በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፣ አሜን።
የአርሲ ክርስቲያኖች ጭፍጨፋ እና የመንግሥት መልስ
ከፌስቡክ ለሦስት ወራት ያህል ዕረፍት ካደረግሁ በኋላ የብፁዕ አቡነ ሉቃስን ዕረፍት ሰምቼ ባለሁበት ሆኜም ቢሆን ሐዘኔን ለመግለጽ ወደ ፌስቡክ ስመለስ የጠበቀኝ የአርሲ ክርስቲያኖች የማያበራ ዕልቂት እና አሁንም የክርስቲያኑ ሐዘንና ለቅሶ ነው። ይገርማል። ከዚህ በፊት ደጋግሜ እንዳልኩት በዚያ አካባቢ አክራሪ ሃይማኖተኞች እና ጽንፈኛ ጎሰኞች ክርስቲያኖችን የተቀናጀ በሚመስልና በታወቀ ዘዴ ይገድላሉ፣ አካል ያጎድላሉ፣ ያፈናቅላሉ፣ የንጹሐኑን ሀብት ንብረታቸውን ይዘርፋሉ፣ ይቀማሉ፤ አብያተ ክርስቲያናትን ያቃጥላሉ፡፡
እኛ ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ እንጮሃለን፣ ስሜታችን እንገልጻለን፣ ከስሜታዊነታችን የተነሣ እኛ በምንፈልገው መንገድ ሐዘኑን ያልገለጸውን ሁሉ ከገዳዮች ጋር እኩል እናወግዛለን፤ እርስ በእርስም እንነቃቀፋለን፣ እነርሱም ይህ ስሜት እስኪቀዛቀዝ ትንሽ ይጠብቃሉ፣ እንደገና ይቀጥላሉ። እንዲህ እያለ ለዐመታት የሚያስቆመው ሳይገኝ ይሄው እስከ ዛሬ እንደቀጠለ ነው፡፡ ይኸ ሁሉ ግፍና መከራ በንጹሐን ላይ ሲደርስ መንግሥት አሁንም ጸጥ ረጭ ይላል። ጩኸቱና ተቃውሞው በጣም ለየት እና በርከት ያለ ሲመስለው እንደ ባለፈው እንዳደረገው የይስሙላ መግለጫ ያወጣል፣ ሁኔታው ሌላ ነው፣ ግጭት ነው፣ የሞተውም ከሁሉም ነው፣ ቁጥሩም በማኅበራዊ ሚዲያ እንደተገለጸው አይደለም፣ ይህንን አጋንነው የሚያቀርቡትን እጠይቃለሁ ይላል። ገዳይ እና አፈናቃዮችን ሳይሆን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ስለጭፍጨፋው አለመቆም የሚጮሁትን አስፈራርቶ አንዳንድ ጊዜም የተወሰኑ ሰባክያንን አጋጣሚውን ተጠቅሞ አስሮ የሰውን ትኩረትም ”ሞትና መፈናቅሉ ይቁም” ከሚል ”የታሰሩት አገልጋዮች ይፈቱ” ወደ ሚል አስቀይሮ ነገሩን በማስለወጥ ይፈጽማል። ከትንሽ ጊዜ ዕረፍት በኋላ ያው ድርጊት ሒደቱ ምንም ሳይለወጥ እንደገና ይደገማል።
ሁኔታውን ለታዘበው ሰው ድርጊቱ በጥሩ ሶፍትዌር ወይም ቴክኖሎጂ ወር ጠብቆ እንደሚከፈል ሒሳብ ወይም ደግሞ ጊዜውን እየጠበቀ እንደሚሠራ ዘመናዊ ማሽን ሆኖ የሚፈጸም ይመስላል እንጂ መንግሥት ባለበት ሀገር በአንድ አካባቢ በገሐድ የሚፈጸም ግድያ አድርጎ ለመቀበል የሚያስቸግር ነው። ይህን የምለው ድርጊቱ እና አፈጻጸሙ የሰውን ምላሽ የተረዳ ብቻ ሳይሆን የሰውን ሐዘንና ለቅሶ ልክ እንደ ሙዚቃ እያየ የሚዝናና እና የሚያላግጥ እጅግ መሠረት የያዘ እና የሚተማመንበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የሚፈጸም መሆኑን ሁሉ እንድናውቅለት ፈልጎ በዚያ ልክ ዕውቅና አልሰጠው በማለታችን የሚበሳጭ እንጂ በድርጊቱ ትንሽ ተጠያቂነት ይኖራል ብሎ የሚገምት አይመስለኝም። የእግዚአብሔር ፍርድ ባይቀርም ይህን አስመስሎ የሚፈጽመውም ዝም ብሎ አይመስለኝም። ሁኔታውን ሳስበው ደግሞ እንኳን ጭፍጨፋው እና ቅንብሩ ይቅርና የእኛም ልቅሶና እና ጩኸትም በእነርሱ ፕሮግራም የተቀረጸ እና የተፈቀደ ያህል ብቻ የሚደረግ እስኪመስለኝ ድረስ የእነርሱን የሥነ ልቡና ዝግጅት እና ሁኔታ ያመለክታል። በአጭሩ ድርጊቱን እንደ ዜጋ እና እንደ ሰው ፣ ደግሞ እንደ ክርስቲያን ተረድተነው በቂ ነገር ማድረግ እንደማንችል በአግባቡ የተረዳ አካል የሚያደርገው መሆኑን ራሱ ዕልቂቱ ደጋግሞ እየመሰከረ ነው።
ስለሁኔታው ከዚህ በፊት በነበሩት ዕልቂቶች ሐዘኔን ስገልጽ በእገላለጼ የሚበሳጩ ሰዎች አስታውሳለሁ። ክርስቲያናዊ ይልቁንም ደግሞ በዐውደ ምሕረት ቆሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ አቅሙ እንደሚናገር ሰው ልናገረው እና ላደርገው የሚገባውን ደጋግሜ አስቤ አውቃለሁ። መጻሕፍትን ለማንበብ፣ ነገሮችን በአግባቡ እና እግዚአብሔር በፈቀደው መንገድ ለማድረግ እንደ ሌሎቹ ሁሉ ጥረት አድርጌአለሁ። ከዚህ የተነሣ የእኔ ገለጻ እና ምላሽ የማይስማማቸው ሰዎች እንዳሉ ሁሉ እኔም የማይስማሙኝን ገለጻዎች እና ምላሾች አያለሁ፣ እንደማይስማሙኝ እና ትክክል አይደሉም ብዬ እንደማስብ ግን በግልጽ ተናግሬ አላውቅም። ዛሬ ግን የማምንባቸውን ሁኔታዎች በትንሹም ቢሆን መግለጽ እፈልጋለሁ።
1) ነገሮችን በእውነተኛ ክርስቲያናዊ ዓይን ለማየት እና በዚያም መንገድ ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት መሞከር አለብን።
በክርስቲያናዊ ዓይን ማየት የምላቸው የሚከተሉትን ነገሮች ነው። በእኔ እምነት እስካሁን በዓለም ካለፉት ክስተቶች እንደተረዳሁት እንዲህ ያሉ ተከታታይ የሆኑ ቀስ በቀስ ክርስቲያኖችንና ክረስትናን የሚጎዱ ድርጊቶች የሚመጡት በአብዛኛው በክርስቲይኖች ኃጢአት ይልቁንም በካህናት ፣ በጳጳሳት እና በሊቃነ ጳጳሳት ኃጢአት ምክንያት ነው። ይህ ልባዊ እምነቴም ጭምር ነው። ነገሩ በታሪክ በተደጋጋሚ በዓለም ላይ ተደጋግሞ የታየ እና የታወቀ ነገርም ነው። ይህን ከታሪክ ማየት እና መማር ይቻላል። ይህ ማለት አሁን እየሞቱ ያሉት ተለይተው በኃጢአታቸው ነው ማለት ግን አይደለም።
በግለሰብ ደረጃ ጻድቁንና ኃጥኡን የሚያውቀው ራሱ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ወይም ደግሞ በማወቁ ምክንያት ስለኃጢአተኛው ምሕረትን የሚለምንና የሚያማልድ እንጂ የማይተች የማይፈርድ እና የማንቅ ጻድቅ ሲኖር በዚህ ቅድስናው ምክንያት እግዚአብሔር ከሚገልጽለት ጻድቅ ውጭ ማንም የማንንም አያውቅም። እግዚአብሔር የአንዱን ኃጢአት ለሌላው የሚገልጸው ያ የተገለጸለት ስለኃጢአተኛው ለምኖለት እንዲድን ሲፈቅድ ወይም እግዚአብሔርን በማይገባ ፈረደ ብሎ አምላኩን እንዳያማርር ለመጠበቅ ሲወድድ ብቻ ነና። እኛ ሌሎችን ኦቆሽሸን እና አሳንሰን ከማየት አልፈን በድፈርት የምንሳደብ እና የምንናገር በኃጢአት ባደፈ ሰውነት ሆነን ነገሮችን ስለምንመለክት ነው። ይህንንም በማድረጋችን ኃጢአት በማብዛት መቅሰፍት እናስጨምራለን እንጂ አናስቀንስም።
ይህን የምለው አይታወቅምም ብዬም አይደለም። ነገር ግን ከታሪክ እና ስለጉዳዩ ከጻፉ አባቶች እንዳነበብኩት እንዲህ ያሉ ክስተቶች ሁላችንንም ለእውነተኛ ንስሐ የሚጠሩ እውነተኛ የእግዚአብሔር ድምጾች ናቸው። እንዲያውም አንድ አባት ”እግዚአብሔርን ቀርቦ ሳለ ጥሩት” የሚለውን ቃል መሠረት አድርጎ እግዚአብሔር የሚቀርብበት ሰዓት የሚባለው እንዲህ ያለው የመከራ ሰዓት እንደሆነና በእንዲህ ያለ ጊዜ አስተውለን መጸለይ እንዳለብን ይመክራል። በዚህ የጥሪ ወቅት የሚገደሉት አብዛኞቹም ለጽድቅና ለክብርም የታደሉ ናቸው። እንዲህ ማለት ግን መግደሉን መቃወም እና ማውገዝ አይገባም ማለት አይደለም። መከራውን ስናወግዝ እና ስንቃወምም መከራ ተቀባዮችም ሰማዕታት አይደሉም ማለታችን አይደለም። ሰማዕታት ናቸው ማለትም ግፉ ይቀጥል ማለት እና ማዘናጋትም አይደለም። እንዲህ ያሉ አገላለጾችን ወደ ጽንፍ ወስዶ ተናጋሪው ያላለውን እንዲህ ልትል ፈልገህ ነው እያልን መነታርክን ማቆም ይገባናል ለማለት ነው እንጂ። ስለሰማዕትነት ጎለቶ የሚነገረው ክርስቲያኖች ከፍርሐት ወጥተው ፣ መከራውን ተሰቅቀው ሃይማኖት ከመለወጥ እና ተመሳስሎ ከመኖር ይልቅ ልክ እንደ አርሲ ክርስቲያኖች ሞትን የማይፈሩ የማይሰቀቁ እና በወንጌል የተጻፈውን ለመፈጸም ከልብ የምንወድድ መሆን አለብን ማለት ነው። ድርጊቱን ስናወግዝም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ትተትን አእምሮአችን በፖለቲካዊ እይታ ብቻ ተይዞ ሰማዕትነትን ማኮሰስ እና ክርስቶስን ማሳዘንም የለብንም።
ታሪክን ካስተዋልነው እኮ በየትኛውም ዘመን ክርስቲያኖች ሲገደሉ የኖሩት በፖለቲከኞች እና ፖለቲካዊ ጥቅም በሚፈልጉ የውስጥ ሰዎችም ጭምር ነው። እኔ እስከማውቀው ድረስ በርበሮች በሰሜን አፍሪካ እና በምዕራባዊ የሮም ግዛት እየገቡ ካደረሷቸው ጭፍጨፋዎች ውጭ ከጥንት እስካሁን ገዳዮች ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ትርፍ ነጋዴዎች ናቸው። ይህ በመሆኑ ግን ችግሩን የሚፈታው በፖለቲካዊ መልስ እና መፍትሔ ብቻ ነው ብለው ክርስቲያኖች እንዲያምኑ አያደርጋቸውም።
ለእኔ እስከሚገባኝ ድረስ እውነተኛ ሰዎች ይህን የመሰለውን ግድያ ለማስቆም ፖለቲካዊ አደረጃጀት ተጠቅመው ለሟቾች እና ለተጎጅዎች ሁሉ ራሳቸውን አሳልፈው ቢሰጡ መጽሐፍ አይቃወማቸውም፣ የተጠላም አይደለም። ብዙዎቹ ሰማዕታትም ወታደሮች እንደነበሩ እንረሳውምና። ነገር ግን እንደዚያ ያሉ መንገዶች ራሱ አዋጭ መሆናቸውን የሚያውቁት መጀመሪያ ክርስቲያኖች በንስሐ ከእግዚአብሔር ጋር ሲታረቁና በጥላቻና በበቀል ስሜት ሆነው ሲነሡ ሳይሆን ስለሟቾች ራሳቸውን አሳልፈው ለመስጠት በፍጹም እውነተኛ ክርስቲናዊ ፍቅር ራሳቸውን ሲሰጡ ነው። በእኔ እምነት ራሱን ስለወንድሙ እና ስለሌላው አሳልፎ የሚሰጥ በዚህ ዘመን ማግኘት ይቸግራል ብዬ አላስብም። ነገር ግን ይህ በተግባር በሌለበት ሁኔታ ያለ አስመስሎ በማኅበራዊ ሚዲያ ማሯሯጥ ለአጥቂዎቹ እና ለከሳሾቻችን እስካሁን በሌለበት የሁለት ወገን አስመስለው ለሚያቀርቡት ሐሰተኛ ክስ ማስረጃ ሆኖ ከመቅረብ ያለፈ ፋይዳ ያለው አይመስለኝም። ከዚህ ይልቅ ዋናው ችግር ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልተናል፣ አልታረቅንም፣ የመታረቅም ፍላጎት ያለን አይመስልም። በየቤተ ክርስቲያኑ ያለው ማኅሌትን ሰበብ ያደረገ ጭፈራ እና ድለቃ ራሱ ፍላጎታችን ለማርካት እንጂ ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅ የምናለቅስ አላደረገንም። ታሪክን ካየን በሶርያ፣ በቱርክ እና በመሳሰሉት የሆነውም እንዲሁ ነበር። ዳር ዳሩን እያጠቃ ፣ ዳር ዳሩን እያጠቃ ቆይቶ በኋላ መካከል ላይ ይመጣል። መካከል ላይ በሚደርስ ጊዜ ደግሞ አደጋውም እልቂቱም ዘግናኝ እና በታሪክ አይረሴ ነው። አሁን እኛም ጋር ያለው ሁኔታ የዚያ ምልክት ማሳያ እንድንመለስ የእግዚአብሔር ጥሪ ነው። ካልተመለስን ደግሞ እርሱ ባወቀ ወደ መሐል ይመጣል፤ ያን ጊዜ በሌሎች ያየነው ሊደገም ይችላል። በእኔ መረዳት አሁን የምናየው እንድንመለስ፣ ንስሐ እንድንገባ በጭፍን ከመሰዳደብ እና ከስሜት ወጥተን ወደ ክርስቶስ ከልብ እንድንመለስ ኃይለኛ ጥሪ ይመስለኛል። ከተመለስን ፣ ከርሱ ጋር ከታረቅን ከማንም ከምንጠብቀው በላይ እኛ ባሰብነው እና በሚመስለን ብቻ ሳይሆን ካላሰብነው እና ከላጠበቅነው ሁኔታ ውስጥ መፍትሔውን እግዚአብሔር ያመጣል። ስለዚህ በመከራ እንኳ የማንመከር ደንዳኖች እንዳንሆን መስማት ይሻለናል። ይህ የፈጣሪ ጥሪ ደግሞ ከሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ ሁላችንንም የሚመለከት ነው። የእነ እገሌ ይበልጣል ከማለት ወጥተን የየራሳችን ኃጢአት አስታውሰን ንስሐ ገብተን ከፈጣሪ ታርቀን ችግሩ ተወግዶ ለማየት ያብቃን።
2) የአርሲና በተመሳሳይ መከራ ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖችን በተመለከተ
በአርሲ መከራ እየተቀበሉ ያሉ ክርስቲያኖች ለእኔ እውነተኛ የክርስቶስ ምስክሮች ናቸው። እስካሁን የሚደረገውን አይተው ሁሉም ግርር ብለው ቦታውን ሊለቁ ይገባቸው ነበር። የገዳዮቻቸውም አሳብ ይህ ይመስለኛል። እነርሱ ግን ማንንም ተስፋ ሳያደርጉ፣ እንደ ሰው ፍርሐት እና ሰቀቀን ባይቀርላቸውም እንደ ክርስቲያን ተስፋ የማይቆርጡ ልክ ያንን ሁሉ ጥፋት እንዳልተፈጠረ ቆጥረው አሁንም በመደበኛ ኑሯቸው መቀጠላቸውን ሳስብ ይህ ያለ እግዚአብሔር ማስቻል የሚቻል እንዳልሆነ በማመን እደነቃለሁ፣ በጽናታቸውም እገረማለሁ። እግዚአብሔር ያስችላችሁ፣ ያበርታችሁ እላለሁ። ከዚህ በፊት እንዳልኩት የአርሲ ክርስቲያኖች ደቡብ ምሥራቅ ቱርክ የሁኗ ኡርፋ (የአብርሃም ዘመኗ ኡር፣ የእነ ቅዱስ ኤፍሬም ዘመኗ ኢዴሳ) እና በአካባቢው የሚኖሩ ትሩፋን የሶርያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችን ይመስሉኛል። እነዚያ ክርስቲያኖች ያን ሁሉ ግድያ፣ ስደት፣ መከራ እና ስቃይ ችለው እየሞቱ፣ እየቀነሱ እየቀነሱ በጣም ትንሽ ሆነው እስካሁን አሉ። ታዲያ ለምን ቦታውን ለቃችሁ አትሔዱም ሲባሉ የመለሱት እየሞትን የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ በሞታችን እየመሰከርን ዳግም ምጽአቱን እንጠብቃለን እንጂ ለቀቀን የትም አንሔድም ነበር ያሉት ። የአርሲዎቹ ክርስቲያኖችም እንደነዛ ለዘር የቀሩ እውነተኛ ክርስቲያኖች ሆነው ይሰሙኛል። ሞታችሁ የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ምስክር ስለሆነ እግዚአብሔር ያጽናችሁ እላለሁ።
ሌላው ክርስቲያን ግን በተቻለ መጠን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በዚያ አካባቢ ላሉ የመከራው ተሳታፊዎች ቢያንስ በገንዘባችን መድረስ ይጠበቅብናል። አስተማማኝ እና ለሁሉም ተጎጂዎች በሚደርስ መንገድ እስከሆነ ድረስ በየትኛውም መንገድ መድረስ ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው። ይህን እያደርግን ከስድድብ እና ከነቀፋ ፣ ከብሽሽቅ እና ካልሆነ ነገር ርቀን በሚዲያም በሚገባው መንገድ ለሚመለከተው አካል ማሳወቅም መልካም ክርስቲያናዊ ተግባር ነው። ይኸ ማለት መንግሥት ባለበት ሀገር በተደጋጋሚ እየደረሰ ያለው፣ ግፍ፣ መከራ፣ ሰደትና የንጹሐን እልቂት አያስቆጭም፣ አያናድድም፣ ስሜታዊም አያደርግም ማለት አይደለም፡፡ ሰዋዊ ስሜታችን እንዳለ ሆኖ፣ ከመጥፎ አጸፋዊ ተግባር ተቆጥበን ለእግዚአብሔር ማመልከታችን፣ በጸሎታችን ማሰባችን፣ ዕርቅ እና ይቅርታ መለመናችን እንደተጠበቀ ሆኖ በሀገር እና በዓለም ፊት ግፉንና በደሉን በማጋነንና በማዛባት ሳይሆን በትትክክል እና የችግሩን ምንጭ ጨምሮ ለሚመለከተው ሁሉና ማቆሚያ ያጣውም መከራ እንዲቆም አስተዋጽዖ ሊያደርጉ ይችላሉ ለሚባሉት ሁሉ ማሳወቅ ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው።
3) ለኢትዮጵያ መንግሥት ያለኝ አሳብ
በአርሲና በአካባቢው ክርስቲያኖች ላይ በሚደርሰው መከራ፣ ጭፍጨፋ፣ መፈናቀል እና እጅግ ስልታዊ ጥቃት ለእኔ ከማንም በላይ የመጀመሪያው ተጠያቂ የኢትዮጵያ መንግሥት ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገር ውስጥ የሚቃወሙት ሰዎች መካከል ሁለት ሦስቱ ባሉበት ድሮን በመተኮስ፣ የተቀናጀ ወታደራዊ ጥቃት በማድረስ በማንም ዘንድ የታወቀ መንግሥት ነው። ከፈለገ ሱዳን ገብቶ፣ ሲፈልግም ሶማሌ ተሻግሮ የሚዋጋ፣ ፍላጎቱን ለመፈጸም የማያመነታ መንግሥት እንደሆነ በተለያዩ ተቋማት የሚወጡ ሪፖርቶች ያሳያሉ። ከትግራይ ጋር በነበረው ጦርነት በሚዲያ በኩራት ይናገር እንደነበረው የሕወሓትን መሪዎች በተንቤን ዋሻዎች ውስጥ ከሚስቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የሚያይ፣ ቤተ ክርስቲያን ሲገቡ አየዋቸሁ ብሎ የሚተኩስ መሆኑን ደጋግሞ በሚዲያ ራሱ ነግሮናል። ‘’ከጠላቶቼ ጋር ያለ ሁሉ ያለምንም መሣሪያ መረጣ ይመታል’’ ሲል ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ የሰማነው በራሱ በመግሥት ሚዲያ ነው። እንዲህ ያለ ‘ረቂቅ ቴክኖሎጂ የታጠቀና ብቃት ያለው መንግሥት’ በየጊዜው በበርካታ ወረዳዎች ከደርዘን በላይ እየገደሉ፣ እያፈኑና እያገቱ የሚሔዱ አርሲ ውስጥ ያሉ አጥቂዎችን ለማየት እንዴት ተሳነው? ወይስ ማየት የሚችለው ወደ ሰሜን ሲሆን ብቻ ነው እንዴ?
ለእኔ ገዳዮቹን ለማጥቃት ባይፈልግ እንኳ ሟቾቹን ለማዳን የሚቸገርበት ምንም ምክንያት አይታየኝም። ምክንያት አለ ከተባለ ብቸኛው ምክንያቱ ፍላጎት ማጣቱ ብቻ ይመስለኛል። ለማዳን ፍላጎት ቢኖረው በፍጹም እንዲህ ሊሆን አይችልም። አንዴ፣ ሁለቴም፣ ሦስቴም፣ አራቴም ተዘናጋ እንበል። በየወሩ፣ በየሳምንቱ ፣ ዓመቱን ሙሉ፣ ለተከታታይ ዓመታት ይህ ሁሉ ሲፈጸም ተጎጂዎችን ካላማዳኑ በላይ በጣም የሚያበሳጨው ፣ መግለጫና ማስፈራሪያ የሚያስወጣው፣ መከራውን በሚዘግቡ አካላት ላይ መሆኑ ፍላጎቱን ያሳብቅበታል። ለእኔ የአርሲ ክርስቲያኖች ሞት የመንግሥት ፍላጎት አይደለም ለማለት የሚያስችል አንድም ምክንያት አግኝቼ አላውቅም። እንዲያውም በቂ ምክንያት ያለው በተቃራኒው ያለውን ለማመን ነው፡፡
ስለዚህ ይህን መረዳቴን ደግሞ ለራሱ ለመንግሥትም ቢሰማም ባይሰማም፣ ለዓለም ማኅበረሰብም ቢያደርግም ባያደርግም መናገር ክርስቲያናዊ ግዴታየ ነው ብዬ አምናለሁ። መንግሥት ፍላጎቱ የዜጎቹ ደኅንነት መጠበቅ ከሆነ አርሲ ውስጥ ሰላም ማምጣት በጣም ቀላል እንኳ ባይሆን በፍጹም ከባድ ድርጊት እንዳልሆነ ግን አምናለሁ። ከድርጊቱ የምረዳው ግን ፍላጎቱ አይደለም። ይህን በቃል እንዲነግረኝ አልጠብቅም። ይኸው ይኸንን ሁለት ቀናት እንኳን የአርሲ ሀገረ ስብከት ያወጣቸውን የድረሱን መግለጫዎች ሰሚ አለማግኘታቸውንና የሚመለከተው አካል ደግሞ ዝምታው ከላይ ያልኩትን ከማጽናት በላይ ናቸው፡፡
መግደሉና ማፈናቀሉ ብቻ ሳይሆን ይህ ዳተኝነቱ እና በድርጊቱ ላይ ፍትሕ በሚጠይቁት ላይ የሚሰጠው ምላሽ ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ እንደሚያመጣ አምናለሁ። በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ አሁን የማናውቀው እውነት እንደሚገለጽም አምናለሁ። ይህንንም ደግሞ መናገር ይገባናል ብዬ አምናለሁ። የምንናገረውም ለማስፈራራት ሳይሆን ሁሉም ሰው ንስሐ እንዲገባና ወደ ልቡናው እንዲመለስ ብቻ ነው። ካልሆነም ጥፋቱ የአንድ ወገን ሆኖ እንደማይቀር በእግዚአብሔር ፍርድ ላይ ካለኝ እምነት በመነሣት አሁን ደግሜ አማጽናለሁ።
በመጨረሻም ለእኛ ለከርስቲያኖች አሁንም እግዚአብሔርን እንለምን እላለሁ። እግዚአብሔር አምላክ የሁላችንም ኃጢአት ይቅር ብሎ በመከራ እና በሰቀቀን ላሉት ወገኖቻችን በሰላም ወጠተው የሚገቡበትን እና ከሰቀቀን ተላቅቀው ዕረፍትን የሚያገኙበትን ቀን እንዲያመጣልን መለመን አለብን። ለገዳዮች እና ለጽንፈኞችም እግዚአብሔር አምላክ እርሱን የሚያውቁበትን ልቡና ሰጥቷቸው ለሚያሳድዱት እምነት ምስክርነት ሲሰጡ ለማየት እንዲያበቃን ከልብ መጸለይ እና መለመን አለብን። የቅዱስ እስጢፋኖስ ጸሎት ሳውልን መልሶ ክርስቲያን አድርጎ ጳውሎስ አሰኝቶ መልሶ ለሐዋርያነት አበቃው ብለን እየሰበክን፣ የእነርሱ ልጆች ነን ብለንም እየተናገርን እረ እንዲያውም እየተመካንም ይህንን በጸሎታችን አለማድረግ በክርስትናው መሳለቅ ብቻ ሳይሆን ከክርስቶስም ጋር ጠላጥነታችን እያበዛን እና ለዋናው ጠላት ለዲያብሎስ በር እየከፈትን ከመሔድ ያለፈ ተግባር የለውም። ሰለዚህ እንደባለ አእምሮ እያሰብን ከስድብ እና ከርግማን ወደ ጸሎት እና ክርስቲያናዊ ተግባር ለመመለስ ያብቃን።
በሰማዕታቱ ደም ይቅር ይበለን፣ አሜን።
©ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:
Post a Comment