ብፁዕ አቡነ ጢሞቲዎስ የኮሌጁ የበላይ ሃላፊ ሊቀ ጳጳስ |
- የኮሌጁ ካፊቴሪያ ለደቀ መዛሙርቱ ምግብ እንዳያዘጋጅ በሊቀ ጳጳሱ ታዝዟል
- ሊቀ ጳጳሱ ሁሉም መምህራን በመደበኛው የቀን መርሐ ግብር እንዳያስተምሩ ከልክለዋል
- ሊቀ ጳጳሱ በቅ/ሲኖዶስ ውሳኔ የተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ ሥራውን እንዳይጀምር አድርገዋል
- በሊቀ ጳጳሱ ዙሪያ የተሰለፈው የቤተ ክህነቱ የጨለማ ቡድን ፓትርያሪኩንም እያሳሳተ ነው
- ደቀ መዛሙርቱን ለማስወጣት የተጠራው የፖሊስ ኀይል ርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ አልኾነም
- በኮሌጁ የሚዘዋወሩ ስመ ደኅንነቶች ደቀ መዛሙርቱን፣ መምህራኑንና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን እያስፈራሩ ነው
የኮሌጁ መምህራን እንደሚናገሩት፣ የትምህርት አስተዳደሩ እንዲሻሻልና የደቀ መዛሙርቱ አካዳሚያዊ መብቶች እንዲከበሩ የቀረቡ ጥያቄዎችን ሓላፊነት በተሞላበት መንገድ ደቀ መዛሙርቱን ከመምህራኑ ጋራ በግልጽ በማወያየት ምላሽ መስጠት ይቻላል፡፡ ይህም ካልኾነ የመማር ማስተማሩን ጤናማነት/ሰላማዊነት ለመጠበቅ ተቃውሞ የቀረበባቸውና ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ መስማማት ያልቻሉ መምህራን ከሓላፊነታቸው ገለል እንዲሉ ማድረግ ነው፡፡
እየኾነ ያለው ግን ላለፉት 14 ዓመታት በኮሌጁ የበላይ ሓላፊነት ከቆዩ ሊቀ ጳጳስ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በቅ/ሲኖዶስ የተቋቋመው ኮሚቴ የማጣራት ሥራውን ጨርሶ ጥያቄያቸው ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ የተቃውሟቸው ሁለቱ ሓላፊዎችና መምህራን ወደ ክፍል ገብተው እንዳያስተምሩ በመከላከላቸው እልክ የተጋቡት ሊቀ ጳጳሱ ‹‹ያቋረጣችኹትን ትምህርት በአግባቡ አልጀመራችኹም›› በሚል የቀኑ መደበኛ መርሐ ግብር ከመጋቢት 30 ቀን ጀምሮ የተዘጋ መኾኑን የኮሌጁን ክብ ማኅተም ይዞ መጋቢት 30 ቀን 2005 ዓ.ም ጠዋት በወጣ ማስታወቂያ አሳስበዋል፤ በቁጥር 181 ያህል የሚኾኑት የቀን መደበኛ ደቀ መዛሙርትም ንብረት አስረክበው በአስቸኳይ ከኮሌጁ እንዲወጡ አዝዘዋል፡፡
ሊቀ ጳጳሱ በተለይ ከቀኑ መርሐ ግብር አስተባባሪና በክፉ ምክር እያሳተ የግል ጥቅሙን ከሚያካብተው ዘላለም ረድኤት ጋራ በመኾን ያወጡትን ይህን ማስታወቂያ የተቃወሙት ደቀ መዛሙርት ግን ከኮሌጁ አልወጡም፤ መምህራኑም ከማስተማር አልታቀቡም ነበር፡፡ ይህ በእጅጉ ያስቆጣቸው ሊቀ ጳጳሱ ትላንት ጠዋት መምህራኑን አስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት ‹‹ማስተማር እንደሌለባችኹ ለማሳወቅ›› በሚል አጀንዳ ሲወዛገቡ ውለዋል፡፡ ከጠዋቱ 3፡00 ጀምሮ ከቀትር በኋላ ቀጥሎ የዋለው ስብሰባው በንዴት በጦፉና አንዳንዶቹም ከሊቀ ጳጳሱ ጋራ ‹‹አንተ አንቺ ቀረሽ›› እላፊ ቃላት በሚነጋገሩ መምህራን ቁጣ የተሞላ ነበር ተብሏል፡፡
‹‹የሁለት ሰዎች ችግር ኮሌጁን ሊያዘጋ አይችልም›› ያሉት መምህራኑ ችግሩን በመመካከር መፍታት እንደሚቻልና በዚህ የማይፈታ ከኾነ ግን መምህራኑን መለወጥ የተለመደ አሠራር መኾኑን ተናግረዋል፡፡ መምህራኑ በቀኑ መደበኛ መርሐ ግብር እንዳያስተምሩ መከልከላቸውንና መርሐ ግብሩን ላልተወሰነ ጊዜ የመዝጋት ርምጃ የገለጹት ‹‹ከእግዝአብሔር ማዕድ ለምን ትለዩናላችኹ!›› በሚል እንደነበር ተዘግቧል፡፡ የቀኑ መርሐ ግብሩ ላልተወሰነ ጊዜ መዘጋቱን የሚገልጸው የአስተዳደሩ ውሳኔ በደብዳቤ እንዲሰጣቸው የጠየቁት መምህራኑ ‹‹የምንጠይቀውን አካል እንጠይቃለን፤›› በማለት መዛታቸውም ተነግሯል፡፡
የመርሐ ግብሩን መዘጋት ተከትሎ ሊቀ ጳጳሱ ለካፊቴሪያው ሓላፊ በቃል ባስተላለፉት ትእዛዝ ካፊቴሪያው ከትላንት በስቲያ ምሽት አንሥቶ ምግብ እንዳያዘጋጅ፣ ሠራተኞችም በምግብ ቤቱ ውስጥ እንዳይታዩ ተደርገዋል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ከትላንት በስቲያ ምሽት ጀምሮ ራትና ምሳ በመከልከል በረኀብ እንዲቀጡ መደረጋቸውን በትላንቱ ስብሰባ መምህራኑ በጥብቅ ተቃውመዋል፡፡
ማስታወቂያው በወጣበት ዕለት ምሽት በግቢያቸው የተሰበሰቡት ደቀ መዛሙርት በበኩላቸው÷ ሁለቱ መምህራን እንዳያስተምሩ ከመከልከላቸው በቀር 90 ከመቶው የመማር ማስተማሩ ሂደት በቀጠለበት ኹኔታ በሊቀ ጳጳሱ የተወሰደው ርምጃ ተቀባይነት እንደሌለው ተወያይተዋል፡፡ በጎጠኝነትና በጥቅም ሊከፋፍሏቸው በሚሞክሩት ጥቂት የኮሌጁ ሓላፊዎች ተንኮል ሳይለያዩ ፣ በረኀብ ሳይፈቱ ጥያቄያቸው ምላሽ እስኪሰጠው ድረስ በተቃውሟቸው ለመቀጠልም ተስማምተዋል፡፡
በትላንት ውሏቸው ደቀ መዛሙርቱ ጥቁር ቀሚሳቸውን በኮሌጁ ዋና መግቢያ አካባቢ በማንጠፍ ምጽዋት ሲለምኑ መዋላቸው ተዘግቧል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ምሳና ራታቸውን የተመገቡትም ከኮሌጁ የድኅረ ምረቃና የማታ ተማሪዎች ጀምሮ ከወጪና ገቢው ባገኙት የገንዘብ ርዳታ መኾኑ ተገልጧል፡፡ ደቀ መዛሙርቱን ከግቢው ለማስወጣት በኮሌጁ አስተዳደር ጥያቄ ወደ ግቢው የተጠራው ፖሊስ የተጠራበትን ርምጃ ከመውሰድ መታቀቡ ተነግሯል፤ ምክንያቱ የደቀ መዛሙርቱ እንቀስቃሴ ለፖሊስ ከተነገረው መረጃ በተቃራኒ ሰላማዊ መኾኑ ከታየ በኋላ ነው ተብሏል፡፡
በአንጻሩ ውዝግቡ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ ከኮሌጁ ቅጽር ያልራቁ፣ ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ የማያሳዩና ራሳቸውን በስመ ‹ደኅንነት› የሚያስተዋውቁ ኀይሎች ደቀ መዛሙርቱን፣ መምህራኑንና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን በተናጠል እየጠሩ እንደሚያስፈራሩና እንደሚያዋክቡ የደረሰን መረጃ ያስረዳል፡፡ አስገራሚው ነገር ከመካከላቸው፣ ‹‹አስተዳደሩን የቀን አበል የሚጠይቁ መኖራቸው ነው፤›› ብለዋል ምንጮቹ፡፡
በኮሌጁ ሊቀ ጳጳስና በመምህራኑ መካከል ትላንት የተካሄደው ስብሰባ፣ ‹‹ያልተለመዱና የማናውቀውን የሊቀ ጳጳሱን ጠባዕያት ፍንትው አድርጎ ያወጣ ነው፤›› የሚሉት መምህራኑ ሰው በዕርግና ዘመኑ እያስተዋለ፣ ታሪኩን እየጠበቀ የሚሄድ ኾኖ ሳለ ‹‹ለካስ አባ ጢሞቴዎስ የኮሌጁ አባት አልነበሩም!›› እንዳሰኛቸው በምሬት ይናገራሉ፡፡ የሊቀ ጳጳሱ አቋም ይዞታም እንደ ዘላለም ረድኤት ካሉ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ጥቅመኞችና ነገረ ሠሪዎች ክፉ ምክር ብቻ የሚነሣ እንዳልኾነ ጥርጣሬያቸውን ያጋራሉ፡፡
በኮሌጁ ምንጮች ጥርጣሬ÷ ውዝግቡ ከተቀሰቀበት ጊዜ ጀምሮ የደቀ መዛሙርቱ ጥያቄ በትክክለኛ ገጽታው ተፈትሾ እንዲፈታ ሳይሆን በሽምግልና እንዲዳፈን የተንቀሳቀሱት ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ መሰንበቻቸውን ከኮሌጁ ሊቀ ጳጳስ ጋራ በማድረግ ችግሩን እንዲያጣራ የተቋቋመው ኮሚቴ ሥራውን እንዳይጀምር ዕንቅፋት ፈጥረዋል፡፡ ከተቋቋመ ከአንድ ሳምንት በላይ ያስቆጠረው አጣሪ ኮሚቴ አባላትም አንድም ጊዜ እንኳ ለስብሰባ አልተጠሩም፡፡ በወሬ ደረጃ፣ በትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገብረ ዐማኑኤል የሚመራው ኮሚቴ ሥራውን እንዳይጀምር የተደረገው÷ ሊቀ ጳጳሱ ተቃውሞ የቀረበባቸው ሁለቱ ሓላፊዎች አይነኩብኝ በሚል የያዙት ለምክክር የማያመች አቋም ተፈርቶ ነው፡፡
በምንጮቹ ጥርጣሬ ደግሞ መሰንበቻቸውን ከሊቀ ጳጳሱ ጋራ ያደረጉት እነ ንቡረ ኤልያስ ኣብርሃና መሰሎቻቸው ለአዲሱ ፓትርያሪክ የተሳሳቱ መረጃዎችን በመስጠት የኮሌጁ ሊቀ ጳጳስ ሰሞኑን በይፋ ያወጡትን ርምጃዎች እንዲወስዱ ሳያደፋፍሯቸው አልቀረም፡፡ አህጉረ ስብከት ከጠቅላላ ገቢያቸው በሚያበረክቱት 5% አስተዋፅኦ የሚተዳደረውን ኮሌጅ የቀን መደበኛ መርሐ ግብር ለመዝጋትና የአህጉረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት የላኳቸውን ደቀ መዛሙርት ከኮሌጁ ለማስወጣት በርግጥም አንዳች የበላይ አካል ማረጋገጫ ያገኘ ይመስላል፡፡
ከ1953 ዓ.ም በፊት የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በመኾን ባበረከተው አገልግሎት ቤተ ክርስቲያንንና አገርን ያገለገሉ ሊቃውንት የፈሩበት ተቋም ከ1953 ዓ.ም በኋላ ለቤተ ክርስቲያናችን ቀዳሚ የነገረ መለኰት ኮሌጅ በመኾን አገልግሎቱን ጀምሯል፡፡ በጊዜው በአገራችን ከነበሩ ስድስት ኮሌጆችም አንዱ ነበር፡፡ ኮሌጁ ከ1953 – 1968 ዓ.ም ባሉት 16 ዓመታት እንደ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ፣ አምባሳደር አእምሮ ወንድምአገኘሁ ያሉ ተጠቃሽ ሊቃውንትን ጨምሮ 60 ደቀ መዛሙርትን ሲያፈራ ቆይቶ የመዘጋት ዕጣ የገጠመው በቀድሞው ሥርዐተ መንግሥት ትእዛዝ በ1969 ዓ.ም ነበር፡፡
ለ18 ዓመታት ተዘግቶ የቆየው ኮሌጅ በቅዱስ ሲኖዶስ ክትትልና በቀድሞው ፓትርያሪክ ጥረት በ1987 ዓ.ም ከተከፈተ ወዲህ፣ መጋቢት 30 ቀን 2005 ዓ.ም ላልተወሰነ ጊዜ እንዲዘጋ የተላለፈውን ውሳኔ ለየት የሚያደርገው ርምጃው በራሱ በኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ የተወሰደ መኾኑ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በሠለጠነው ዓለም በተለያዩ መስኮች የተካነ በርካታ የሰው ኅይል በሚያስፈልጋት ወቅት፣ ቀዳሚውና አንጋፋ የኾነው መንፈሳዊ ኮሌጅ ላልተወሰነም ይኹን ለአጭር ጊዜ መዘጋት ለሚያስከትለው ጉዳት ተጠያቂው ሊቀ ጳጳሱና የኮሌጁ ሓላፊዎች ብቻ ሳይሆኑ÷ በብፁዕነታቸው ዙሪያ ተሰልፎ ፓትርያሪኩን ለማሳሳት፣ በዚህም የኮሌጁ ሊቀ ጳጳስ ከፓትርያሪኩ ጋራ አላቸው የሚባለውን ቁርኝት በመበዝበዝ ግለሰባዊና ቡድናዊ ጥቅሙን ለማደላደል የሚራወጠው የጨለማ ቡድንም መኾኑ አይቀሬ ነው፡፡
የጨለማው ቡድን በጥቅመኞችና በመናፍቃን መመጋገብ የተፈጠረ ያልተቀደሰ ትስስር ነው፡፡ የትስስሩ ተግባር የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብት ለብክነት፣ ኦርቶዶክሳዊ ማንነቷን ለጥፋት/ብረዛ የሚዳርግ ነው፡፡ ይህን ፻ኛ የሐራ ዘተዋሕዶ ጦማር ለንባብ ስናበቃ ያለን ተስፋና ለዚህ ፅልመታዊ ቡድን የምናሰማው ዜና÷ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ፀረ – ጥቅመኛ ግለሰብና ፀረ – ሕገ ወጥ ቡድን ናቸው፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ፀረ – ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ናቸው የሚል ነው፡፡ይህን የፓትርያሪኩን አቋም የዜናነት ፋይዳ የሰጠነው ከጥቅመኛና ሕገ ወጥ ግለሰቦችና ቡድኖች እንዲሁም ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አራማጆች በአንጻሩ÷ ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅና ማስጠበቅ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻው ከፍተኛ ሥልጣን ባለቤት የኾነውን የቅዱስ ሲኖዶሱን ልዕልና በማክበር በዐበይት ጉዳዮች ላይ ሁሉ በቅ/ሲኖዶስ እያስወሰኑ መሥራት፤ በቅዱስ ሲኖዶስ የወጡ ሕጎችን፣ የተላለፉ መመሪያዎችንና ውሳኔዎችን ሁሉ በቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ አማካይነት በተግባር ላይ መዋላቸውን መከታተልና መቆጣጠር በሕገ ቤተ ክርስቲያን ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ የተሰጣቸውና ሊፈጽሙት የሚገባ ሓላፊነት መኾኑን በመዘንጋት አይደለም፡፡
የፓትርያሪኩ አቋም ለወዳጅም ለጠላትም በዜናነት ሊነገር የሚያስፈልገው÷ ከአንድ ፓትርያሪክ የሚጠበቁትና በሕገ ቤተ ክርስቲያን የሰፈሩት ሓላፊነቶች የተጻፉበትን ወረቀት ያህል ዋጋ እንኳ አጥተው፣ ተንቀውና ተጠቅጥቀው የቆዩበትን ያለፈውን ዘመን የመሻገር ተስፋ የአሁኑ ፓትርያሪክ ሥርዐተ ሢመታቸውን ከፈጸሙበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ መድረኮች ባስተላለፏቸው ምክሮችና መመሪያዎች ውስጥ በማግኘታችን ነው፡፡ ስለሆነም ተስፋ አለን – የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ጥያቄ የግለሰቦችንና ቡድኖችን ፍላጎት ሳይሆን የኮሌጁን ዓላማና ክብር በሚያስጠብቅ አኳኋን ምላሽ እንደሚያገኝ፡፡
Source:http://haratewahido.wordpress.com/
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment