ኦርቶዶክሳዊነት ወዴት ገባ? አቦ አቦ መባልን መሽሽ ወዴት ገባ? ራስን ከክብር ከስልጣን ማራቅ ወዴት ገባ? ኸረ ወዴት ገባ? ስለልጆቹስ የሚገደው አባት ወዴት ጠፋ? ስለምእመናን ምቾትስ እድሜህን ሁሉ በጉስቁልና የኖርክ ዮሐንስ አፈወርቅ ሆይ እስኪ ተናገርና እንስማህ? ስለእርቅ ምን ያክል ዋጋ ትከፍል ነበር? ስለምዕመናንስ አንድነት ምን ያክል ዋጋ ትከፍል ነበር? ስለክርስትናስ ክብር ምን ያክል ዋጋ ትከፍል ነበር? አባታችን ተናገረንና እስኪ እንጽናና ፤ በእኛ ቤት ግን ከእርቅ ይልቅ የሥልጣን ጥማቱ አይሏል ፥ ከምዕመናን አንድነት ይልቅ የራስን ሹመት ማዳበር አይሏል ፥ ከክርስትናው ክብር ይልቅ የቤተ መንግሥቱ ክብር በልጧል ፤ በእኛ ቤት እንዲህ ሆኗል ፤ ያ ሥልጣንን ስለአለመፈለግ ወደገዳም ሽሽቱ ኦርቶዶክሳዊው ትህትና ቀርቷል ፥ ሁሉም ራሱን ይመርጣል ፥ ሁሉም ምረጡኝ ይላል ፥ ሁሉም ድጋፍን ይሻል ፤
ጽኑ ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ አባታችን ሆይ ፦ እስኪ የክርስትናውን ዋና አላማ አስተምረን ፤ በመንግሥት እጅ ጥምዘዛ ክርስቶስ ይካዳል እንዴ? በክፉ የዲያቢሎስ ሽንገላ ክርስትና ይላላል እንዴ? ዓለማዊ ምቾትና ኦርቶዶክሳዊው መምህርነት በምን ይዛመዳሉ? አባታችን ሆይ ፦ የክርስቶስን መስቀል ይዞ ከእርቅ ሽሽቶ እንዴት ይሆናል? እረኛ ሆኖ ሳለ በጎች ሲበተኑ መተባበር ፥ በጎች ሲጠፉ አለመፈለግ እንዴት ይስማማል? ሰላማዊ ክርስቶስን እየሰበኩ ከሰላም መራቅ ምን ይባላል? ትሁት ክርስቶስን እየሰበኩ ራስን መሾም ምን ይባላል? አባታችን ፦ ተመሳስሎ ስለመኖርማ ከፋሽስት ክብር ቀርቦለወት አለነበረምን? ክርስቶስን ስለማክበር የእርስወን ክብር ሸሿት እንጂ ፤ ሥልጣንስ ቀርቦለወት አልነበረምን? መደለያ ቀርቦለወት አልነበረምን? በልብወ ያለው የክርስቶስ ፅናት ፡ የምዕመናን ፍቅር ግድ አለወት እንጂ ፤ አባታችን ፦ ዛሬ ግን ይህን አናይም ፤ ለእኛ ለምዕመናን አብነት ሊሆን የሚወድ ትሁት አባት ራቀብን ፤ ሹመት ሽልማትን ንቆ ለክርስትናው ዘብ የሚቆም እውነተኛ እረኛ ማየት አልቻልንም ፤ በቤተ መንግሥት መደለያ የማያጓጓው ፡ የቤተ መንግስት ቁጣ የማያስበረግገው ፅኑ አባት ማየት አልቻልንም፡፡
ታዳያ ዛሬ ወደማን እንጩኽ? ኸረ ማን ይበለን አምላካችን ምነው በግብጽ በረሃዎች ስለተንከራተቱት፣
በምድረ ኢትዮጵያ ከጨካኝ ሄሮድስ ሽሽት ስለተንከራተተችው ድንግል ማርያም፣ ቃል ስለ ገባህላቸው ስለ ደጋጎቹ አባቶቻችን፣ ምድሪቱን
በእጃቸው ክንድ ከፍ አድርገው ስላስባረኩት ቅዱስ አባት አባ ዛሙኤል ዘዋልድባ ብለህ እንዲሁም ለበጎ ነገር ስለሚጋደሉ፣ ስለ ስምህ
ፍቅር ብለው ድንጋይ ተንተርሰው፣ ጤዛ ልሰው፣ ግርማ ሌሊቱን ታግሰው፣ ከአራዊት ታግለው፣ ቅጠል በጥሰው እየቀመሱ በዱር በገደሉ
ስለሚንከራተቱት አባቶች እና እናቶች ብለህ ይህችን ቅድስት፣ ርትዕይት የሆነች ቤተክርስቲያን ለአውሬ አትተዋት፣ ለቀማኛ እና ለእሾም
ባይ አትተዋት፥ ስለ ስምህ ቁልቁል የተሰቀሉትን፣ አንገታቸው በካራ የተቀላውን፣ ቆዳቸው ተሸልቶ ስልቻ የተሰፋውን ደጋጎቹን ቅዱሳን
ሐዋሪያት አስታውስ ሌት ተቀን ስምህን የሚጠሩትን ቅዱሳን አስብ፣ . . . ኸረ የቤተ ክርስቲያን አምላክ ሆይ ዝም አትበለን፥ ተዓምራትክን
አሳየን በቤተክርስቲያን ላይ የተነሱትን እጆች፣ የክፉ መንፈስ መልዕክተኞችን ሁሉ ገስጽልን ምዕመናን በአንድነት እንዲመሩ ለአባቶቻችን
ሰላም ስጥልን በቁጣ አትቅሰፈን ሰላም . . . ለቤተክርስቲያን ሰላም . . . ለምዕመናን እንዲሆን እንጮኻለን ልመናችንን ጩኽታችንን
ስማን የሰራዊት አምላክ የድንግል ማርያም ልጅ . . .
“በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” ሐዋ.20:28
ወስብሃት ለእግዚአብሄር
ከታምራት ፍሠሃ FB የተገኘ
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment