Wednesday, December 5, 2012

የኢ/ኦ/ተ ቤተ ክርስቲያን አባቶች የእርቀ ሰላም ውይይት ዛሬ ይጀመራል



  • ከኢትዮጵያ የመጣው ልዑክ ዳላስ የገቡት ትናንት ኅዳር 26/ ዲሴምበር 4 ነው።

ሁለቱም ታራቂ አባቶች ከውይይታቸው በፊት በጋራ ተቀምጠው
 
(ደጀ ሰላም ኅዳር 26/2005 ዓ.ም፤ ዲሴምበር 5/2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ለመፍታት የሚደረገው ሦስተኛ ዙርየዕርቅ ድርድር ዛሬ በሰሜን አሜሪካ ዳላስ ቴክሳስ ከተማ ይጀመራል:: ከዛሬ ኅዳር 26 እስከ 30(ዲሴምበር 5-9/2012) የሚካሄደው ስብሰባ ውጤታማ እንዲሆን በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ምኞታቸውን እየገለጡ ሲሆን በውጪው ዓለም የሚገኙ ካህናት፣ ምዕመናን እና መንፈሳውያን ማኅበራት በሁለቱም በኩል ላሉት አባቶች ችግሩ እልባት እንዲያገኝ የተማጽኖ ፊርማ እያሰባሰቡ መሆኑን መዘገባችን ይታወል::



በአባቶች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ለመፍታት ከሁለት ዓመታት በላይ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ የነበረው የሰላምና አንድነት ጉባኤ እያከናወነ ያለው ታሪካዊ ሥራ የሚያስመሰግነው ሲሆን የዕርቁ ሂደት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ በወቅቱ የጉዳዩ ባለቤት ለሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መዕመናን ማሳወቅ እንዳለበት አስተያየት እየተሰጠ ይገኛል::

ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ረፍ በኋላ የመጀመሪያው የሆነው የእርቅ ድርድር ብዙኃኑ ዝበ ክርስቲያን ተስፋ የጣለበትና የ21 ዓመታት ልዩነት መቋጫ ይበጅለታል ብሎ የሚጠብቀው ሲሆን በኢትዮጵያው አባቶች በኩል 6ኛውን ፓትርያርክ ለመምረጥ እያደረጉ ያለው እንቅስቃሴና ውጪውየሚገኙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርርዮስ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ወደመንበራቸው ይመለሱ የሚለው ጠንካራ አቋም ሕዝበ ክርስቲያኑ እየጠበቀው ያለውን አንድነት እንዳያደናቅፈው ስጋት ፈጥሯል::

ድርድሩን ለማካሄድ ኢትዮጵያ የተወከሉት ብፁዕ አቡነ ገሪማ የልዑካኑ መሪ፣ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ አባል፣ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ አባል ሁነው በዳላስ ቴክሳስ የተገኙ ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ያልወከላቸውና የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ከተጠናቀቀ በኋላ በስርዎጽ ከልዑካኑ ጋር አብረው እንዲጓዙ የተደረጉት ንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃ በጸሐፊነት እንደተገኙ ታውቋል::

የውጪውን በመወከል ለድርድር የተገኙት ልዑካን ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የልዑካኑ መሪ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ አባል፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ አባል ሆነው ተገኝተዋል ሦስቱም ቀደምትነት ካላቸው ሊቃነ ጳጳሳት መካከል መሆናቸውንና ከሁለት ዓመታት በፊት በሞት የተለዩትን ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስን ጨምሮ አራተኛውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርርዮስን በመያዝ “ሕጋዊ ሲኖዶስ በሚል ያቋቋሙ መሆናቸው ይታወቃል:: ምንም እንኳን ድርድሩ በሊቃነ ጳጳሳት ደረጃ ይደረጋል ተብሎ ቢጠበቅም በኢትዮጵያ ሲኖዶስ የንቡረ ድ ኤልያስን በልዑክነት መጨመር ተከትሎ ሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ የውጪውን ሲኖዶስ በመወከል በጸሐፊነት ሊሳተፉ በድርድር ቦታው መገኘታቸው ታውቋል::
  
በኢትዮጵያም ሆነ በውጪ ያሉትን አባቶች ለማቀራረብ በሁለቱም በኩል እውቅና እንደተሰጠው የሚነገርለትና አደራዳሪ ሁነው የሚቀርቡት  የሰላምና አንድነት ጉባኤ አባላት ከተለያዩ አስተዳደራዊ ክፍሎች የተገኙ መሆናቸውን ዝርዝራቸው ያመለክታል።

በኢትዮጵያ ጠ/ቤተ ክህነት ሚተዳደሩ አብያተ ክርስቲያናት መላከ መንክራት ቀሲስ አንዱዓለም ይርዳው በአስታራቂ ጉባዔው ሰብሳቢነት፣ ሊቀካህናት ኃይለሥላሴ ዓለማየሁ እና መጋቤ ሃይማኖት ቀሲስ ፋሲል አስረስ  አባልነት በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ ውጪው በሚገኙት አባቶችሚተዳደሩ አብያተ ክርስቲያናት የመጡት ደግሞ ቆሞስ አባ ጽጌ ደገፋው፣ መ/ር ልዑለቃል አካሉዲ/ን አንዱዓለም ዳግማዊ በኮሚቴው አባልነት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። በተለምዶ “ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት” ከሚባሉት ደግሞ ሊቀ ማዕምራን ዶ/ር አማረ ካሳየና ቀሲስ መኮነን ኃይለጊዮርጊስበኮሚቴው አባልነት የሚገኙ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል
  
ታሪካዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  የኢትዮጵያ ሲኖዶስ፣ ስደተኛ ሲኖዶስ እና ገለልተኛ በመባል መከፋፈሏ ተወግዶ የቀደመ ጥንካሬዋን ለማስመለስ ሰዓቱ እንዳልመሸ አስተያየት ሰጭዎች ይናገራሉ አሁን ባለችበት ሁኔታ የምትቀጥል ከሆነ ግን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ አጠያያቂ አይደለም:: በዚህ የድርድር ስብሰባ በሁለቱም በኩል ያሉ አባቶች በእግዚአብሔርም በታሪክም ተጠያቂ ላለመሆን ቤተ ክርስቲያንን ብቻ ማዕከል ባደረገ ሁኔታ ተወያይተው መፍትሄ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል:: ደጀ ሰላምም የዚህን ታላቅ ጉባዔ ሒደት፣ ውይይቱን በማያደናቅፍ መልኩ እየተከታተለች ለማቅረብ ትሞክራለች።

ከኢትዮጵያ የመጣው ልዑክ ዳላስ የገቡት ትናንት ኅዳር 26/ ዲሴምበር 4 ነው።
    
“ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተ ክርስቲያን - ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላም ጸልዩ”።

ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

1 comment:

  1. ዲያቆን አንዱዓለም ዳግማዊ ከዳላሱ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያ ስለሆነ "ከገለልተኛ" ቤተክርስቲያን ተብሎ ቢስተካከል የሚል ሓሳብ አለኝ። ጅማሬውን በሕብረትና በአንድነት ሲቀመጡ ያሳየን አምላክ ፍጻሜውንም ያሳምረው እላለሁ።

    ReplyDelete