Monday, October 26, 2026

በአርሲ የተፈጸመው ጥቃት ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ካላት ጥቅም ጋር የተገናኛ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ገለጸ

 ሰኞ ፤ጥቅምት 16 ቀን 2019ዓ.ም (#አዲስ ማለዳ)May be an image of fire

በአርሲ የተፈጸመው ጥቃት ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ያላትን ብሔራዊ ጥቅም እንዳታስጠብቅ፤ በሰሜን የደረሰበትን ኪሳራ አቅጣጫ ለማስቀየር የተደረገ በውጭ ኃይሎች የሚደገፍ “በጽምዶ” የተፈጸመ ነው ሲል የኦሮሚያ ክልል አስታወቀ

በዚህ ጥቃት ባለፈው ቅዳሜ 43 የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች እንደተገደሉ ሀገር ስብከቱ ሲሳውቅ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን 46 መድረሳቸውን ገልጾ 39ኙ በጅምላ እንደተቀበሩ ገልጿል።

የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ በትናንትናው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ግድያውን ከቀይባህር እና በሰሜን ኢትዮጵያ ከተከሰተው ሁኔታ ጋር አያይዘው የኃይማኖት ግጭት ለመፍጠር የተደረገው መኩራ እንዳልተሳካ እና እንደከሸፈ ተናግረዋል። በተለያዩ ጊዜያት በክልሉ ጥቃቶች ከተፈፀሙ በኋላ “ማን ፈጸመው” ለሚለው ምላሽ የሚሰጠው ክልሉ፣ ሽብርተኞች እንዲሁም የኃይማኖት ግጭት ለማስነሳት የሚፈልጉ ኃይሎች እንደሆኑ ይገልጻል።

ጥቃት የፈጸመው ደግሞ “ጽምዶ” ሲሉ የጠሩት እና የኢትዮጵያን አንድነት በማይፈልጉ ኃይሎች መሆኑን ጠቁመዋል። ምንም እንኳ ይህ ጥቃት ትብብር ፈጠርን ካሉ ኃይሎች በኋላ የተከሰተ ቢሆንም መሰል ጥቃቶች ግን በተደጋጋሚ ሲፈጸሙ እና በርካቶች ንብረት እና ህይወታቸውን ሲያጡ እንደነበር ይታወሳል።


ኢትዮጵያ ታሪካዊ አንድነቷን እና ሉዓላዊነቷን እንዲሁም ህብረ ብሔራዊነት አስጠብቃ በቀይ ባህር  ላይ ብሔራዊ ጥቅሟን አስከብራ፣ በምስራቅ አፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር እንዳትሆን “ታሪካዊ ጠላቶች” ውስጣዊ አጀንዳዎችን በማቀናጀት የተለያዩ ድርጊቶችን እየፈጸሙ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ ይህም በእነሱ አስተባባሪነት የተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ኃላፊው “ባለፈው ዓመት” በማለት አስታውሰው፣ በሽብርተኞች ተላላኪነት አማካኝነት የሀገርን አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና የህዝቦችን አብሮነት ለመሸርሸር “አፍራሽ ኃይሎች” አደረጃጀት ፈጥረው ሲንቀሳቀሱ የነበረ ቢሆንም፣ መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ “የሀገርን አንድነት ለመጠበቅ” በወሰደባቸው  እርምጃ ሲመክንባቸው አርሲ ላይ ንጹኃንን እንደገደሉ ተናግረዋል።

አክለውም፤ የሀገርን አንድነት የማስጠበቅ እርምጃዎችን መቋቋም የተሳናቸው እነዚህ “የጥፋት ቡድን አባላት” ትኩረትን ለመሳብ ሲሉ በኦሮሚያ  የሚንቀሳቀሰውን “ሸኔ” የሽብር ቡድን በመጠቀም በንጹኃን ላይ ያነጣጠሩ የሽብር ተግባራትን እንዲፈጸም አድርገዋል ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል፤ ደቡብ ምስራቅ ዞን፣ በሲርካ ወረዳ በብር ጮሌ ቀበሌ በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ “የሽብር ድርጊት” የሚሉት ኃይሉ “በአሰቃቂ ሁኔታ” ህይወታቸው ያለፈ ዜጎች መኖራቸው እንዲሁም በንብረት ላይ ውድመት መድረሱን ተናግረዋል።  ይሁን እንጂ የሟቾች አሐዝን በተመለከተ ያሉት ነገር የለም፡፡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የጸጥታ አካላት በዚህ የሽብር ቡድን ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉ ብለዋል።

ኃይሉ ከዚህ ቀደም ግንቦት ወር ላይ ተመሳሳይ ጥቃት በተፈጸመበት ወቅት በሰጡት መግለጫ፤ “የሽብርተኛ ኃይሎች ድርጊት” ነው ብለው የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ “ሽብርተኛ ቡድን”  ሲሉ ጠርተው ሀገራዊ አንድነትን ለመሸርሸር ሲል አንዴ የኃይማኖት፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ የብሔር ካባ በመልበስ ህዝብን እርስ በእርስ ለመጋጨት ጥረት እያደረገ ይገኛል በማለት ወንጅለዋል።

ኃይሉ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመቆም ጥቆማዎችን በመስጠት ለታለመላቸው የጸጥታ እርምጃዎች ከፍተኛ  አስተዋፅኦ እንዳለውም አንስተዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች እና ሀገረ ስብክቱ ደግሞ ይህ ከመፈሙ በፊት የድረሱልን ጥሪ አቅርቦ እንደነበር ተዘግቧል።

ክልሉ በተፈጠረው ድርጊት እንዳዘነ ገልጸው፤ “በሽብር ቡድኑ” ላይ የክልሉ የጸጥታ አካላት ጥብቅ እርምጃዎችን መውሰድ እንቀጥላለን የሚሉት ኃይሉ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች መልሶ የማቋቋምና የማደራጀት ሥራዎች እንደሚሰሩ ጠቁመዋል። 

እንደ ቤተክርስቲያኗ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ከሆነ፤ ከሟቾች በተጨማሪ ከ20 በላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች፣ ከ20 በላይ መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን እንዲሁም አብያተ ክርስቲያን መዘረፋቸው ተመላክቷል፡፡

ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦

ምንጭ፡ አዲስ ማለዳ

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment