በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ቅድሚያ ለእርቀ ሰላም!
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
አዲስ አበባ
የተከበራችሁ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አባቶቻችን፣ በቅድሚያ ቡራኬያችሁ ይድረሰን። ቤተ ክርስቲያናችን ለሁለት አሥርት ዓመታት በፈተና ውስጥ እንድትቆይ ያደረገውን የልዩነት ግድግዳ አፍርሶ አንድ ሲኖዶስ፣ አንድ ፓትርያርክ፣ አንድ አስተዳደር እንዲኖራት ለማድረግ የተጀመረውን የእርቀ ሰላም ዓላማ በመደገፍ ልዑካንን በመሰየም የጀመራችሁት ሂደት አስደስቶናል። ነገር ግን የእርቀ ሰላሙ ሂደት ሳይጠናቀቅ ወደ ፓትርያርክ ምርጫ ጉዞ መጀመሩ በእጅጉ እንድናዝን አድርጎናል።
እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት በሰንበት ት/ቤት ውስጥ የምንገኝ ወጣቶች አብዛኛው ዘመናችንን ያሳለፍነው ቤተክርስቲያናችን
በሁለት ሲኖዶስ ተከፍላ የልዩነት፣ የውግዘት እና የመራራቅ ባዕድ ሥርዓቶችን ስናስተናግድ ነው። ይህም በሰንበት ት/ቤት ተሳትፎ ለቤተክርስቲያናችን የሚገባውን አገልግሎት እንዳንሰጥ ትልቅ መሰናክል ሆኖ ቆይቷል። ቢሆንም ጊዜው ደርሶ የተጀመረው የእርቀ ሰላም ሂደት ትልቅ ተስፋ ሰጥቶን ነበር። ነገር ግን በተቃራኒው እየተከናወነ ያለው የፓትርያርክ ምርጫ ጉዞ የተቀረ ዘመናችንን በተስፋ እና በበለጠ መነሳሳት እንዳንጓዝ እያደረገን ይገኛል።
በተለይም እኛ በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የምንገኘው የቤተክርስቲያን ልዩነት በእጅጉ ገዝፎ በሚታይበት አኅጉር በመሆኑ የእርቀ ሰላሙ ሂደት መደናቀፍ የቤተክርስቲያናችንን ችግር ወደ ባሰ አዘቅት ውስጥ እንደሚጨምረው ለመገመት አያዳግተንም። በእርቀ ሰላም ጉባኤያቱ ምክንያትም የተጀመረውን ወደ አንድነት የመምጣቱን የተስፋ ጭላንጭልን አክስሞ ለሚቀጥሉት የማይታወቁ አያሌ ዘመናት የምእመናንን አንገት የሚያስደፉ ሁኔታዎችን ሊፈጥር እንደሚችልም ግልጽ ነው።
የቤተ ክርስቲያን አንድነት ወደ ተሻለ የአገልግሎት ምዕራፍ አሸጋግሮን በልዩነት ምክንያት ያልተነኩ ዘርፈ ብዙ ተልዕኮዎችን ለመፈጸም እየተሰናዳን ባለንበት ወቅት ከእኛ አልፎ ለልጆቻችን የምናወርሰው የመከፋፈል እና የመለያየት ሥርዓትን በድጋሚ የምናስተናግድበት አቅም ለማግኘትም እንቸገራለን።
ስለዚህ ፍጹም በሆነ የልጅነት መንፈስ የሚከተለውን መልእክት ለማስተላለፍ እንወዳለን፦
1) የተጀመረው የእርቀ ሰላም ሂደት ሳይጠናቀቅ ወደ ፓትርያርክ ምርጫ ጉዞ በመጀመሩ በእጅጉ አዝነናል።
የቀጣይ የአገልግሎት ዘመናችንንም በተስፋ እንዳንጓዝ እንቅፋት ሆኖብናል። ስለዚህ ለተተኪ ልጆቻችሁ ስትሉ የእርቀ ሰላሙ ሂደት እንዲጠናቀቅ እንድታደርጉ በቅድስት ቤተክርስቲያን ስም እንጠይቃለን።
2) እንደ ቀደሙት አባቶቻችን ለቤተክርስቲያን እና ለመንጋችሁ ስትሉ ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ከሆነ ተፅዕኖ በጸዳ ሁኔታ መክራችሁ የእርቀ ሰላሙን ሂደት ለውሳኔ እንድታበቁ እንማጸናለን።
3) የተፈጠረው የአስተዳደር ልዩነት ተወግዶ ቤተ ክርስቲያንን ወደ አንድነት ሊያመጣ የሚችል ጥንቃቄ የተሞላበት የመፍትሄ ውሳኔ እንድትወስኑም አደራ እንላለን።
አምላካችን እግዚአብሔር የተፈጠረውን መለያየት አስወግዶ እና የቤተ ክርስቲያን አንድነትን ወደ ቀድሞ ቦታው መልሶ በአንድነት እንድናመሰግነው ያበቃን ዘንድ መልካም ፈቃዱ ይሁንልን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር።
ህዳር 13/2005 ዓ. ም
በሰሜን አሜሪካ አኅጉረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ
ሰሜን አሜሪካ
ግልባጭ:
ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት
ለሰሜን አሜሪካ አኅጉረ ስብከት
ለሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት በያሉበት ፣
ለኢትዮጵያ የሰንበት ት/ቤቶች ኅብረት ፣
ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች ኅብረት ፣
በካናዳ፣ በአፍሪካና አና በአውሮፓ ለሚገኙ ሰንበት ት/ቤቶች ፣
ለሰላም እና አንድነት ጉባኤ፣
ለመገናኛ ብዙኃን በሙሉ።
ሙሉውን ቃል ለማንበብ እዚህ ይጫኑ
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment