· ወጣቶቹ ሊቃነ ጳጳሳት እንዲህ መስመር የሣተ አቋም የያዙበት ምክንያት ምንድር ነው? አረጋውያኑን በማስፈራራትም፣ በመናቅም የሚገፉት እስከመቼ ነው?
· አሜሪካ ለዕርቅ የተጓዘው ልዑክ ሪፖረቱን ነገ ማክሰኞ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፤
(ደጀ ሰላም ታኅሣሥ 22/2005 ዓ.ም፤ ዲሴምበር 31/2012/ PDF)፦ ከመንግሥት ጋር ቃል እንደተገባቡ የሚነገርላቸው ጥቂት ሊቃነ ጳጳሳት “ቤተ ከህነቱን ተቆጣጥረናል፣ ከመንገዳችን የሚገታን አይኖርም” ሲሉ እየተሰሙ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸው ከ10 የማያንስ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የፕትርያርክ መሾሙን እሽቅድምድም እንደማይስማሙበት በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ መንግሥትም በበኩሉ የሰላምና የዕርቅ ኮሚቴውን ልዑክ በሚሳዝን ሁኔታ ከሀገር በማባረር በግልጽና በአደባባይ ለዕርቁ እንቅፋት መሆኑን በድርጊቱ አረጋግጧል፡፡ በአንድ በኩል የሃይማኖት ነጻነትን እየሰበኩ በሌላ በኩል ልዑካንን ማሰር ማንገላታት ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሰሜን አሜሪካ ቆይተው የተመለሱት ልዑካን ሪፖርታቸውን ለማቅረብ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል፡፡ በሰላሙ ጉዳይ እነርሱ በሌሉበት ስለተፈፀመው የአስመራጭ ኮሚቴ ምርጫ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ እና ድርጊቱንም አጥብቀው እንደሚወግዙ እየተናገሩ ነው፡፡ እነዚህ አባቶች ሪፓርታቸውን ሲያቀርቡ የአስመራጭ ኮሚቴ ጉዳይ እኛ ባለንበት እንደገና ይታይ የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡ መልሱ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውም ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡ ጥያቄው የሦስቱ ሊቃነ ጳጳሳት /አቡነ አትናቴዎስ፣ አቡነ ገሪማ፣ አቡነ ቀውስጦስ/ ብቻም አለመሆኑ ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ ያከብደዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ፣ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ እና ሌሎችም ለጊዜው ስማቸውን ያልዘረዘርናቸው አባቶች አለመስማማታቸውም እያሰሙ የሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳት ናቸው፡፡
ከአሥር የማያንሱ እነዚህ አባቶችን ጥያቄ ሳይመለስ ቅዱስ ሲኖዶስ ምርጫውን ከቀጠለ አባቶች ጉዳዩን በአደባባይ ማውገዝ እንደሚጀምሩም ይጠበቃል፡፡ በመንፈሳዊነት እና በቤተ ክርስቲያን እውቀት የበለጸጉ እነዚህ አባቶች የቁርጥ ቀን አርበኞች ሆነው ከተገኙ ዳር ደረሰ የተባለውን የምርጫ ጉዳይ መፍትሔ ሊሰጡት ይችላሉ፡፡ ምን አልባትም ለጊዜው ተደልለውም ከመንግሥት ሰዎች በኩል እየመጣባቸው ያለውን ጫና መቋቋም ተስኗቸው ተመሳስለው የምናያቸው ሌሎች የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትም ትክክለኛ አቋም ሊይዙ ይችላሉ። በወጣቶቹ ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራውና እና መንግሥታዊ ድጋፍ እንዳለው የሚነገርለት ቡድን አረጋውያኑን አባቶች ለማስፈራራት ወይም ለማታለል የቻለውን ያህል ጥረት ያደርግ ይሆናል፡፡ ለሁሉም ሪፖርቱን አስከትሎ የሚከሰቱ ጉዳዮችን በየጊዜው ለመዘገብ እንሞክራለን፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፣ አሜን።
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment