Monday, May 7, 2012

(ሰበር ዜና) የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ ከሓላፊነታቸው ተነሡ


·         የዋና ሓላፊው መነሣት በቤተ ክህነቱ የጨለማ ቡድን የተቀነባበረ ነው፤ የአቡነ ጳውሎስ ስውር ትእዛዝና የአቡነ ገሪማ የተለመደ አድርባይነት እንዳለበትም ተረጋግጧል
·         የመምሪያው ሊቀ ጳጳስ “እኔ በማላውቅበት ኹኔታ የመምሪያው ሓላፊ ሊቀየሩ አይችሉም” በማለት ርምጃውን ተቃውመዋል
·         “ተግባሩ በቤተ ክህነታችን እየኾነ ያለው አሳሳቢ ኹኔታ መገለጫ ነው” /ማኅበረ ቅዱሳን/
(ደጀ ሰላም፤ ሚያዚያ 29/2004 ዓ.ም፤ May 7/2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ ከአሿሿማቸው እና ከተሾሙበት ጥቅምት ወር 2003 ዓ.ም አንሥቶ መነጋገርያ የኾኑት በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራው ከሓላፊነታቸው መነሣታቸው ተሰማ፤
የመምሪያው ምክትል ሓላፊ የኾኑት መ/ር ዕንቍ ባሕርይ ተከሥተ በቦታቸው የተተኩ ሲኾን የመምሪያው ጸሐፊ የኾኑት መ/ር መኰንን ወልደ ትንሣኤ ደግሞ የመምሪያ ምክትል ሓላፊ ኾነዋል፡፡ ከዋና ሓላፊነት የተነሡት መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞችና በፓትርያሪኩ ሳይቀር “መጋዘን” እየተባለ ወደሚጠራው መንፈሳዊ ፍርድ ቤት አባል ኾነው እንዲሠሩ ተዘዋውረዋል፡፡
መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ከሓላፊነታቸው ለመነሣት ያበቃቸው በቀድሞው ዋና ሓላፊ አባ ሰረቀ አማካይነት ሲገፋ ለቆየው÷ ማኅበረ ቅዱሳንንና ሰንበት ት/ቤቶችን አሽመድምዶ በማዳከምና በመቆጣጠር የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶን ፕሮጀክት ለማሳከት፣ የግልንና የቡድን ጥቅምን ለማስፈን ምቹ ኹኔታ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ለሚገኘው የቤተ ክህነቱ የጨለማ ቡድን ሤራ አልመች፣ አልታዘዝ በማለታቸው እንደ ኾነ ተዘግቧል፡፡
የጨለማ ቡድኑ ዋነኛ መሪዎች ለረጅም ጊዜ የመምሪያው ም/ሓላፊ ኾኖ ሲሠራ የነበረውና የግል ጥቅሙን በማሳደድ የሚታወቀው ዕንቍ ባሕርይ ተከሥተ፣ ከቀድሞው ዋና ሓላፊ በሚሰጠው ጥቅምና ተስፋ ሥጋዊ ኑሮውን ሲያደላድል የቆየው የመምሪያው ጸሐፊ መኰንን ወልደ ትንሣኤ እና አንዴ ‹ኢሕአዴግ ነኝ፤ ተሰሚነት አለኝ› ሌላ ጊዜ ‹የሲ.አይ.ኤ አባል ነኝ፤ ከዲፕሎማቶች ጋራ እገናኛለሁ› እያለ የሚያጭበርበረው የአቡነ ፋኑኤል ተስፈኛ ይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን ናቸው፡፡
ካለፈው ሳምንት ዐርብ ምሽት ጀምሮ የጨለማ ቡድኑ ሲያካሂድ የቆየውንና ዛሬ ጠዋት ገሃድ የኾነውን አስከፊ ማፊያ ተግባር የመምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል፡፡ ሊቀ ጳጳሱ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ “እኔ በማላውቅበት ኹኔታ የመምሪያው ዋና ሓላፊ ሊቀየሩ አይችሉም” የሚል ተቃውሞ ማሰማታቸው ተገልጧል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ሚያዝያ 24 ቀን 2004 ዓ.ም “ሕገ ወጥ ሕግ አስከባሪዎች” በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ የጨለማ ቡድኑን አባላት “ጆቢራዎች እና ወሮበሎች” በማለት የገለጻቸው ሲኾን ድርጊቱም “በቤተ ክህነታችን እየኾነ ያለው አሳሳቢ ኹኔታ መገለጫ ነው” ሲል ማጋለጡ ይታወሳል፡፡
የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች ለደጀ ሰላም እንደገለጹት በዚህ ሕገ ወጥ ተግባር የፓትርያሪኩ አቡነ ጳውሎስ ቀጥተኛ ይኹንታ እንዳለበት ያመለከቱ ሲኾን ጸሐፊያቸው አቡነ ገሪማ ከጨለማ ቡድኑ አባላት ጋራ ኾነው እንዲያስፈጽሙም ማዘዛቸው ተረጋግጧል፡፡
በአሁኑ ወቅት የጨለማ ቡድኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማኅበረ ቅዱሳንን ከአክራሪዎች ጋራ በመደመር በፓርላማ የተናገሩትን ውንጀላ እንደምቹ አጋጣሚ በመጠቀም መስከረም 12 ቀን 2002 ዓ.ም ከቅዱስ ሲኖዶስ ሥልጣንና ከማኅበረ ቅዱሳን መተዳደሪያ ደንብ በሚጋጭ አኳኋን የተላለፉ ውሳኔዎችን ለማስፈጸም እየጣረ መኾኑ ተገልጧል፡፡ በሌላም በኩል ኹኔታውን ፓትርያሪኩ በቅርቡ በሚጀመረው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያን፣ ከገዳማት ህልውና እና ክብር መጠበቅ ጋራ ተያይዞ ለሚነሡባቸው አጀንዳዎች እንደ ትኩረት ማስቀየሻ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ እየተነገረ ነው፡፡
ከዜናው ጋራ የተያያዙ ዝርዝር መረጃዎችን እንደ ደረሰን እናቀርባለን፡፡  
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

2 comments:

  1. እግዚአብሔር ሆይ ወዴት አለህ??????

    ReplyDelete
  2. "አባ"ሰረቀን ለማውረድ ስንት ዓመት ፈጀባቸው እኚን አባት ግን ለማንሳት ጊዜ አልፈጀባቸውም አሁንስ ክፋታቸው በዝቶ ለቤተክርስትያን ጠላት ሆነው ከመነሳታቸው የተነሳ ሰይጣን እንኳን ያላሰበውን ሐሳብ እያሰቡ ከጎኑ መቆማቸውን በግልጥ እያሳዩት ነው።

    ReplyDelete