ቅዳሜ ፤ጥቅምት 14 ቀን 2019ዓ.ም (#አዲስ ማለዳ)
በጉራጌ ዞን የሚፈጸመው እገታና ግድያ ሲቀጥል፣ በተጠናቀቀው ሳምንት አበሸጌ ወረዳ ውስጥ ከ20 በላይ ሰዎች መታገታቸውን፤ እነዚህ ዜጎች ናቻ ከተማ ላይ መኪና በማስቆም እና ከመኖሪያ ሰፈራቸው ታግተው የተወሰዱ መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ ከሳምንት በፊት ዞኑ ላይ ባገረሸው እገታና ግድያ 5 ሰዎች ታግተው፣ ከነሱ መካከል አንድ የሀገር ሽማግሌ መገደላቸውንና ሕይወታቸው ማለፉን ከሟቹ የቅርብ ሰው አዲስ ማለዳ ማረጋገጥ ችላለች፡፡
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የሟች የቅርብ ሰው እንደገለጹት፤ ራሱን “ፋኖ” ብሎ ሰይሟል ባሉት አጋች አካል ባለፈው ሳምንት ዓርብ የሀገር ሽማግሌው ስብሰባ ላይ ውለው ወደ መኖሪያ ስፍራቸው ወደ አበሸጌ ወረዳ፣ ዳርጌ ከተማ ለመመለስ መንገድ ላይ ሳሉ፤ የሚመጡበት ሰዓትና የመኪና ታርጋ ተለይቶ ከወልቂጤ ከተማ 16 ኪሎ ሜትር ርቀት ካለው ስፍራ ላይ ቀን 10 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ተይዘው ጫካ ውስጥ ተገድለዋል፡፡
ከአራት ቀን በኋላም አስክሬናቸው ስፍራው ላይ ባለ የአካባቢው ህዝብና በዳርጌ ከተማ ነዋሪዎች ፍለጋ ተገኝቷል ብለዋል፡፡ አዲስ ማለዳ በገለልተኝነት በፋኖ ስለመፈጸም/አለመፈጸሙ ግን ማረጋገጥ አልቻለችም፡፡
በወረዳው የነበሩ ከፍተኛ አመራሮች አስክሬኑ ከመገኘቱ በፊት ሟቹ በሕይወት እንዳሉና በድርድር እንደሚለቀቁ ተነግሯቸው የነበረ ሲሆን፤ አመራሮቹ አጋቾቹን እስከማወቅ ደረጃ ደርሰው የነበረ ቢሆንም ከግድያው በኋላ በገዳዮች ላይ ምንም ዓይነት የህግ እርምጃ አለመወሰዱን ገልጸዋል፡፡ አክለውም የአስክሬን ፍለጋው ላይ የወረዳው ፖሊስ አለመሳተፉን ሲናገሩ፣ በወረዳው ያለ ሚሊሻ ብቻ መሳተፉን ጠቅሰዋል፡፡
ሌሎች ከሟቹ ግለሰብ ጋር ታግተው የነበሩ ሁለቱ 500 ሺሕ ብር ከፍለው ሲለቀቁ፣ ቀሪዎቹ ሁለቱ ገንዘብ የለንም በማለታቸው በነጻ መለቀቃቸውን አስረድተዋል፡፡
በጉራጌ ዞን ያሉ የመንግሥት አካላት እገታውንና ግድያውን ለማስቆም ጣልቃ ለመግባት ካለመፈለግ ባለፈ፣ እገታ የሚፈጽሙ አካላት ከተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮች ጋር በትብብር እንደሚሠሩ እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡ በዞኑ በተለያየ ወቅትና ቦታዎች እገታና ግድያ እንደሚፈጸም ሲናገሩ፣ አሁንም ሥጋቶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
ሌላኛው አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ነገር ግን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በጉራጌ ዞን የሚገኙ ነዋሪ፤ ጥቃቱን የሚፈጸሙት አካላት ጫካ ውስጥ ያሉ ህገወጥ ታጣቂዎች እንደሆኑና ብሔርን መሰረት ያደረገ ጥቃት እንደሚፈጽሙ ተናግረዋል፡፡
መንግሥት እርምጃ ቢወስድም ታጣቂዎቹ በበቆሎ ማሳ ውስጥ በመደበቅ እገታና ግድያ የሚፈጽሙ መሆናቸው መንግሥት ችግሩን እንዳይፈታ አድርጎታል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ አክለውም ጥቃቶቹ በአብዛኛው የሚፈጸሙት አበሸጌ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ በዋልጋና ዳርጌ ከተማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ ለአዲስ ማለዳ መረጃ የሰጡ ሌላ የጉራጌ ዞን ተወላጅ፤ በሶዶ ክስታኔ፣ በሶዶ ወረዳ ዙሪያና በጉራጌ ዞን አበሸጌ ወረዳ ላይ ሥጋት ያለባቸው አካባቢዎች ናቸው ብለዋል፡፡
መንግሥት በስም መጥቀስ የማይፈልጋቸው ታጣቂዎች “ሌሎች ኃይሎች ናቸው” የሚላቸው አካላት የንጹኀጃን ዜጎች ሞትና እገታ ይፈጽማሉ ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ አበሸጌ ወረዳን ጨምሮ በዙሪያው ያሉ አጎራባች የኦሮሚያ ዞኖች የሚያካትት ኮማንድ ፖስት ቢዋቀርና መተዳደር ከጀመረ ቢቆይም፣ የሚፈጸመውን እገታና ግድያ ማስቆም አልቻለም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በጉራጌ ዞን ያለውን ችግር የመፍታት የሰላም ውይይቶች በወረዳና በዞን ቢደረጉም ዘላቂ መፍትሔ መምጣት አልቻለም ብለዋል፡፡
“እገታና የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዲቆሙ ፍላጎትና ቁርጠኝነት አለ ወይ የሚለው ትልቅ ጥያቄ ነው” ያሉት የጉራጌ ዞን ነዋሪ፤ መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
አዲስ ማለዳ በአካባቢው የሚገኙትን የመንግሥት መዋቅር በዞኑ ያለውን እገታና ግድያ ለማስቆም ምን እያደረገ ነው ስትል የሚመለከታቸውን አካላት ለማነጋገር ሞክራለች። የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳደር መብራቱ ወልደማርያምን ለማግኘት ለሁለት ቀናት ጥረት ብታደርግም አንድ ጊዜ ስብሰባ ላይ ነኝ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ምላሽ ባለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልቻለችም፡፡
እንዲሁም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ተመስገን ካሳን አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ በአጭር የጽሁፍ መልዕክትም በሥልክም ለማግኘት ጥረት ብታደርግም ሊሳካላት አልቻለችም፡፡ ኃላፊዎቹ ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ በሆኑበት አፍታ አዲስ ማለዳ ታስተናግዳለች፡፡
አዲስ ማለዳ የተመለከተችው “የጉራጌ ዞን የጸጥታ ተቋማት የ2018 በጀት ዓመት ማጠቃለያ ሪፖርት” እንደሚያሳየው፤ አበሸጌ ላይ በዓመቱ “ጽንፈኛው ቡድን” ሲል በጠራው አካል፤ 46 ወንዶችና 12 ሴቶች በድምሩ 58 ሰዎች የታገቱ ሲሆን፣ ሁለት ወንዶችና አንድ ሴት መቁሰላቸው ተገልጿል፤ በድምር 23 ሰዎች መገደላቸውም ተመላክቷል፡፡
ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦
ምንጭ፡ አዲስ ማለዳ
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment