Monday, March 9, 2026

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ በመምህር ዘለዓለም ወንድሙ ሕልፈተ ሕይወት የሐዘን መልዕክት አስተላለፉ።

የቅዱስ  ፓትርያርኩ ሙሉ መልእክት ነው። 

“መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ”
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን !!
‹‹ወነአምር ከመ ለእመሂ ተነሥተ ቤተ ማኅደርነ ዘበምድር ዘውእቱ ሥጋ ብነ ሕንጻ በኀበ እግዚአብሔር በሰማያት ዘኢገብሮ እደሰብእ፡-
በምድር ያለው ማደሪያ ቤታችን ቢፈርስም በሰማይ በእግዚአብሔር ዘንድ የሰው እጅ ያልሠራው ዘለዓለማዊ ቤት እንዳለን እናውቃለን፡፡›› (2ቆሮ. 5፡1)

በልዩ ልዩ ጊዜያት ዐረፍተ ዘመን የገታቸውን ወገኖች ልንሸኝ እንችላለን፤ የአንዳንድ ሰዎች ሞት ግን ከልብ ቶሎ የማይወጣ፤ ለዘመናትም በህሊና መዝገብ ላይ የሚቆይ ነው፡፡

በመሆኑም የሚከተሉት ሃይማኖት ወይም መርጠው ያልተወለዱበት አካባቢ እንደበደል ተቆጥሮባቸው ከየአቅጣጫው በሚሰነዘረው ጥቃት በሚገደሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች፣ ምእመናን በአጠቃላይ የሰው ልጆች ኀዘን ልባችን በትካዜ ውስጥ በሚገኝበት በዚህ ወቅት በመንፈሳዊ ሕይወቱ እና በትጋቱ ለቤተ ክርስቲያን ተስፋ የነበረው፤ ለበርካታ ዓመታትም በገጠር፣ በከተማ፣ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ እየተዘዋወረ ወንጌለ መንግሥትን ሲያስተምር የቆየው የመንፈስ ቅዱስ ልጃችን መ/ር ዘለዓለም ወንድሙ ለመንፈሳዊ አገልግሎት በተጓዘባት ሰሜን አሜሪካ ባጋጠመው ሕመም ከዚህ ዓለም ድካም በሥጋ ማረፉን ስንሰማ ታላቅ ድንጋጤ ፈጥሮብናል፡፡

በእርግጥ መምህር ዘለዓለም ወንድሙ ስመ ጥምቀቱ ወልደ ሰማእት በሥጋ ከእኛ ቢለይም ያለዋጋ የተቀበለውን የእግዚአብሔር ቃል ለምእመናን በማስተማር አደራውን በሚገባ ተወጥቶአልና በሰማይ ወደሚጠብቀው ዘለዓለማዊ ስፍራ በክብር እንደሚገባ እናምናለን፡፡
የመልካም ሰዎች መጉደል ለሀገር በተለይም ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን የነገ ዕጣ ፈንታ የሚያስጨንቅ ቢሆንም ሁሉን የሚችል አምላክ ተተኪዎችን እንዲያዘጋጅልን በመጸለይ፤ ለመንፈስ ቅዱስ ልጃችን ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶችና ምእመናን መጽናናትን እየተመኘን አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡ 

እግዚአብሔር አምላክ የአገልጋዩ ወልደ ሰማዕትን ነፍስ በመንግሥቱ ያሳርፍልን፤ 

“እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ”
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አሜን!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ 
ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣
የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment