Saturday, November 28, 2026

"ነቢይ ነን" በማለት የሰበሰቡትን በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከሀገር እንዳሸሹ በተጠረጠሩ ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ ሰፊ የወንጀል ምርመራ መጀመሩ ተሰማ

በኢትዮጵያ ብሎም በመላው የአፍሪካ አህጉር "ነቢይ ነን" እና "ተአምር አድራጊ ነን" የሚሉ ግለሰቦች በፍጥነት መበራከት  የሃይማኖታዊውንና የማኅበረ-ፖለቲካዊውን ምኅዳር በከፍተኛ ሁኔታ እየቀየረው ይገኛል። 

እነዚህ አካላት ፈጣን ብልጽግናንና መለኮታዊ ጣልቃ ገብነትን በመስበክ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮችን ወደ ራሳቸው መሳብ እንደቻሉ ይሰማል። ይሁን እንጂ ከሚታየው ግዙፍ የአገልግሎት ተቋማት ጀርባ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ አንዳንድ ግለሰቦች በመንፈሳዊ መሪነት፣ በፖለቲካዊ ጥገኝነት እና በግዙፍ የንግድ ኢንተርፕራይዝ መካከል ያለውን ድንበር እያደበዘዙት መጥተዋል። 

ከዚህ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ውስጥ "ነቢይ ነን" በሚል ሽፋን በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ላይ እጅግ ሰፊ ፋይሎችን የያዘ የሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር (Money Laundering) ምርመራ በይፋ መጀመሩን የመሠረት ሚዲያ ታማኝ ምንጮች አረጋግጠዋል። 

በዚህ ከፍተኛ የወንጀል ምርመራ መዝገብ ውስጥ ስማቸው በግንባር ቀደምትነት ከተጠቀሱት መካከል እነ እዮብ (ጆይ) ጭሮ በዳሶ እንደሚገኙበት ምንጮቻችን ገልጸዋል። 

ይህንን ውስብስብና ሀገራዊ ኢኮኖሚውን የጎዳ የገንዘብ ማሸሽ ወንጀል ለማጣራት የተቋቋመው ልዩ የምርመራ ቡድን ሜክሲኮ በሚገኘው የወንጀል ምርመራ ቢሮ አድርጎ ሥራውን በስፋት ጀምሯል። 

ምርመራውን በበላይነት እየመሩት የሚገኙት ኢንስፔክተሮች እና ከፋይናንስ ደህንነት መሥሪያ ቤት የተመደቡት ናቸው የተባሉ ኃላፊዎች መሆናቸው ታውቋል። 

"መርማሪ ቡድኑ እስካሁን ባደረገው ማጣራት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በባንክ አካውንታቸው የተላለፈላቸውን በርካታ ግለሰቦች ወደ ቢሮው በመጥራት ቃላቸውን እየተቀበለና መረጃዎችን እያሰባሰበ ይገኛል" በማለት አንድ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ አካል ለመሠረት ሚድያ ጠቁመዋል። 

በተጨማሪም የምርመራ ቡድኑ የገንዘብ ዝውውሩን ሰንሰለት ሙሉ በሙሉ ለመበጣጠስ ሲል ከተለያዩ የሀገሪቱ ባንኮች የተጠርጣሪዎቹንና የግብረ-አበሮቻቸውን የባንክ ሂሳብ መግለጫዎች (Bank Statements) በሕጋዊ መንገድ እንዲቀርቡለት ጥያቄ አቅርቧል። 

ይህ የሰነድ ማጣራት ሂደት በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የቤተ-እምነት መሪዎች ባለፈ በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ዳያስፖራዎች ጋር ያላቸውን የጥቅም ትስስር በግልጽ እያሳየ መምጣቱ ተነግሯል። 

ከፓስተሮቹና "ነቢይ ነን" ከሚሉት ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር የተሰማሩ የዳያስፖራ አባላትን የመለየትና በኢትዮጵያ ውስጥ ያፈሯቸውን ንብረቶች የመመዝገብ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተሰምቷል። 

ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው በመሆኑም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በወንጀሉ ዙሪያ መረጃ ለመለዋወጥና ሕጋዊ እርምጃዎችን ለማስተባበር በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎችን ለማነጋገር ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን የመሠረት ሚዲያ መረጃዎች ያመለክታሉ። 

እነዚህ የቤተ-እምነት ባለቤቶችና "ነቢያት" ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ፖለቲካ እንደሚደግፉ በማስመሰልና ይህንኑ እንደ ፖለቲካዊ ከለላ በመጠቀም ሀገሪቱን ሲዘርፉ መቆየታቸው ከምርመራው ሾልከው የወጡ አንዳንድ መረጃዎች ያመለክታሉ። 

በዚህም ስልት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በሕገ-ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ እንዲሸሽ ማድረጋቸው ተረጋግጧል። 

አስገራሚው ጉዳይ ደግሞ እነዚህ ግለሰቦች ይህንን ሁሉ ከፍተኛ ሀብት ቢያንቀሳቅሱም በሀገር ውስጥ ኢኮኖሚውን የሚደግፍ አንድም ሕጋዊ ኢንቨስትመንት አለመሥራታቸው ነው። 

በሌላ በኩል ይህ የፋይናንስ ደህንነትና የወንጀል ምርመራ ክትትል በቤተ-እምነት መሪዎች ላይ ብቻ የተገደበ አለመሆኑ ታውቋል። በተመሳሳይ የመኒ ላውንደሪንግ ወንጀል ውስጥ እጃቸው አለበት ተብለው በተጠረጠሩ አንዳንድ የሌሎች እምነቶች ተቋማት ላይም ጥብቅ ክትትል እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ምንጮቻችን አያይዘው ገልጸዋል። 

ምንጭ፡ መሠረት ሚዲያ ነው  

 

ዓለመአቀፍ የተዋሕዶ ቤተሰቦች 

 

 

 

 

 


No comments:

Post a Comment