· ኮሚቴው ፍጹም ውግዘት የሚገባቸውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ አራማጅ ማኅበራትና ግለሰቦች ለይቷል - ማኅበረ ሰላማ፣ ማኅበረ በኵር፣ የምሥራች አገልግሎት፣ አንቀጸ ብርሃን፣ የቅድስት ልደታ ለማርያም መንፈሳዊ ማኅበር፣ የኢትዮጵያ መንፈሳዊ ተሐድሶ ኅብረት፣ አሸናፊ መኰንን፣ አግዛቸው ተፈራ፣ ጽጌ ስጦታው እና ግርማ በቀለ ይገኙባቸዋል።
· “ሃይማኖቴ እንደ አባቶቼ ነው” ያሉት የአባ ሰረቀ እና “የቅን ልቦና የመንፈሳዊና የፈውስ አገልግሎትን ያቋቋምኹት ልጆቼን የማበላቸው ስለተቸገርኹ ነው” ያሉት የ‹ሊቀ ካህናት› ጌታቸው ዶኒ ጉዳይ ያለውሳኔ ሐሳብ ለምልአተ ጉባኤው ውሳኔ ቀርቧል።
· አባ ጳውሎስ ከጥንተ አብሶ ጋራ በተያያዘ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሕና እንዲመሰክሩ ሊጠየቁ ይችላሉ።
· ሊቃውንት ጉባኤው ተደጋጋሚ ጥሪ አድርጎለት ያልቀረበው በጋሻው ደሳለኝ ዛሬ ጠዋት የሊቃውንት ጉባኤውን ሰብሳቢ በእጅጋየሁ በየነ አማላጅነት ሲለማመጥ ታይቷል፤ ሊቃውንት ጉባኤው “በአንድ ወቅት በራስ ቅል ኮረብታ ላይ ኢየሱስና ዲያቢሎስ ቁማር ተጫወቱ . . . ዲያቢሎስም በጨበጣ ገባ” የሚለውና ሌሎቹም ጥንቃቄ የጎደላቸው ንግግሮቹ ፍጹም ውግዘት የሚገባቸው እንደኾኑ አመልክቷል።
· የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን አመራርና መዋቅር ይሻሻላል፤ በጠቅላላ ጉባኤና በቦርድ ይመራል፤ የኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር እንደሚኾኑ ተጠቁሟል።
· የማኅበራት መመሪያ ረቂቅ ለውይይት ቀርቧል፤ አሁን ባሉበት አኳኋን ከቀጠሉ “ሌላ ሲኖዶስ ይኾናሉ፤ የፖሊቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ ይኾናሉ፤ በቀኝ ዘመምና ግራ ዘመም አቋም ቤተ ክርስቲያኒቷን ይውጣሉ/ይከፍላሉ” የሚል ስጋት የቀረበባቸው ማኅበራት ንብረት በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ተጠቃልሎ እንዲተዳደር ሐሳብ ቀርቧል፤ የመመሪያውን ረቂቅ በጥንቃቄ የተመለከቱት የምልአተ ጉባኤው አባላት ጉዳዩ በይደር እንዲታይ አድርገዋል።








