በአርሲ ሀገረ ስብከት በኖኖ ጃዊ ቀበሌ የሚኖሩ 14 ኦርቶዶክሳውያን በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ።
ጥቅምት 18 ቀን 2018 ዓ.ም [ተ.ሚ.ማ/ አዲስ አበባ]
በአርሲ ሀገረ ስብከት ጉና ወረዳ በሚገኘ ኖኖ ጃዊ ቀበሌ የሚኖሩ ኦርቶዶክሳውያን መገዳላቸውን ከቦታው የደረሰን መረጃ ያሳያል።
በደረሰን መረጃ መሠረት በቀበሌው የሚኖሩ 14 ኦርቶዶክሳውያን ከለሊቱ 6:00 ሰዓት አካባቢ በዕለተ ረቡዕ ጥቅምት 13 ቀን 2018 ዓ.ም ለ14 አጥቢያ ከተኙበት ከቤታቸው አስወጥተው የታጠቁ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ሲሆን ስድስቱ ከመገደላቸው ከአንድ ቀን በፈት ቀድመው ታፍነው ተወስደው ነበር ተብሏል።
የተገደሉት ምእመናን የዕድሜ ክልላቸው ከ2 ዓመት ጀምሮ እስከ 76 ዓመት አዛውንት እንደሚገኙበት መረጃው ይገልጻል።
በተጨማሪም ሁለት ሰዎች በጥቃቱ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ለተሻለ ሕክምና ወደ አቦምሳ ከተማ ሪፈር መሄዳቸውን በመረጃው ተያይዞ ተነግሯል፡፡
ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ በቀበሌው ውስጥ የሚኖሩ 8 ኦርቶዶክሳውያን ሌሊት ላይ ከቤታቸው አስወጥተው የታጠቁ ኃይሎች በአሰቃቂ ሁኔታ መግደላቸውን በደረሰን መረጃ ለማወቅ ችለናል።





