![]() |
| መ/ር ጳውሎስ መልአከ ሥላሴ |
(መ/ር ጳውሎስ መልክአ ሥላሴ/ PDF):- በቀድሞ ዘመን ማዶ ለማዶ በመንደር ተለያይተው በቅርብ ርቀት ላይ የሚኖሩ የኅብረተሰብ
ክፍሎች እንደነበሩ ይነገራል፡፡ እነዚህ ህዝቦች ታዲያ ባልታወቀ ምክንያት ቅሬታ ፈጥረው በሆነው ባልሆነው ምክንያት እስከ መካሰስ ደርሰው ነበር፡፡ ልዩነታቸውም እየሰፋ ሲመጣ አንዱ ለሌላው መጥፎ ስም መስጠት ጀመረ፡፡ ከአሉባልታዎቹም መካከል፡- የታችኛው መንደር የላይኛዎቹን፤ “እዚያ ማዶ ያሉት ቡዳ ናቸው” ሲሉ፡- በላይኛው መንደር ያሉትም በተራቸው፤ “ታች መንደር ያሉት ቡዳ ናቸው” እየተባባሉ እርስ
በርሳቸው ይተማሙ ነበር፡፡ በሌላ መንደር የሚኖረው ሕዝብም ሁለቱን በቡዳነት ፈርጆ የሚቀርባቸው እስኪያጡ ድረስ ራሳቸው ባመጡት ጣጣ ገለልተኞች ሆነው ብዙ ዘመን ኖሩ፡፡
ከቀኖች
በአንደኛው ቀን ከታችኛው መንደር አንድ የመሸበት መንገደኛ ወላጆቹ “ቡዳ” እንደሆኑ ከነገሩበት ላይኛው መንደር ደረሰ፤ እንዳይገባ ፈራ፤ አልፎ ከሄደ ደግሞ መሽቷልና የጅብ እራት ሊሆን ነው፡፡ ስለዚህም ጥቂት ካመነታ በኋላ፣ “ጅብ ከሚበላኝ ቡዳ ቢበላኝ አይሻልምን? ቡዳውንስ በጸበል እድናለሁ፤ ጅብ ከበላኝ መሞቴም አይደል? ደግሞስ ቡዳ ይሁኑ፣ አይሁኑ፣ ሰማሁ እንጂ የበሉት የለ? እንዲያውም በዚሁ አጋጣሚ ጉዱን ልወቅ” በማለት አማራጭ ያጣለትን ማደር እውነቱን ማረጋገጫ አድርጎ ሊጠቀምበት በማሰብ ፍርሃቱን አስወግዶ ወደ መንደሩ ገባ ይልና፤ “የእግዚአብሔር እንግዳ፣ የመሸበት መንገደኛ ነኝ፤ አሳድሩኝ” ይላል፡፡ በተሰጣቸው መጥፎ ስም ምክንያት እንግዳ የናፈቁት የመንደሩ ሰዎች እጅግ ደስ ብሏቸው ልብን በሚነካ ሁኔታ ተቀብለው፣ እግሩን አጥበው፣ ጥሩ እራት አዘጋጅተው በክብር አስተናገዱት፡፡ በመስተንግዷቸው ውስጡ በጣም የተነካው እንግዳም ለጊዜውም ቢሆን “ቡዳ ናቸው” የሚለውን ነገር ዘንግቶ ነበር፡፡







