳጳሱ የተላለፈባቸውን እግድ በመቃወም ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ የጻፉት ደብዳቤ ያመለክታል፡፡
በሌላ በኩል ሊቀ ጳጳሱ በሥራ አስኪያጁ ላይ ያስተላለፉትን እግድ ተቃውመዋል የተባሉት የሀ/ስብከቱ አድባራት አስተዳደሮች፣ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ በጽሑፍ ባስታወቁት ዝርዝር አቤቱታቸው÷ ሊቀ ጳጳሱ ሥራ አስኪያጁን መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይንና የቀድሞውን ጸሐፊ መጋቤ ሥርዐት ደስታ ጌታሁንን ከሓላፊነት በማገድና በማንሣት የወሰዷቸው ርምጃዎች መንሥኤ ‹‹ጎጠኝነትና ሙሰኝነት ነው›› በሚል እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል፡፡
በተቃውሞ አቤቱታው ላይ የተጠቀሰውና በሊቀ ጳጳሱና በሥራ አስኪያጁ መካከል ለተፈጠረው አለመግባባት ዋነኛ መነሻ የተባለው ግን፣ በስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ ጋራ ከሀ/ስብከቱ በመራጭነት እንዲሳተፉ የተለዩት ሰዎች ትውልዳዊ ማንነት መኾኑ በእጅጉ አሳዛኝ ነው፡፡ በአቤቱታው እንደተመለከተው፣ ከሀ/ስብከቱ ተወክለው በፓትርያሪክ ምርጫው እንዲሳተፉ ከተለዩት 13 ልኡካን 12ቱ(ሥራ አስኪያጁ ሲቀሩ) የምርጫ ሕጉ ድንጋጌ እንደሚያዝዘው ሊቀ ጳጳሱ በሚመሩት የአስተዳደር ጉባኤ ሳይሆን በሊቀ ጳጳሱ ቀጥተኛ ውሳኔ የተመረጡቀራቢዎቻቸውና ዘመዶቻቸው ናቸው፡፡
12ቱ መራጭ ልኡካን ሀ/ስብከቱ ካሉት 33 ያህል አጥቢያዎች መካከል ከስድስት አጥቢያ ብቻ የተመረጡ ነበሩ የሚሉት የዜናው ምንጮች፣ ሥራ አስኪያጁ እንደ ሊቀ ጳጳሱ ቃል በሊቀ ጳጳሱ ቀጥተኛ ውሳኔ የተመረጡትን ልኡካን በቃለ ጉባኤ አስደግፈው ለአስመራጭ ኮሚቴው እንዲልኩ የተላለፈላቸውን ትእዛዝ አለመቀበላቸው ግልጽ ግጭት ውስጥ እንደከተታቸው ያብራራሉ፡፡ በምትኩ የሀ/ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ ባካሄደው ‹‹የብሔር ተዋፅኦ የጠበቀ›› የመራጮች ልየታ በፓትርያሪክ ምርጫው የሊቀ ጳጳሱ ደጋፊዎች እንዲኾኑ የተዘጋጁት ልኡካን በቁጥር በማነሳቸው ለሥራ አስኪያጁ ‹‹ከምርጫው በኋላ እንገናኝ›› የሚል ዛቻ እንዳተረፈላቸው ምንጮቹ አልሸሸጉም፡፡
የአቤቱታው አቅራቢዎች እንደሚያምኑት፣ አሁን መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይን ከሥራ አስኪያጅነት ሓላፊነት በማገድ የተገለጸው ርምጃ ‹‹የአቡነ ሕዝቅኤል የፓትርያሪክነት ሥልጣን ጥማት የወለደው በቀል›› ነው፤ ሊቀ ጳጳሱ ከምደባቸው ጀምሮ የጠሏቸውን አባ ኅሩይን ከሥራቸው ሊያሳግድ የሚያስችል በቂ ምክንያት ይነቀስ ቢባል ከስም ማጥፋት ያለፈ አንድም ነጥብ እንኳ ማቅረብ እንደማይቻልም ርግጠኞች ናቸው፡፡ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ያቀረቡትን አቤቱታ ሲያጠቃልሉም ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠባቂዋና መሪዋ እንደመኾንዎ መጠን ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል እያራመዱ ያሉት ግፍና በደል ሙስናና ዘረኝነት ቆሞ ከዚህ ሁሉ የጸዳ ሥራ እየሠሩ ያሉት አባ ኅሩይ ከቅዱስነትዎ መመሪያ ወርዶ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እስኪዛወሩ ድረስ አቡነ ሕዝቅኤል በሰብል መሰብሰቢያ ወቅት የሰጧቸው እግድ ተነሥቶላቸው የዘሩትን ዘር ምርቱን እንዲሰበስቡ እንዲደረግ ቅዱስነትዎ ቆራጥ አመራርና ርምጃ ወስደው መመሪያ እንዲሰጡልን ከእግረ መስቀልዎ ዝቅ ብለን እናመለክታለን›› በማለት ጠይቀዋል፡፡
የሥራ አስኪያጁ ማመልከቻ የደረሳቸው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ÷ የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት ውዝግቡን እንዲያጣራ፣ የማጣራቱ ተግባር እስኪጠናቀቅ ድረስ በሊቀ ጳጳሱ የተላለፈው እግድ ተነሥቶ መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወደ ሓላፊነታቸው ተመልሰው ሥራቸውን እንዲቀጥሉ አባታዊ መመሪያ መስጠታቸው ተሰምቷል፡፡ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ መመሪያው በብፁዕ ዋ/ሥራ አስኪያጁ ወይም በጽ/ቤታቸው ተፈጻሚ እንዳልኾነ የተገለጸ ሲሆን ይህም የቅ/ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ በኾኑት ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤልና በብፁዕ ዋ/ሥራ አስኪያጁ አቡነ ፊልጶስ መካከል ባለው ተዘምዶ የመረዳዳት ኹኔታ ተደርጎ ተወስዷል፡፡
ለፓትርያሪኩ እንደ ልዩ ሀ/ስብከት በሚቆጠረው አራቱ የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት በአንዱ በተፈጠረው በዚህ አለመግባባት፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በሰጡት መመሪያ ቅር የተሰኙት አቡነ ሕዝቅኤል በበኩላቸው÷ ለእግድ ርምጃቸው ድጋፍ ለማሰባሰብ ይመስላል የምዕራብ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎችን፣ ጸሐፊዎችን፣ ሒሳብ ሹሞችን፣ ቁጥጥሮችንና ገንዘብ ያዦችን በነገው ዕለት በጽ/ቤታቸው ለማነጋገር ስብሰባ መጥራታቸው ተዘግቧል፡፡
* * *
በብፁዕነታቸው ጥንተ ሀ/ስብከት – ከፋ ሸካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት – ጎልተው የሚሰሙ መሰል የመልካም አስተዳደርና ሙስና ችግሮችን ለጊዜው እናቆያቸው፡፡ ብፁዕነታቸው በአዲስ አበባ ደርበው በያዟቸው ሁለት አህጉረ ስብከትና እንደ ቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋልባቸው አስተዳደራዊ ውሳኔ÷ በሐቀኝነት በሚወሰዱና በጥቅመኞች ተጽዕኖ በሚገለባበጡ አቋሞቻቸው መካከል የሚዋልልና ምልስ ቅልስ የበዛበት እንደኾነ ተጨማሪ ማሳያዎች እየተነቀሱ የሚቀርቡባቸው ትችቶች ጥቂቶች አይደሉም፡፡
ትችት (፩)፤ አባ ዮናስ መልከ ጼዴቅ ይባላሉ፡፡ በምዕራብ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት የቶታል ሰፈረ ገነት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ናቸው፡፡ ደብሩ ለሚያሠራው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልገውን ሞያዊ አበርክቶ አቅሙና በጎ ፈቃዱ ባላቸው የቤተ ክርስቲያን ልጆች በማሟላት ከ20 ሚልዮን ብር በላይ ወጪ ለማዳን ከምእመናን የቀረበላቸውን ሐሳብ በተለያዩ ስልቶች ውድቅ በማድረግ፣ በጥቅም ለተሳሰሩት አካል ያለግልጽ ጨረታ ይሰጣሉ፡፡ ምእመናን አካሄዱን ተቃውመው አምስት ጊዜ ወደ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል እየተመላለሱ አቤት ቢሉም የብፁዕነታቸው አቋምና ውሳኔ ከአስተዳዳሪው ጋራ ነበር፡፡
ይኹንና ምእመናኑ አቤቱታቸውን አጠንክረው ለበላይ አካል በማሰማታቸው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ለመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ምክትል ሥ/አስኪያጅ በሰጡት መመሪያ አላግባብ በጥቅም ትስስር የተሰጠው የሕንጻ ግንባታ ፕሮጀክት አፈጻጸም ውሳኔ ተሽሮ ቤተ ክርስቲያን በልጆቿ ሞያዊ በረከት እንድትገለገልና ከከፍተኛ ወጪ እንድትድን ተደርጓል፡፡
ብፁዕነታቸው ግን በውሳኔው ደስ አልተሰኙም፡፡ እንዲያውም እልክ በመጋባት ይመስላል ከደብረ ሣህል ጻድቃኔ ቅድስት ማርያም እስከ መርካቶ ደ/ኀ/ቅ/ ራጉኤል የቤተ ክርስቲያንን መሬትና ንብረት እየሸጡ የግል ጥቅማቸውን በማካበት፣ ከዚህም ጋራ በተያያዙ የፍ/ቤት ክሦችና ንጽሕ ከመጠበቅ አኳያ በሚቀርቡባቸው አቤቱታዎች የሚታወቁትን የደብሩን አስተዳዳሪ በጅቡቲ ደ/ፀ/ቅ/ገብርኤል አስተዳዳሪነት ለማሾምጥረው አድርገው የነበረ ቢኾንም ይህም አልሠመረላቸውም – ከፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤትና የውጭ ግንኙነት የበላይ ሓላፊ ቢሮ የወጣው ትእዛዝ እንደሚያመለክተው ጥቅመኛው አባ ዮናስ ለጊዜውም ቢኾን ለዚህ ሓላፊነት የተገቡ ኾነው አልተገኙም፡፡
ትችት (፪)፤ ይኼኛው ትችት ብፁዕነታቸው በቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊነት ካለባቸው ሓላፊነት ጋራ የሚያያዝ ነው፡፡ ችግሩ በአጭሩ ሲገለጽ በድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ሥራ የተፈጸመውን ሙስናና ምዝበራ ይመለከታል፡፡ በውለታ ከተያዘው ጊዜ በአምስት ዓመት በዘገየው የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ግንባታ በአነስተኛ ግምት ከስድስት ሚልዮን ብር በላይ የምእመናን ገንዘብና የቤተ ክርስቲያን ንብረት ለተቋራጩና ለጥቅመኛ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ አባላት ሲሳይ እንደተዳረገ ታምኗል፡፡
ይህም በቀደመው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቁጥጥር አገልግሎት ኦዲት ሪፖርትና ቅ/ሲኖዶስ ዳግመኛ በላከውና በም/ሥ/አስኪያጁ በተመራው አጣሪ ኮሚቴ ሪፖርት መረጋገጡ ተነግሯል፡፡ በተለይም ከመቶ በላይ በሚቆጠሩ ገጾች የተጠናቀረው የአጣሪ ኮሚቴው ሪፖርት ከአባሪ ማስረጃዎች ጋራ የቀረበላቸው የቅ/ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ፣ ለሚመለከተው አካል በአጀንዳ አስይዘው እንዲያስወስኑ በተለያየ ጊዜ ከተደረጉት ጥረቶችና ማሳሰቢያዎች በተፃራሪ ሪፖርቱን ለወራት አግተው የመያዛቸው ምስጢር ለኮሚቴውና ለፍትሕ ፈላጊ የሀ/ስብከቱ ምእመናን ግርታን የሚፈጥር ኾኗል፡፡
* * *
ብፁዕነታቸው በመልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ላይ ባስተላለፉት የእግድ ርምጃና እግዱ ተነሥቶ መንሥኤው እንዲጣራ ቅዱስነታቸው በሰጡት አባታዊ መመሪያ መካከል የታየው ልዩነት የመጀመሪያ እንዳልኾነ የሚናገሩት የመንበረ ፓትርያሪኩ ምንጮች፣ ኹኔታው በአንድ በኩል÷ ብቁ አመራር ከመስጠት አንጻር ብፁዕነታቸው በመሠረቱ ያለባቸውን ውስንነት ያሳያል ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይህን ውስንነት የሚበዘብዙቀራቢና ዘመድ ነን ባይ ጥቅመኞች በብፁዕነታቸው ዙሪያ መበራከታቸውን እና ብፁዕነታቸውም በማወቅም ይኹን ባለማወቅበተጽዕኗቸው መጠለፋቸውን እንደሚያረጋግጥ ያምናሉ፡፡
አሁን በአባ ኅሩይ ላይ የተላለፈውን እግድ መጽናት የሚጠባበቁ ሁለት ግለሰቦች እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡ አንዱ፣ የፓትርያሪኩን ልዩ ጽ/ቤትና የውጭ ግንኙነት መምሪያ በሓላፊነት የመቆጣጠር ተስፋቸው የጨለመባቸውና ለአራት የተከፈለውን የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት በአንድነት ይዞ ጥቅምን የማስፋትሌላ ከንቱ ተስፋ መሰነቃቸው የሚነገርላቸው ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ናቸው፡፡ ሌላው÷ በቀድሞው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሒሳብና በጀት ክፍልሓላፊ የነበሩቱ ናቸው፡፡ ግለሰቡ የሀ/ስብከት ሓላፊነታቸውን እንደ ትርፍ ጊዜ ሥራ ይሠሩ የነበሩ፣ በሙሉ ጊዜያቸው ግን በአንድ የግል ባንክ ውስጥበአካውንቲንግ ሞያ በመደበኛ ሠራተኝነት የተቀጠሩ፣ በዓለ ሆቴልመኾናቸው ተገልጧል፡፡
ሁለቱም በብፁዕነታቸው ዙሪያ በብፁዕነታቸው ስም ተጽዕኗቸውን ያጠናከሩ ግለሰቦችን በተላላኪነትና በሽምግልና እየተጠቀሙ መኾናቸው ተገልጧል፡፡ በዚህም እንደተባለው በወቅቱ የሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ላይ ያለማስረጃ ተላልፏል የተባለው እግድ ከጸና በቋሚ ሲኖዶስ ስብሰባ በብፁዕነታቸው ለሥራ አስኪያጅነት የመጠቆም ዕድል እንደሚያገኙ ተስፋ ያደርጋሉ¡¡
ይህና ይህን የመሳሰሉት የጥቅመኞች ተስፋዎች ግን÷ በመጪው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከመንበረ ፓትርያሪኩ ጀምሮ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን አስተዳደር በተዋረድ በዘመናዊ መልክ ለማዋቀርና ዘመኑን የዋጀ ቀልጣፋ አሠራር ለመዘርጋት በሚያስችል የባለሞያ ጥናት ላይ ለመወያየት ከጥቅምት ምልአተ ጉባኤ ያደረ አጀንዳ ለያዘው ቅዱስ ሲኖዶስና የቅዱስነታቸው አስተዳደር አንዱ መፈተኛው ይኾናል፡፡
እኒህን የመሳሰሉ የጥቅመኞችን ተስፋዎች መሥመር ማስያዝ÷ በፀረ ሙስናና በልማት እንዲሁም በሰላምና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ የተጠናከረ ሥራ ለመሥራት ከምንጊዜውም በላይ የተዘጋጀች እንደኾነች በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔዎች መግለጫ ላይ ያስታወቀችው ቤተ ክርስቲያናችን ዝግጁነት የሚለካበት እንደኾነ ጥርጥር የለውም፡፡
ምዕራብ÷ ‹‹ዕርበተ ፀሓይ›› የሚፈጸምበት ዐቢይ ማእዘን የመኾኑን ተፈጥሯ ሥራት በምሳሌነት በመያዝ በምዕራብ አዲስ አበባ ሀ/ስብከትአስተዳደር የተቀሰቀሰው ውዝግብ አፈታት÷
- የቤተ ክርስቲያናችን የፀረ ሙሰኝነትና ፀረ ጎጠኝነት አቋም ትርጉም ባለው ደረጃ የሚታይበት፣
- አዲስ አበባ በአራት አህጉረ ስብከት የመደራጀቱ ፋይዳ በቅርጹም በይዘቱም የሚፈተሽበት፣
- ከሁሉም በላይ ያዘቀዘቀችውና ድልህ የመሰለችው የሙሰኞችና ጎጠኞች ‹ጀንበር› ዳግመኛ ላትወጣ ግባቷ (መጥለቋ) የሚረጋገጥበት እንዲኾን እንመኛለን፡፡
‹‹የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ለአራት መከፈል ሙስናውን ጨርሶ ባያስወግደውም ይቀንሰዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡›› /ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ጥቅምት 2005 ዓ.ም/፡፡
ምንጭ: ሐራ ዘተዋሕዶ
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment