- ማኅበረቅዱሳን የመምህር ዕንቁባህርይ ተከሰተ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪ ዋና ሃላፊነት ሹመት ህገወጥ መሆኑን አስታወቀ፡፡
- የአቡነ ጳውሎስና የአቡነ ሣሙኤል ውዝግብ የአሁኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ዋነኛ አጀንዳ እንደሚሆነ እየተነገረ ነው፡፡
- ጥንተ አብሶንና የተሃደሶ መናፍቃን አስተባባሪዎችን አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖድስ ሃይማኖታዊ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
- የገዳማትንና የሰሜን አሜሪካን አስመልክቶ በስፋት እንደሚነጋገር ይጠበቃል፡፡
(አንድ አድርገን ግንቦት ልደታ 2004ዓ.ም)፡- የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሃላፊነት ሹመት ህገወጥ የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች ህብረትም የተቃወመው ሲሆን ተቃውሟቸውን የፊታችን ቅዳሜ ይገልጣሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ተቃወሟቸውን አንዳይገልጹ የተለያዩ አካላት ተጽዕኖ ለማሳደር እየጣሩ ይገኛሉ፡፡ በቤተክህነቱ እየተስተዋለ ለመጣው ህገወጥነትና የማፍያ ተግባር በምክንያትነት እንዲሁም ህገ ቤተክርስቲያን በመጣስ፣ ለታህድሶ መናፍቃን መሸሸጊያ በመሆን ቤተክርስቲያኗን ለማፍረስ ለጨለማው ቡድን ወግነዋል፣ አባታዊ ግዴታቸውን አልተወጡም ተብሎ የሚታመነው የፓትሪያሪኩ ጉደይ የመጨረሻ ውሳኔ እደሚሰጥም ይጠበቃል፡፡
መደበኛው የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ትናንት ሚያዚያ 30 ብጹዓን ሊቃነጳጳሳት በተገኙበት በጸሎት ተጀምሯል፡፡ በህገወጥ የጨለማው ቡድን አቀነባባሪነት ቤተክህነቱ ሲታመስ በመሰንበቱ ጉባኤው በደራሽ አጀንዳዎች አንዳይጠመድ ተፈርቷል፡፡ጉባኤው ዛሬ ጠዋት አጀንዳ አርቃቂ ኮሜቴ ሰይሞ ከሰዓት በኋላ አጀንዳዎችን እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል፡፡ ቤተክርስተያን አሁን ካለችበት ነባራዊ ሁኔታና ቤተክህነቱ ሰሞኑን ሲያስተናግደው ከነበረው ትዕይንት አንጻር የሚከተሉትን አጀንዳዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚነጋገር ይጠበቃል::
1. የአቡነ ጳውሎስና የአቡነ ሣሞኤል ውዝግብ፡-ከሀምሌ 2001 ዓ.ም ተጀምሮ የነበረው የአቡነ ጳውሎስና የአቡነ ሣሙኤል ውዝግብ ለጊዜው ጋብ ያለ ቢመስልም ከአንድ ወር በፊት አቡነ ጳውሎስ በጻፉት ደብዳቤ አቡነ ሣሞኤል በልማት ኮሚሽኑ ለሚወጣ ወጭ ቼክ ላይ እንዳይፈርሙ የከለከሏቸው ሲሆን በአጸፋው አቡነ ሣሙኤል በፓትሪያሪኩ የተሾሙት የልማት ኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር አግደውን ያለርሳቸው ፈቃድ ምንም እንዳያደርጉ አዘዋቸዋል፡፡ ፓትሪያሪኩ ይህን ያደረጉት አቡነ ሣሙኤል ለመበቀል ካላቸው ፍላጎት ባሻገር የልማት ኮሚሽንን ገንዘብ በርሳቸው ቁጥጥር ስር ለማስገባት ያላቸውን ፍላጎት እውን ለማድረግ ነው፡፡ ይሄንን ለመከላከል ብጹዕ አቡነ ሣሙኤል በአቡነ ጳውሎስ የተሸሙትን ዶክተር አግደውን የሚፈጹሙትን ማንኛውን ስራ ያለርሳቸው ፈቃድ እንዳያከናውኑ በማድረግ የአቡነ ጳውሎስ ፍላጎትን በተዘዋዋሪ መንገድ አክሽፈውታል፡፡ከዚህ በተጨማሪ በተመሳሳይ ሰዓት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሃፊ ብጹዕ አቡነ ህዝቅኤል በተመሳሳይ መንገድ ቼክ ላይ እንዳይፈርሙ አግደዋቸዋል፡፡ይህ ፓትሪያሪኩ ከህገ-ቤተክርስቲያን በተጻራሪ የቤተክርስቲያኗን ገንዘብ በእርሳቸው ቁጥጥር እንዲሆን ያላቸውን ፍላጎት ፍንትው አድረጎ ያሳያል፡፡በህገ ቤተክርስቲያን ፓትሪያሪኩ በገንዘብ አስተዳደር እንዳይሳተፉ ይከለክላል፡፡ይህ ስልጣን የጠቅለይ ቤተክህነት ስራ አስኪያጅ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ህገ ቤተክርስቲያንን የሚያስጠብቅ ውሳኔ ይወስናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡.
2. የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ኃላፊ ህገወጥ ሹመትን አስመልክቶ :- ማህበረቅዱሳን ያቀረበውን ጥያቄ መልስ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ማኅበረቅዱሳን ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ ለሁሉም ሊቃነጳጳሳትና ለጠቅላይ ቤተክህነት በ30/08/2004ዓ.ም በጻፈው ድብዳቤ የመምህር ዕንቁባህርይ ተከሰተ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሃላፊነት ሹመት ህገወጥ በመሆኑ በቀጣይ ጊዜያት አብሮ ለመስራት እንደሚቸገር ገልጿል፡፡ማኅበሩ የሹመቱን ህገወጥነቱ ሲያብራራ ህገወጥ የሆኑትን ጆቢራዋችን በመቃወማቸው ቆሞስ መላእከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንዲፍራው ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውና የህገወጥ ቡድኑ አጋፋሪ የነበረው የመምህር ዕንቁባህርይ ተከሰተ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሃላፊነት ሹመት ህገወጥ በመሆኑ መፍትሄ እንዲሰጠው ይጠይቃል፡፡ ብጹዕ አቡነ ቀለምንጦስ የማደራጃ መምሪያው ሊቀ ጳጳስም እርሳቸው የማያውቁት በመሆኑ እንደማይቀበሉት ገልጸው እንደነበር ይታወቃል፡፡የመምህር ዕንቁባህርይ ተከሰተ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሃላፊነት ሹመትን የአዲስ አበባ ስንበት ት/ቤቶች ሕብረትም የተቃወመው ሲሆን ተቃውሟቸውን የፊታችን ቅዳሜ ይገልጣሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ተቃውሟቸውን አንዳይገልጹ የተለያዩ አካላት ተጽዕኖ ለማሳደር እየጣሩ ይገኛሉ
3. የጥንተ አብሶ ጉዳይ፡- አባ ሠረቀ ብርሃን ባሳተሙት መጽሐፍ “እመቤታችን ጥንተ አብሶ ነበረባት” በማለታቸውና ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በፕሪስተን ቲዎሎጅ ሴሚናር ፒኤችዲ መመረቂያ ወረቀታቸው (dissertation) ላይ “እመቤታችን ጥንተ አብሶ ነበረባት”ብለው መጻፋቸውን ውስጥ ውስጡን በቤተክህነቱ ይወራ የነበረውን “እውነትና ንጋት” በሚለው በአባ ሠረቀ መጽሐፍ በአስረጅነት በመጥቀሳቸውና ከቤተክርስቲያኗ አስተምህሮ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የቤተክርስቲያኒቱን መሠረት እምነት እንደሚያጸና ይጠበቃል፡፡
‹‹ ቅድስት ድንግል ማርያም ጥንተ አብሶ (የአዳም የውርስ ሀጥያት) ጥላ ስር የተወለደች ናት››(To read click here) በማለት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እና አባ ሰረቀ ብርሀን እንደሚደግፉት የዛሬ ወር አካባቢ ማስነበባችን ይታወቃል ፤ ይህን ጉዳይ በእኛ ገጽ ከወጣ በኋላ ከ9ሺህ በላይ ሰዎች ጎብኝተውታል ፤ በተለያዩ መጽሄቶች ታትሞ ሰዎች ዘንድ ደርሶ መነበቡን ለማወቅ ችለናል፡፡ በጊዜው አባ ሰረቀ አንድ መጽሄት ላይ በሰጡት አስተያየት ‹‹ሲኖዶሱ በዚህ ጉዳይ ላይ ሁለት ልብ ነው›› ማለታቸው የሚታወቅ ሲሆን ፤ ሙሉ ቃለ ምልለሱ እጃችን ላይ ይገኛል ፤ መረጃውን ለሚፈልግ ሰው ለመስጠት ፍቃደኛ ነን ፤ በዚህ የሲኖዶስ ጉባኤ በዚህ ነገር ላይ ይነጋገራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ መጽሀፉን በፒዲፌ ያንብቡ(To Read click here)
4. የተሃድሶ መናፍቃንን ስውር ሴራ:- በማኅበረቅዱሳንና በስንበት ት/ቤቶች አማካኝነት የተሃድሶ መናፍቃንን ስውር ሴራ አስመልክቶ የቀረበው መረጃ ቅዱስ ሲኖዶስ ያቋቋመው ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳትንና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንን ያሉበት ኮሚቴ አጣርቶ ስለጨረሰ በተሃድሶ መናፍቃንና በግብረ አበሮቻቸው ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡
5. የሰሜን አሜሪካ አህጉረስብከት ያለውን ውዝግብ፡- አቡነ ፋኑኤል የሄዱበትን አፍራሽ አካሄድንና የምእመናን አቤቱታ ለቅዱስ ሲኖዶስ ለማቅረብ ከአኅጉረ ስብከቱ ሰራ አስፈጻሚና ከምእመናን ተወካዩች ከአሜሪካ ወደ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡ይህንን ጥያቄ ለማድበስበስ ቅድመ ጉባኤው በኃ/ጊዮርጊስና በአቡነ ፋኑኤል አማካኝነት የተደረገው ደባ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ለዚህም ሲኖዶሱ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ ይጠበቃል፡፡
6. የገዳማት ጉዳይ፡-የተቃጠሉት የአሰቦትና የዝቋላ ገዳም፣ የወልቃይት የስኳር ልማት ፕሮጀክትና የዋልድባ ገዳም ጉዳይ አጀንዳ እንደሚሆኑ ይገመታል፡፡ ዋልድባን ገዳም አስመልክቶ የማኅበረቅዱሳን አጥኝ ቡድን ሪፖርት ሰሞኑን በተፈጠረው ውዝግብ ምክንያት ለፓትሪያሪኩና ለሊቃነጳጳሳት ካለመድረሱ ጋር ተያይዞ በጉዳዩ ላይ በጥልቀት ውይይት ሳይደረግበት ሊቀር እንደሚችል እየተፈራ ነው፡፡
ከአነዚህ በተጨማሪ ፓትሪያሪኩ የአዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እንደተለመደው እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል፡፡የጨለማው ቡድን ባቀነባበራቸውና ወደ ፊት በሚያቀነባብራቸው ሴራዎች የስብሰባ ጊዜ እንዳይባክንና የቤተክርስቲያኗን ክፉኛ እየጎዷት ያሉት የውስጥ አርበኞች ተጨማሪ ጊዜ እንዳያገኙ ተሰግቷል፡፡ ለዚህም አጀንዳዎችን ለማጽደቅና በቀጣይ ቀናት አጽራረ ቤተክርስቲያንን ለማስታገስና ህገ ቤተክርስቲያን ለማስከበር ለሚወሰኑ ውሳኔዎች የፓትሪያሪኩ እምቢተኝነት ብጹዓን ሊቃነጳጳሳትን እንዳያሰላች ይፈራል፡፡ ይህን ለመከላከል ፓትሪያሪኩን ራሳቸውን አጀንዳ በማድረግና ውሳኔ በማሰተላለፍ ስጋቱን መቀነስ ይቻል ይሆናል፡
እኛ እናንተ መረጃ እንድታገኙ ለማስቻል የቻልነውን ያህል መረጃ ከእናንተው ዘንድ ለማድረስ እንሰራለን ፤ እኛም ከመጻፍ አንቦዝንም እናንተም ከማንበብ አትቦዝኑ መልእክታችን ነው፡፡
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment