(ደጀ ሰላም ጥቅምት 30/2005 ዓ.ም፤ ኖቬምበር 9/2012, READ THE NEWS IN PDF)፦በሃይማኖት ጉዳይ በተነሣባቸው ጥያቄ ምእመኑ ዓይናችሁን ላፈር ያላቸው ብዙ ሰዎች ቢኖሩም በተለይ በበጋሻውና በባልንጀሮቹ ላይ ጠበቅ ያለ አጀንዳ እንደተከፈተባቸው ለረዥም ጊዜ ስንዘግብ መቆየታችን ይታወሳል። ጉዳዩ በቅዱስነታቸው እረፍት እና በመከካሉ በመጣው ጊዜ ክፍተት ተረሣ ቢመስልም “ይደር” ተባለ እንጂ “ይዘጋ” ስላልተባለ እነሆ ርዕሳችን አድርገነዋል። በድጋሚ። ከበጋሻው እንጀምር።
በጋሻው በሊቃውንት ጉባኤ የተያዘበት ጉዳይ ካለፈው ዓመት ግንቦት የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ያደረለት የአንዳንድ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ሐዘኔታ በማትረፍ በአቋራጭ የቅ/ሲኖዶሱን ይቅርታ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ እንዳልሠራለት ታውቋል፡፡ የበጋሻው የኑፋቄ ንግግሮች የተሰራጨባቸውን ቪሲዲዎች እና መጻሕፍት መርምሮ ለምልአተ ጉባኤው የውሳኔ ሐሳብ ለማቅረብ የተቋቋመው የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ኮሚቴ “ግለሰቡ ለጥያቄ ተፈልጎ ስላልተገኘ ወደፊት ቀርቦ እንዲጠየቅና በሚሰጠው መልስ ጉዳዩ እንዲታይ በሚል አስተያየት ታልፏል” በማለቱ ጉዳዩ ሳይወሰንበት ለዚህ ዓመት ድኅረ አቡነ ጳውሎስ ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ተላልፎ የነበረ ቢኾንም ምልአተ ጉባኤው በሥራ ላይ በቆየባቸው ዐሥር ቀናት ከጥምር ኮሚቴው የቀረበለት ነገር አልነበረም፡፡
ይኹንና በጋሻው ምልአተ ጉባኤው በሚካሄድበት ሰሞንና ከዚያም ቀደም ብሎ ባለሟሎቹን ይዞ በሦስት ያህል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ቤት ባደረገው ማግባባት “ከዚህ በፊት ለቅዱስነታቸው የቀረበ የይቅርታ ደብዳቤ አለው፤ እንይለት” በሚል ጉዳዩ በምልአተ ጉባኤው ላይ በብፁዕ ዋና ጸሐፊው በኩል እንዲነሣ ማድረጉ ተመልክቷል፡፡ እነ ብፁዕ አቡነ ገሪማም “ይቅርታ ሊደረግለት ይገባል፤ እንመልከተው” በማለት በድንገት የተነሣው ጉዳይ አጀንዳ እንዲኾን መጣራቸው ተዘግቧል፡፡ የበጋሻውን ማግባባት ከሰብአዊ ርኅራኄ አንጻር የተመለከቱ ሌላው ብፁዕ አባትም “የቤተ ክርስቲያናችን ልጅ ነው፤ ቤተ ክርስቲያናችን ይቅርታ ልታደርግለት ይገባል፤” አሉ፡፡
የምልአተ ጉባኤው አቀባበል ግን በጋሻው “የመስቀሉ ሥር ቁማርተኞች” ለተሰኘው የተቀሰጠ መጽሐፉ በፓትርያርኩ ትእዛዝ፣ በጠ/ቤተ ክህነቱ በጀት እና በመ/ር ዘሪሁን ሙላቱ አዘጋጅነት “የስድብ አፍ” የተሰኘ ምላሽ ከተሰጠው በኋላ (መ/ር ዘሪሁን በቅርቡ በጋሻውንና መሰሎቹን ሃሞን ጎግ በተሰኘ ቪሲዲ ሊደግማቸው ተዘጋጅቷል) ዞሮ ተመልሶ አቡነ ጳውሎስን ይቅርታ እንደ መጠየቅ የቀለለ አልኾነለትም፡፡ በጋሻው ስለ ኑፋቄ ምክንያት መረጃ ከቀረበባቸው ዘጠኝ ግለሰቦች አንዱ እንደኾነ ያስታወሱት ብፁዕ አቡነ ኤልያስ÷ ስሕተት የተናገረባቸው መጽሐፎቹና ቪሲዲዎቹ አሁንም በስርጭት ላይ ባሉበትና በሊቃውንት ጉባኤው ፊት ቀርቦ ለመጠየቅ ባልፈቀደበት ኹኔታ፣ ቤተ ክርስቲያናችንም በሽግግር ላይ ባለችበት ወቅት መናፍቅነቱን የሚሸፍነው የይቅርታ ደብዳቤ ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጽ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡ እግር ላይ ወድቆ የሚለምን ሁሉ ቅን እንዳልኾነ እንዲስተዋልና የልጁ ይቅርታ ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችለው ስሕተት ናቸው የተባሉት ትምህርቶቹ ታይተው ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ ሊኾን እንደሚገባው ለምልአተ ጉባኤው አመልክተዋል፡፡
“ጉዳዩ የሃይማኖት እንጂ በግል የተፈጠረ ጠብ የለም” ያሉት ብፁዕ አቡነ አብርሃም በበኩላቸው÷ በበጋሻው የግለኝነት ተግባርና የስሕተት ትምህርት ምክንያት የሳቱ ግለሰቦች/ቡድኖች በየአህጉረ ስብከቱ እንደሚያስቸግሩ በመጥቀስ የቀረበው ማስረጃ በሚገባ ታይቶ ስሕተቱን እንዲያርም በማድረግ እንጂ በደፈናው ይቅር እንበለው የሚለው እንደማይሠራ አስረድተዋል፡፡ ለ31ኛው የመ/ፓ/አጠ/ሰ/መ/ጉባኤ ላይ የቀረበውና በበጋሻው ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ሳቢያ ከሀ/ስብከት ቁጥጥር ውጭ የሚንቀሳቀስ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እንዲፈጠር ምክንያት ስለመኾኑ የሚያስረዳው የጉጂ ቦረናና ሊበን ሀ/ስብከት ሪፖርት የብፁዕ አቡነ አብርሃምን አስተያየት የሚደግፍ ነው - “በሀገረ ስብከቱ የተፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም ያልተፈቀደ ጉባኤ በአዶላ ወረዳ በክብረ መንግሥት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በሊቀ ጳጳስ የታገደውን ጉባኤ በዲያቆን በጋሻው ደሳለኝ መሪነት ከመስከረም 12 - 14 ቀን 2004 ዓ.ም ድረስ አካሂደዋል፡፡ በዚህም ደብሩ ከሀ/ስብከቱ መመሪያ ውጭ እንዲንቀሳቀስ መንገድ ኾኗል፡፡” /በሪፖርቱ ገጽ (2) ተ.ቁ (7.1) ይመልከቱ/
አሰግድ ሣህሉ
አሰግድ፣ ከሕገ ወጥነት ባሻገር የቤተ ክርስቲያንን ኦርቶዶክሳዊ ማንነት ለመበረዝ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለውስጥ የሚረጩትን ገንዘብ በማስተላለፍ፣ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሕዋሶችን በትምህርት ተቋማት ውስጥ እያደራጀ ደቀ መዛሙርትን በመመልመልና በመቀሰጥ የታወቀ የመናፍቃን ተላላኪ ነው። በሰሞኑ የመንበረ ፓትርያርኩ የመምሪያ ሓላፊዎች ምደባከስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዋና ሓላፊነት ተወግዶ ወደ ሊቃውንት ጉባኤ መምሪያ በአባልነት የተዛወረው መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር ሁለት ጊዜ በጻፈለት የፈቃድ ደብዳቤ÷በአዶላ ወረዳ በሚገኘው በክብረ መንግሥት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተደጋጋሚ ሕገ ወጥ ስምሪት አካሂዷል፡፡ መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር ኦርቶዶክሳዊ ማንነታችንን ለማስጠበቅ፣ ውስጣዊ ሰላሟንና አንድነቷን ለመከላከል ለሚፋጠኑት የፀረ - ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሰባክያን በተደጋጋሚ የነፈገውን ፈቃድ ለአሰግድ በተደጋጋሚ የሰጠው በክብረ መንግሥት ቅ/ሚካኤል ብቻ ሳይሆን በድሬዳዋ ቅ/ሚካኤልም ጭምር እንደነበር ማስረጃዎች ያሳያሉ /የፈቃድ ደብዳቤውን ይመልከቱ/፡፡
በአንጻሩ ባለፈው ዓመት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አሰግድ ሣህሉን ከትምህርት በማገድ አስተዳደራዊ ርምጃ መውሰዱ ይታወሳል፡፡ የኮሌጁ አስተዳደር ጉባኤ በመጀመሪያ አሰግድ ከተመዘገበበት የቀን መርሐ ግብር ወደ ማታው መርሐ ግብር በማዛወር በኋላም ከማታውም መርሐ ግብር ጨርሶ በማገድ የወሰደው ርምጃ በዋናነት ለአቀባበል መሟላት የሚገባውን መስፈርት በትክክል አሟልቶ ከመገኘት ጋራ የተያያዘ ነበር፡፡ በዚህም አሰግድ የሰበካ ጉባኤ አባል ለመኾኑ ከደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን አመጣኹት ያለው ማስረጃ እንደለመደው ለጥቅም ያደሩ ሓላፊዎችን በገንዘብ በመደለል የተገኘ መኾኑ ተረጋግጧል፡፡ በመኾኑም ኮሌጁ÷ ከተቋቋመበት ዓላማ፣ በኮሌጁ ከሚሰጠው የትምህርት ይዘት፣ ይህንንም መነሻ በማድረግ ለተማሪነት ማንን እንደሚመለምል፣ ለምልመላው ማሟያ የኾኑ መስፈርቶችን፣ እነዚህ መስፈርቶች መሟላት አለመሟላታቸውን ለመወሰንእንደ አንድ የቤተ ክርስቲያናችን ነጻ ተቋም በተተወለት ሙሉ ሥልጣን መሠረት አግዶታል፡፡
ይኹንና አሰግድ በወቅቱ ለፓትርያርኩ ቀራቢ የነበሩትን እንደ እጅጋየሁ በየነ ያሉትን ባለሟሎቹን ይዞ የፓትርያርኩን ተጽዕኖ በመጠቀም በኮሌጁ ላይ በከፈተው ክስና በተላለፈው የፍ/ቤት ውሳኔ ፍትሕ ለጊዜውም ቢሆን አንገቷን እንድትደፋ ተደርጋ አሰግድ በማታው መርሐ ግብር በዲግሪ ተመርቋል መባሉ ተሰምቶ ነበር፡፡ የአሰግድ ባልንጀሮች የኾኑና እንደ ግለሰብ በስም ተለይተው የሚታወቁ፣ በኮሌጁ እና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የተሰገሰጉ ግለሰቦች በሚያዘጋጇቸው መፍቀሬ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ብሎጎችም በመቶዎች ከሚቆጠሩ ምሩቃን ደቀ መዛሙርት መካከል የአሰግድን መመረቅ አጽንዖት በመስጠትና በመቀባበል ዘግበው ነበር፡፡ እርሱም ራሱ አሰግድ ቤተ ክርስቲያናችን ካስቀመጠችው የሃይማኖተኝነት እና የዲስፕሊን ጉዳዮች መስፈርት በላይ በመደበኛ ፍ/ቤቶች ቀርቦ በዓለማዊ ሕጎች ሊዳኝና በፍርድ ሊያልቅ የማይችለውን ‹መብት› ከፍ/ቤት አገኘኹት ያለበትን የ‹ድል ዜና› በግል ፕረሶች አዘግቧል፤ ቃለ ምልልስም አድርጓል፡፡
ነገር ግን÷ ከክሱ መጀመር አንሥቶ ኮሌጁ÷ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነቷን ለማስፋፋትና አማኞቿን ለማስተማር ሲባል የተቋቋመ ስለኾነ በዚህ ጉዳይ ፍ/ቤት ውሳኔ ለመስጠት አይችልም፡፡ ውሳኔ ለመስጠት ሥልጣን አለው ከተባለ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደ መግባት ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን ስለሌለው መዝገቡን ይዝጋልኝ” በማለት ሲከራከር ለቆየበት ጉዳይ ታላቅ ድል ኾኖ ሊመዘገብ የሚችል እና ለፍርድ ሂደቱ ቅርበት ያላቸው የሕግ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ደግሞ በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ለሚነሡ ክርክሮች ምሳሌያዊ ማሳያ እና አብነታዊ ኾኖ ሊወሰድ የሚችል ውሳኔ ከፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አግኝቷል፡፡
ሰበር ሰሚው ፍ/ቤት በመዝገብ ቁጥር ሰ/መ/ቁ 77479 በቀን 06/02/2005 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ÷“ከሳሽ [አቶ] አሰግድ ሣህሉ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ላይ ክስ ያቀረቡበት ጉዳይ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37 እንደተደነገገው በፌዴራል ፍ/ቤቶች አማካይነት በፍርድ ሊያልቅ የሚገባው ጉዳይ (justiceable) አይደለም፤” በማለት በይኗል፡፡ በዚህም መሠረት የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ሐምሌ 7 ቀን 2003 ዓ.ም የሰጠው ብይን እና ፍርድ፣ ከፍተኛ ፍ/ቤት ኅዳር 28 ቀን 2004 ዓ.ም የሥር ፍ/ቤት ውሳኔ “የፍርድ ጉድለት የለበትም” በሚል ያሳለፈውና የመጨረሻ ዳኝነት የኾነው ትእዛዝ እንደ ተሻሩ አስታውቋል፡፡ ኮሌጁም ተቋማዊ ሥልጣኑን መሠረት በማድረግ መናፍቁ አሰግድ ሣህሉ በተጭበረበረ ማስረጃ ያገኘውን ዲግሪ በማገድ ጥቅም አልባ እንደሚያደርገው ተመልክቷል፡፡
ሰበር ሰሚው ፍ/ቤት በፍርድ ሐተታው ላይ እንደገለጸው መደበኛ ፍ/ቤቶቹ በክሱ ደረጃ የቀረበላቸውን ጉዳይ ተቀብለው ወደ ዋናው የክርክር ይዘት ዘልቀው ከመግባታቸው በፊት ግራ ቀኙን ያከራከረውና ክስ የቀረበበት ጉዳይ በፍርድ ሊያልቅ የሚገባው ነው ወይስ አይደለም፤ ፍ/ቤቶችስ ጉዳዩን አይተው ለመወሰን ሥልጣን አላቸው ወይስ የላቸውም የሚሉትን በቅድሚያ የመመርመርና የማየት ግዴታ እንዳለባቸው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37 ሥር መደንገጉን አውስቷል፡፡ ዝርዝር ሕግ በኾነው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር ላይም ቢሆን መደበኛ ፍ/ቤቶች የቀረበላቸውን ማናቸውም ጉዳይ ያለገደብ ተቀብለው ለማስተናገድ የሚያስችል ሥልጣን እንደሌላቸው አመልክቷል፡፡ አንድ ሰው በፍ/ቤት ክስ አቅርቦ ለማስወሰን የሚችልበትን መንገድ ሲያስረዳም ከሕግ የመነጨ መብት ያለው መኾኑን በክሱ ዝርዝር በፍሬ ነገር ደረጃ ማመልከት የቻለ እንደኾነ ብቻ ስለመኾኑ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 33(2) ድንጋጌን ጠቅሷል፡፡
ከዚህ አኳያ ከሳሽ ለትምህርት ከገባበት ኮሌጅ ያለ አግባብ የተሰናበተ ስለመኾኑ ገልጦ ባቀረበው የፍሬ ጉዳይ ክርክር አንጻር ማጣቀሻ ሊኾን የሚችል የአገሪቱ የሕግ ማዕቀፍ አካል የኾነን ሕግ መሠረት አድርጎ ክርክሩን እንዳላቀረበ በሰበር ሰሚው ፍ/ቤት የፍርድ ሐተታ ላይ ተመልክቷል፡፡ ይልቁንም የተማሪዎች ምልመላ እና የምልመላ መስፈርቶች እንዲሁም የአካዳሚያዊ ዲስፒሊን ጉዳዮች የመወሰን ሥልጣን ቤተ ክርስቲያኒቱ ላቋቋመችው ኮሌጅ የተተወ በመኾኑ ይህን ሊሸፍን የሚችል ዝርዝር ሕግ በሕግ አውጭው በኩል አለመቀረጹን አስረድቷል፡፡ አያይዞም በአሰግድ ሣህሉ እና በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መካከል በተደረገው ክርክር የታየው ፍርድ እና የተላለፈው ውሳኔ የተለያዩ ሙያዎችንና ክህሎቶችን ለማስረዳት እንዲቻል በሚል በተቋቋሙት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጭምር ለትምህርት ነጻነት ሲባል ከላይ የተመለከቱትን ጉዳዮች አስመልክቶ ተመሳሳይ ክርክር ቢነሣ እንኳ እንደ ማናቸውም ጉዳይ ያለገደብ በፍ/ቤት ቀርበው ሊታዩ የማይችሉ ጉዳዮች እንደኾኑ በዐዋጅ ቁጥር 650/2001 መሠረት አብነታዊ ማሳያ (precedence) መኾኑን ችሎቱ ገልጧል /ለዝርዝር ንባብ የሰበር ሰሚውን ችሎት የፍርድ ሐተታና ውሳኔ አራት ገጽ ከዚህ (LINK) ይመልከቱ/፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment