Friday, December 21, 2012

የቅ/ሲኖዶሱ አባላት በውሳኔያቸው ተከፋፍለዋል


  • የዕርቀ ሰላሙ ልኡካን በሲኖዶሱ ውሳኔ ላይ የወሰዱት አቋም በመንሥኤነት ተጠቅሷል
  • ‹‹ይኾናል ብለን አንጠብቅም፤ ኾኖ ከተገኘ በጣም እንቃወማለን›› /አቡነ አትናቴዎስ/
  • ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ከሲኖዶሱ ስብሰባና ውሳኔዎች ራሳቸውን አግልለዋል
  • ዋና ጸሐፊው ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ፈቃደኛ አልኾኑም
  • ማኅበረ ቅዱሳን በዕርቀ ሰላሙ እና በፓትርያሪክ ምርጫ አጣባቂኝ ውስጥ ገብቷል
የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ትላንት፣ ታኅሣሥ 10 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀትር በኋላ የፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንብ አጽድቆ ምርጫውን የሚያስፈጽም 13 አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ ሠይሟል፡፡ የኮሚቴው አባላት ከቅ/ሲኖዶስ አባላት፣ ከመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ መምሪያ ሓላፊዎች፣ ከገዳማት አበምኔቶች፣ ከሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፣ ከመንፈሳውያን ማኅበራት እና ከታዋቂ ምእመናን ‹‹የተውጣጡ ናቸው›› ተብሏል፡፡
የኮሚቴውን መቋቋም ተከትሎ ለዕርቀ ሰላሙ ንግግሩ ወደ አሜሪካ የተላኩትና በቅ/ሲኖዶሱ የተሰጣቸውን ተጨማሪ የሰላም ተልእኮ ለመፈጸም በዚያው ከሚገኙት ሦስት ብፁዓን አባቶች መካከል ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ÷ ትላንት ሌሊቱን ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ እና ከቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ጋራ በስልክ ተነጋግረዋል፡፡ በጥቅምት ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት በደብዳቤ መላካቸውንና በዳላሱ የሰላም ጉባኤ በወጣው የጋራ መግለጫ መሠረት ዕርቀ ሰላሙን ከሚያደናቅፉ ተግባራት ለመቆጠብ ተስማምተው መፈረማቸውን ያስታወሱት ብፁዕነታቸው÷ ቅ/ሲኖዶሱ የልኡኩን ሪፖርት ሳያዳምጥና የሎሳንጀለሱን የሰላም ጉባኤ ውጤት ሳይጠብቅ አስመራጭ ኮሚቴ መሠየሙን እንደማይቀበሉት ማስታወቃቸው ተዘግቧል፡፡
ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ እና ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ
ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ እና ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ


‹‹ወደ አገራችን ተመልሰን ሰላም ለጠማው ሕዝብ መግለጫ እንሰጣለን፤›› ያሉት ብፁዕነታቸው÷ ውሳኔው የማይታረም ከኾነ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ከሚያውክና ለሰላሟ ከማይጨነቅ ስብስብ ጋራ እንደማይቀጥሉ ለዐቃቤ መንበሩ አስጠንቅቀዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ ይህንኑ አቋማቸውን ዛሬ፣ ታኅሣሥ 11 ቀን ማምሻውን በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ በተደመጠው ቃላቸው በይፋ አሰምተዋል፡፡ ትላንት ሌሊቱን ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ጋራ የተደረገው የብፁዕነታቸው ውይይት በመግባባት የተካሄደ ቢኾንም ከዋና ጸሐፊው ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ጋራ የተደረገው ግን ባለመግባባት መቋጨቱ ነው የተሰማው፡፡
ይኸው የዕርቀ ሰላም ልኡካኑ ፈጣን ማሳሰቢያ የፈጠረው ተጽዕኖ ይመስላል ለዛሬ ከሰዓት በኋላ በቅ/ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ እንዲሰጥ ተቀጥሮ  ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል
ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል
የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡ የዜናው ምንጮች እንደገለጹት÷ ብፁዕ ዋና ጸሐፊው ለጋዜጣዊ መግለጫው ለመቅረብ ፈቃደኛ አልኾኑም፡፡ ‹‹ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋራ መጣላት አልፈልግም›› ያሉት ብፁዕነታቸው÷ በጥቅምት ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጋዜጣዊ ጉባኤ ላይ ‹‹አምስት ብለን ስድስት እንጂ ወደ አራት አንመለስም›› የሚለው ንግግራቸው ያስከተለባቸው ትችት ሕዝባዊ ድጋፉ እየተጠናከረ የመጣውን የዕርቀ ሰላም ጉባኤ የሚያደናቅፈውን የሲኖዶሱን ውሳኔ የመግለጥ ድፍረት አሳጥቷቸዋል፡፡ ‹‹ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበር ይመለሱ የሚለውን እቃወማለኹ እንጂ ዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ እንዲሰጠው እፈልጋለኹ›› ያሉት ብፁዕነታቸው ጋዜጣዊ መግለጫውን እንዲሰጡ ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ዳግመኛ ቢታዘዙም ፈቃደኛ ሳይኾኑ መቅረታቸው ተገልጧል፡፡ የሲኖዶሱን ውሳኔ ለሚዲያ አካላት የመግለጽ ሓላፊነት በብፁዕ ዋና ጸሐፊው ላይ ብቻ ሳይኾን በራሳቸው በዐቃቤ መንበሩ ላይም መታየቱ ውሳኔው በውጫዊ ጫና ስለመተላለፉ ተጨባጭ ማስረጃ ተደርጎ ተወስዷል፡፡
‹‹የዕርቀ ሰላም ልኡኩን እንጠብቅ፤ ሪፖርቱን እንስማ›› የሚል የአቋም ልዩነት ቢኖራቸውም በአስመራጭ ኮሚቴው ውስጥ እንዲገቡ ከተደረጉት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ጋራ ተመሳሳይ አቋም የያዙት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ትላንት በፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንብ ማጽደቅና በአስመራጭ ኮሚቴ ማቋቋም እንዲሁም በዛሬው ስብሰባ ሳይገኙ ቀርተዋል፤ ፊርማቸውን አለማስፈራቸው ታውቋል፡፡ እንደ ስብሰባው ምንጮች መረጃ አቡነ ጎርጎሬዎስ ብፁዕነታቸውን አግባብተው ለማስፈረም ጥረት ቢያደርጉም ‹‹ብንታገሥ ምን አለበት›› የሚሉት ብፁዕነታቸው በአቋማቸው በመጽናታቸው የዘለፋ ቃል ደርሶባቸዋል፡፡
በሌላ በኩል በተቋማዊ መንገድ ያልወከለው የሥራ አመራር ጉባኤ አባሉ በአስመራጭ ኮሚቴ ውስጥ የተካተተው ማኅበረ ቅዱሳን በፓትርያሪክ ምርጫ ሂደቱ በመሳተፍና ዕርቀ ሰላሙን በማስቀደም መካከል አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ ተገልጧል፡፡ የቀጣዩ የዕርቀ ሰላም ጉባኤ ውጤት እስኪታወቅ አስመራጭ ኮሚቴው እንዳይቋቋም ዐቃቤ መንበሩንና ሌሎቹንም ብፁዓን አባቶች ለማግባባት በማኅበሩ አመራሮች በኩል ጥረት የተዘገበ ቢኾንም ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ‹‹ማኅበረ ቅዱሳንና አንዳንድ ጳጳሳት ከመንግሥት ጎን ኾነው ቤተ ክርስቲያኗን እየከፋፈሏት ነው›› በመንበረ ፓትርያሪኩ ዙሪያ ተበትኖ ማደሩ ተመልክቷል፡፡ በማኅበሩ በኩል በጉዳዩ ላይ የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ የለም፡፡
በደረሰን መረጃ መሠረት የኮሚቴው አባላት ስም ዝርዝር፡-
ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
1)  ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፣ 2) ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ 3) ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ 4) ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ናቸው፡፡
ከመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ሁለት መምሪያዎች፤
5) ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ – የሰበካ ጉባኤ መምሪያ ዋና ሓላፊ
6) መጋቤ ምስጢር ዓምደ ብርሃን – የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዋና ሓላፊ
ከታላላቅ ገዳማት እና አድባራት
7) ፀባቴ አባ ኀይለ መስቀል ውቤ – የደብረ ሊባኖስ ገዳም አበምኔት
8) ንቡረ እድ አባ ዕዝራ – የአኵስም ጽዮን ንቡረ እድ
ከአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት
9) ዲያቆን ኄኖክ ዐሥራት
ከማኅበረ ቅዱሳን
10) አቶ ባያብል ሙላቴ
ከታዋቂ ምእመናን
11) አቶ ዓለማየሁ ተስፋዬ – ከኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት
12) ቀኝ አዝማች ኀይሉ ቃለ ወልድ
13) አቶ ታቦር ገረሱ ናቸው፡፡

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment