- ማስታወቂያው የተለጠፈው በመርሐ ግብሩ አስተባባሪ ዘላለም ረድኤት ነው
- ደቀ መዛሙርቱ በተቃውሟቸው ለመቀጠል በመስማማት ትምህርት ጀምረዋል
- ‹‹ሲያስወጡን እንተናነቃለን፤ ኮሌጁን ቅ/ሲኖዶስ እንጂ ዘላለም አይዘጋውም›› /ደቀ መዛሙርቱ
- የኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ‹‹[ለደቀ መዛሙርቱ] እንኳን ምሳ ራት አልሰጥም›› እያሉ ነው
ሙስናንና የአሠራር ብልሹነትን በመቃወም ከሁለት ሳምንት በላይ በተቃውሞ የሰነበቱት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የቀን መደበኛ መርሐ ግብር ደቀ መዛሙርት በትላንትናው ዕለት ረፋድና ከሰዓት በኋላ በክፍል በመገኘት ትምህርት ጀምረዋል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ትምህርት በማቋረጥና በካፊቴሪያው ከመመገብ በመከልከል በኮሌጁ እየከፋ የመጣው ሙስናና የአሠራር ብልሹነት እንዲስተካከል፣ ለዚህም ተጠያቂ ናቸው ያሏቸው ሁለት ሓላፊዎች ከቦታቸው እንዲነሡ ያቀረቡትን ጥያቄ እየተማሩም ለመቀጠል በመወሰን ነው ትምህርታቸውን ለመጀመር የተስማሙት፡፡
በቀጣይ በሚቋቋመው ኮሚቴ መሠረት በሁለቱ ሓላፊዎች ላይ የቀረቡት ጥያቄዎች በሚገባ ተጠንተው ውሳኔ እንዲሰጥባቸው በፓትርያሪኩ የተሰጠውን መመሪያ መቀበላቸውን የተናገሩት ደቀ መዛሙርቱ÷ ሁለቱ ሓላፊዎች ማለትም የቀኑ መደበኛ መርሐ ግብር አስተባባሪ መ/ር ዘላለም ረድኤት እና አካዳሚክ ምክትል ዲኑ መ/ር ፍሥሓ ጽዮን ደመወዝ በክፍል ተገኝተው ማስተማራቸውን እንደሚቃወሙና ይህም ተቃውሞ ሓላፊዎቹ ውሳኔ እስኪሰጥባቸው ድረስ እንደሚቀጥል በመስማማት ነው ትምህርታቸውን የጀመሩት፡፡
ደቀ መዛሙርቱ የደረሱበት ውሳኔና ወደ ትምህርት የተመለሱበት ኹኔታ የተቀሰቀሰባቸውን ተቃውሞ ይበልጥ እንደሚያጠናክረው የሰጉት የቀን መርሐ ግብር አስተባባሪው መ/ር ዘላለም ረድኤት ግን ከመማር ማስተማሩ ጤናማነት ይልቅ በቀጣይ የደቀ መዛሙርቱ የተቃውሞ ስልት ግላዊ ጥቅማቸው አደጋ ውስጥ መግባቱን በማሰብ ውዝግቡን የሚያባብስ ርምጃ መውሰድን መምረጣቸው ተመልክቷል፡፡ በተካኑበት አሳባቂነትና ነገር ሠሪነት የኮሌጁን መምህራንና አስተዳደር እርስ በርስ በማተራመስ፣ ከሰሞኑ እንኳ ተቃውሞ ያነሡባቸውን ደቀ መዛሙርት ሳይቀር በጥቅም ለመከፋፈል እስከመሞከር የሚታወቁት አስተባባሪው÷ የኮሌጁን የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ በማሳሳት በትላንትናው ዕለት ባወጡት ማስታወቂያ፣ በተቃውሞ የሰነበቱት የቀኑ መደበኛ መርሐ ግብር ደቀ መዛሙርት በዕለቱ እስከ ቀኑ 8፡00 ኮሌጁን ለቀው እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
የኮሌጁን ፕሮቶኮል ሳያሟላ የወጣው ይኸው ማስታወቂያው÷ ደቀ መዛሙርቱ በትምህርት ገበታ ያልተገኙበትን ኹኔታ በመጥቀስ በዚህ ሳቢያ ኮሌጁ ለኪሳራ መዳረጉን፣ የቀኑ መርሐ ግብር ላልተወሰነ ጊዜ መዘጋቱንና ኮሌጁ የሚያተስናግደው የድኅረ ምረቃና የተከታታይ(የማታ) መርሐ ግብር ተማሪዎችን በመኾኑ ደቀ መዛሙርቱ እስከ ቀኑ ስምንት ሰዓት ኮሌጁን ለቀው እንዲወጡ የሚያሳስብ ነው ተብሏል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ትምህርት ገበታ በተመለሱበትና የመማር ማስተማሩ ሥርዐት በቀጠለበት ኹኔታ አስተባባሪው ያወጡት ይኸው ማሳሰቢያ መምህራኑን አስቆጥቷል፤ ደቀ መዛሙርቱን ግራ አጋብቷል፡፡
ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ልኡካን ጋራ በመተባበር ደቀ መዛሙርቱ ትምህርታቸውን እየቀጠሉና እየተመገቡ ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ ያግባቡት መምህራኑ፣ በአስተባባሪው እልክና በሊቀ ጳጳሱ ውሳኔ ብቻ መርሐ ግብሩ ሊስተጓጎል እንደማይችል ገልጸዋል፡፡ እንደ መምህራኑ አስተያየትየግል ጥቅምን ለመከላከል ከማሰብ በቀር እንዲህ ዐይነቱን ውሳኔ ለመስጠት የሚገፋፋ በቂ ኹኔታ የለም፤ ካለም ውሳኔውን መስጠት የሚችለው ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ ነው፡፡ ማሳሰቢያው የተመለከቱት ከከፍል ሲወጡ መኾኑን የተናገሩት ደቀ መዛሙርቱ በበኩላቸው÷ በሓላፊዎቹ ላይ ያነሷቸው ጥያቄዎች በቀጣይ በሚቋቋመው ኮሚቴ እንደሚታይ ተስፋ በማድረግ ትምህርት ከጀመሩ በኋላ በአስተባባሪው ወጥቷል በተባለው ማሳሰቢያ ግራ መጋባታቸውን ተናግረዋል፤ በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ መነጋገራቸውንም አስታውቀዋል፤ ‹‹ውጡ ብለው ሲያስወጡን እንተናነቃለን›› ብለዋል ደቀ መዛሙርቱ፡፡
በትላንትናው ዕለት የተቋረጠው ትምህርት መጀመሩን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ልኡካን፣ መምህራኑና የጸጥታ አባላት ተዘዋውረው መመልከታቸውንና ማረጋገጣቸውን የገለጹት ደቀ መዛሙርቱ÷ ካፊቴሪያው የምግብ አገልግሎት እንዳልሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ ምግብ አልተዘጋጀም ቢባልም እንጀራ እየተጫነ ሲወጣ መመልከታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ካፊቴሪያው ለደቀ መዛሙርቱ አገልግሎቱን እንዲቀጥል በመምህራኑና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ልኡካን ሲለመኑ የዋሉት የኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስም ‹‹እነዚህ መውጣት ነው ያለባቸው፤ ለእነርሱ እንኳን ምሳ ራትም አልሰጥ›› ሲሉ መደመጣቸው ተዘግቧል፡፡
እንደ መ/ር ዘላለም ረድኤት ባሉት የበታች ሓላፊዎች የተንኰልና ጥቅመኝነት ምክር ብዙ ስሕተት ሲፈጽሙ ለቆዩት ሊቀ ጳጳስ ይህ ዐይነቱ አነጋገራቸው አዲስ ባይሆንም፣ ደቀ መዛሙርቱ ያነሷቸው የሙስናና የአሠራር ብልሹነት ጥያቄዎች በርግጥም በቂ ማስተካከያና ምላሽ እንደሚሰጥባቸው በማግባባትና የፓትርያሪኩን መመሪያ ዋስትና በማድረግ ትምህርት ባስጀመሯቸው መምህራን ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳይፈጥር ተሰግቷል፡፡
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment