Tuesday, May 8, 2012

ሊቀ ስዩማን ኀ/ጊዮርጊስና አቡነ ፋኑኤል ሴራ ሪፖርታዥ(ክፍል ሁለት)

    
    ኃይለጊዮርጊስ ጥላሁን
  • የጆቢራዎቹን ህገወጥ ደብዳቤ ያከሸፉት ቆሞስ መላእከ ጽዮን አባ ሕሩይ ወንድይፍራው ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊነታቸው ተነስተው የማደራጃ መምሪያው ምክትል ሓላፊ የነበረው መምህር እንቁባህርይ ተከስተ በቦታው ተሹመዋል፡
· የመምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቀለምንጦስ “እኔ በማላውቅበት ኹኔታ የመምሪያው ሓላፊ ሊቀየሩ አይችሉም” በማለት ርምጃውን ተቃውመዋል፡፡
· ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ለተሃድሶ መናፍቃን ከለላ መስጠቱን ቀጥለውበታል፡፡
· ብጹዓን ሊቃነጳጳሳት የቤተክርሰቲያን ዋነኛ ችግር የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ለህገ ቤተክርስቲያን ተገዥ አለመሆናቸው መሆኑን ተናግረዋል·

ዝርዝሩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል
(አንድ አድርገን ሚያዚያ 30 ፤ 2004ዓ.ም)፡- በክፍል አንድ ዘገባችን የጆቢራዎቹ ህገወጥ እንቅስቃሴ ቆሞስ መላእከ ጽዮን አባ ሕሩይ ወንድይፍራው ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃለፊ ያከሸፉት ቢሆንም እርሳቸው ላይ ተጽእኖ ለማሳደር ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን፤ ባለፈው አርብ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ የጨለማው ሲኖዶስ አባላት የፈጸሙትን ሸፍጥ ዝርዝሩን ለማቅረብ ቃል በገባነው ቃል መሰረት ይዘን ቀርበናል፡፡

መንግስት ከአክራሪ እስልምና ጋር በተያያዘ ሐሙስ ምሽት መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ከሰሞነኛው የጠቅላይ ሚኒሰትሩ ንግግር መነሻ በማድረግ ማኅበረ ቅዱሳንን በተመሳሳይ መንገዱ ለመፈረጅ የተሃድሶ መናፍቃን ልሳን የሆኑ ድረ-ገጾች ሲያስተጋቡ ነበር፡፡ ለተሃድሶ መናፍቃኑ ሽፋን እየሰጡ ያሉት ቅዱስነታቸው አርብ ከሰዓት በኋላ ለርክበ ካህናቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ከየአህጉረስ ብከቶቻቸው ለስብሰባው አዲሰ አበባ የገቡትን ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት አስቸኳይ ጉዳይ ስላለ ለአርብ ከሰዓት በኋላ 9፡00 ላይ እንዲገኙ ጥሪ ያስተላልፈሉ፡፡ በጉዳዩ ላይ የፓትሪያሪኩ ቃኝ እጅ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ገሪማ፣ ብጹዕ አቡነ ማርቆስ፣ ብጹዕ አቡነ ፋኑኤል፣ ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ ከፓትሪያሪኩ ጋር ቀድመው መክረውበታል፡፡ የጨለማው ሲኖዶስ ሃሳብ እውን ለማድረግ ተስማምተው ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት ለማሳመን ተዘጅተው ነበር፡፡ የስብሰባው አጀንዳ ቅዱስነታቸው እንዲህ ነበር የገለጹት “መንግስት ትናንት ማታ አክራሪነትን በተመለከተ መግለጫ እንዳወጣ ሰምታችኋል? እኛም ጋር ችግር አለ ፤ ስለዚህ እኛም መግለጫ ማውጣት አለብን፡፡”ይላሉ፡፡ማን ነበር? “ቤተክህነቱ መንግስት ያሰበውን ብቻ ሳይሆን ወደ ፊት ሊያስበው ይችላል ብለው ያሰቡትን ለመፈጸም ይፋጠናሉ” ያለው? ብጹአን ሊቃነ - ጳጳሳት “እኛ ጋር ያለው ችግር አላወቅነውም ይንገሩን?” ይሏቸዋል፡፡ አስቀድመው ከቅዱስነታቸው ጋር የመከሩት አራቱ ሊቃነ ጳጳሳት(ብጹዕ አቡነ ገሪማ፣ ብጹዕ አቡነ ማርቆስ፣ ብጹዕ አቡነ ፋኑኤል፣ ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ) “ይሄ እኮ የታወቀ ነው” ይላሉ በደፈናው:: ብጹዕ አቡነ ቀውስጡስና ብጹዕ አቡነ ህዝቅኤል “ ቅዱስ አባታችን እንኳን ከርስዎ መጣ እንጂ እኛ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለው ችግር እርስዎ ነዎት፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ተሰብስበን እንወስናለን አንዱም አይተገበርም፡፡ ለህገ ቤተክርስቲያን እየተገዙ አይደለም::” በማለት የቤተክርሰቲያን ዋነኛ ችግር የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ለህገ-ቤተክርስቲያን ተገዥ አለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡ እንደተለመደው ከባድ ተቃውሞ ሲገጥማቸው እንደሚያደርጉት ለግማሽ ሰዓት ያህል በዝምታ ብቻቸውን የቆዩ ሲሆን በዚህ ጊዜ ብጹዓን ሊቃነጳጳሳት በጸሎት ዘግተው እንዲያሰናብቷቸው በትዕግስት ጠብቀዋቸዋል፡፡


ይህ ነገር አልሳካላቸው ሲላቸው አርብ ቀን አመሻሹ ላይ 11፡00 አካባቢ ደግሞ ሌላ ሸፍጥ ተጠነሰሰ፡፡ ለተሃድሶ መናፍቃንን ስውር አጀንዳ ላለመፈጸም ቤተክህነቱ ያጣውን ጥብዓት ያሳዩትን ቆሞስ መላእከ ጽዮን አባ ሕሩይ ወንድይፍራው ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊነታቸው በማንሳት፤ ከተሃድሶ መናፍቃን ቅጥረኞች ጋር የጥቅም ትስስር ያለው የማደራጃ መምሪያው ምክትል ሓላፊ የነበረው መምህር እንቁባህርይ ተከስተ በቦታው ተሹሟል፡፡


ህገወጡን ደብዳቤ ከኃ/ጊየርጊስ ጋር በመሆኝ ሲያስፈጽም የነበረውን የመምሪያው ጸሐፊ የነበረውን መ/ር መኰንን ወልደ ትንሣኤ ደግሞ የመምሪያ ምክትል ሓላፊ ሆኗል፡፡የመምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቀለምንጦስ “እኔ በማላውቅበት ኹኔታ የመምሪያው ሓላፊ ሊቀየሩ አይችሉም” በማለት ርምጃውን ተቃውመዋል፡፡

ማህበረ ቅዱሳን ከአባ ሠረቀብርሐን ጋር በመሆን ላለፉት ሰባት ዓመታት የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት ሲያደናቅፍ የነበረውን የማደራጃ መምሪያው ምክትል ሓላፊ የነበረው መምህር እንቁባህርይ ተከስተን ባለፈው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ከኃላፊነት አንዲነሱ ጠይቆ እንደነበረ ይታወቃል ፤ በጊዜው የአባ ሠረቀብርሐን ጉዳይ እልባት ያገኝ ሲሆን መምህር እንቁባህርይ ጉዳይ ተድበስብሶ በመቅረቱ ማህበሩን አሁን ዋጋ ሊያስከፍለው እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡ የጨለማው ሲኖዶስ አባላት ቤተክህነቱን በከፍተኛ ሁኔታ እያመሱት ይገኛሉ ፤ ይህን ህገ ወጥ ስራቸውንም አባቶች እና ምዕመኑ እንዲያውቁት የማድረግ ስራ ከማህበሩ ይጠበቃል ብለን እንገምታለን፡፡ በተለይ ኀ/ጊየርጊስ በሚመለከት ያሉትን ማስረጃዎች ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እንዲሁም ለምእመናን ይፋ እንዲያደርግ እየተጠየቀ ነው፡፡
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment