Thursday, April 18, 2013

በረኀብ የተዳከሙት ደቀ መዛሙርት ልመና በፖሊስ ታገደ፤ ፖሊስ ደቀ መዛሙርቱን ለመርዳት ከሚሞክሩ ምእመናን ጋራ ተወዛግቧል


  • ሓላፊዎቹ ከመምህራን የቀረቡላቸውን ሦስት ማግባቢያዎች በሙሉ ውድቅ አድርገዋል
  • ደቀ መዛሙርቱ በኮሌጁ አስተዳደር ላይ ክሥ መመሥረታቸው ተጠቁሟል
  • በአዲስ አበባ ዘመድ/መጠጊያ የሌላቸው ደቀ መዛሙርት በእጅጉ ተቸግረዋል
  • ፓትርያሪኩ ‹‹ጣልቃ አልገባም›› ማለታቸው የመምህራኑን ጥረት ጎድቷል
  • ‹‹ሃይማኖት የሌለው መምህር አያስተምረንም ባልን በረኀብ እየተቀጣን ነው›› /በደቀ መዛሙርቱ ከተለጠፉት ጥቅሶች አንዱ/
ሚያዝያ 7 ቀን 2005 ዓ.ም፤ ንጋት ላይ ነው፡፡ በአራት ኪሎ ወ.ወ.ክ.ማ በኩል ወደ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴCollege bld 01 ካቴድራል በሚያስገባው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሦስተኛ በር በርካታ ምእመናን ተሰባስበዋል፡፡ ዕለቱ የቅድስት ሥላሴ ወርኀዊ በዓል መታሰቢያ እንደመኾኑ የምእመናኑ ቁጥር ከፍተኛ ነበር፡፡ በኮሌጁ ቅጽር ውስጥ ቆመው ጥቁር ቀሚሳቸውን እንደለበሱ መሥመር ይዘውና ፊታቸውን በካቴድራሉ መውጫና መግቢያ ላይ አድርገው በዝምታ የቆሙትን ደቀ መዛሙርት ይመለከታሉ፡፡ የብዙዎቹ ደቀ መዛሙርት ገጽታ ድካምና ጉስቁልና ይነበብበታል፡፡ ከፊት ለፊታቸው ነጭ ጨርቅ ተዘርግቷል፡፡



በኮሌጁ በር ላይ የተለጠፉት ጥቅሶች ደቀ መዛሙርቱ በዚያ አኳኋን የተገኙበትን ምክንያት የሚያስረዱ ነበሩ – ‹‹ሃይማኖት የሌለው መምህር አያስተምረንም ባልን በረኀብ እየተቀጣን ነው››፤ ‹‹ወንጌል ይዘው በረኀብ እያሠቃዩን ነው››፤ ‹‹የረኀብ እሳት እየገረፈን ነውና ረኀባችንን አሥታግሱልን››፤ ‹‹እየሞትንም ቢኾን ሙስናንና ዘረኝነትን እንዋጋለን››፡፡ ከምእመናኑ የቻሉት በአጥሩ አሻግረው/አሾልከው በጨርቁ ላይ ምጽዋት ይጥሉላቸዋል፤ ያልቻሉት አዝነው ይሄዳል፡፡ አንዳንዶቹም ወደ ቅጽሩ ቀረብ ብለው ማብራሪያ ይጠይቃሉ፤ ምን እንርዳችኹ ባዩም ጥቂት አልነበረም፡፡ ኮሌጁ መዘጋቱንና ከሳምንት በላይ ምግብ መከልከላቸውን ለምእመናኑ ያስረዱት ደቀ መዛሙርቱ ችግራቸውን ገልጠው ይናገሩ ነበር፡፡
ትዕይንቱ የተቀየረው ከቆይታ በኋላ በስፍራው የደረሰው የፖሊስ ኀይል በወሰደው ርምጃ ነበር፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ርዳታ መጠየቃቸውን የተከላከለው ፖሊስ በኮሌጁ መግቢያ በር ላይ የተለጠፉ ወረቀቶችን ቀዳዷል፤ ምእመናኑም እንዲበተኑ አድርጓል፡፡ የታሸገ ውኃ እንኳ በአጥር ለማቀበል የተደረገውን ሙከራ ፖሊስ እንዳይገባ ሲከላከል ታይቷል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በግቢያቸው ውስጥ ተወስነው ርዳታ እየጠየቁ ባለበት ኹኔታ የፖሊስ ኀይሉ ከጸጥታ ማስከበር ባሻገር የወሰደውን ርምጃ ፊት ለፊት የተቃወሙ ምእመናን ከፖሊስ አባላቱ ጋራ ሙግት ገጥመው ታይተዋል፡፡ የሙግቱን ፋይዳቢስነት የተረዱ ጥቂት ምእመናን፣ ‹‹ምንም ቢኾን ልጆቻችን ናቸው፤›› በሚል ሰብሰብ ብለው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩን ለማነጋገር ወደ መንበረ ፓትርያሪክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ያመራሉ፡፡
ምእመናኑ በበጎ ሐሳብ ተነሣስተው ያደረጉት ሙከራ ግን እንዳሰቡት አልተሳካላቸውም፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩን በቅዳሴ መግቢያ ሰዓት ለማግኘት ሲጠባበቁ የነበሩት ምእመናኑ የገጠማቸው ኀይለ ቃልና ማመናጨቅ ነበር፤ ከቅዱስነታቸውም የሰሙት ቃል ቢኖር ‹‹ወደ ቅዳሴ እየገባኹ ነው›› የሚል እንደነበርና በዚህም ማዘናቸውን ተናግረዋል፡፡ ቅንነትና ለኮሌጁ ማሰብ ብቻ ለውዝግቡ እልባት ለመስጠት በቂ ነው የሚሉት ምእመናኑ፣ ደቀ መዛሙርቱ በምርጫው ወቅት ይዘውት የነበረውን አቋም በማስታወስ ‹‹ምናልባትም መፍትሔውን አዘግይቶ ለመበቀል ይኾን?›› የሚል ጥርጣሬ እንዳደረባቸው አልሸሸጉም፡፡
የቀን መደበኛ መርሐ ግብር ደቀ መዛሙርቱ በኮሌጁ ግቢ ውስጥ እስካሉ ድረስ የካፊቴሪያውን አገልግሎት መነፈግ እንዳልነበረባቸው የሚተቹ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው፣ በተለይም በአዲስ አበባ ዘመድና መጠጊያ የሌላቸው ደቀ መዛሙርት በከፍተኛ ችግር ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ከኮሌጁ ምንጮች ለመረዳት እንደተቻለው ደቀ መዛሙርቱ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ÷ መብታቸውን በጠየቁ በረኀብ እየተቀጡ መኾኑን፣ የተቃወሟቸው ሁለቱ ሓላፊዎች የያዟቸው ኮርሶች ከመስተጓጎላቸው በቀር ትምህርት እየተማሩ ባሉበት ኹኔታ መምህራን እንዳያስተምሩ፣ መርሐ ግብሩም እንዲቋረጥ መደረጉን በመጥቀስ በኮሌጁ ላይ ክሥ መሥርተዋል፡፡
ይኸው የደቀ መዛሙርቱ ርምጃ የተሰማው የኮሌጁ መምህራን፣ ደቀ መዛሙርቱ የተቃወሟቸውን ሁለቱን ሓላፊዎች ለማግባባት ያቀረቧቸው ሦስት የማግባቢያ አማራጮች በሙሉ በሁለቱ ሓላፊዎች ውድቅ መደረጋቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡ ባለፈው ሳምንት ኀሙስ መምህራኑ ሁለቱን ሓላፊዎች በሦስት አማራጮች ለማግባባት ቀኑን ሙሉ ባደረጉት ጥረት፣ በእነርሱ ምክንያት ኮሌጁ መዘጋት እንደሌለበት፣ የመፍትሔው አካል መኾን እንዳለባቸውና ጫናውንም መጋራት እንደሚገባቸው አሳስበዋቸው እንደነበር ተገልጧል፡፡
ተቃውሞ የቀረበባቸው የቀን መርሐ ግብር አስተባባሪውና የአካዳሚክ ዲኑ ምላሽ ግን ‹‹ከሥልጣኔ ዝቅ ብዬ ነው የማናግራችኹ እናንተ አያገባችኹም፣ ከእነርሱም ጋራ ድርድር አንቀመጥም፤ ገብተው ይማሩ፣ እኛም እናስተምራለን፤ ካልተማሩ ውጤቱን እናያለን፤›› በሚል ግትርነትና ማናለብኝነት ነበር ማግባቢያዎቹን ያልተቀበሏቸው፡፡ መምህራኑ ያቀረቧቸው ሦስት ማግባቢያዎች ከባከነው ጊዜ አንጻር በሓላፊዎቹ የተያዙት ኮርሶች የሚሸፈኑባቸውን አማራጮች፣ ኮርሶቹ ከአማራጮቹ በአንዱ ከተሸፈኑ በኋላ ሓላፊዎቹ ፈተና እንዲያዘጋጁ፣ የፈተናው እርማትና ውጤት ደግሞ ለዚህ ተብሎ በሚቋቋም ኮሚቴ እንዲሠራ የሚያመላክት እንደነበር ተዘግቧል፡፡
ውዝግቡ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የማግባቢያ ጥረቶችን ቢያደርጉም ያልተሳካላቸው መምህራኑ፣ የቀኑ መደበኛ መርሐ ግብር ላልተወሰነ ጊዜ መዘጋቱን የሚገልጸው የአስተዳደሩ ውሳኔ የተላለፈበት ደብዳቤ እንደደረሳቸው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩን ለማነጋገር ዐቅደው በዝግጅት ላይ እንደነበሩ ተዘግቧል፡፡ ይኹንና ፓትርያሪኩ ‹‹እኔ በመሐል ገብቼ ምን አደርጋለኹ›› በማለት ለቪ.ኦ.ኤ የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት የሰጡት ምላሽ ከጥረታቸው እንደገታቸው ተመልክቷል፡፡
http://haratewahido.wordpress.com/

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment