Wednesday, April 10, 2013

መታሰር ያልሰለቸው ቀበሮ መነኩሴ




(አንድ አድርገን ሚያዚያ 1 2005 ዓ.ም)፡- በደብረ ብርሐን ከተማ አባ በረከት የሚባል ሰው በገዳማት እና በአድባራት ላይ ብዙ ጉዳት እንዳደረሰ ገልጸን ከወራት በፊት መጻፈችን ይታወሳል፡፡ አባ በረከት መጀመሪያ ጎንደር ይኖር የነበረ ከዚያም ደንጨት ዮሐንስ ገዳም ሲያገለግል የነበረ ሰው ሲሆን ከመንዝ አካባቢ እንደመጣ የጀርባ ታሪኩ ይናገራል ፡፡ የካቲት 2004 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በደብረ ብርሐን ከተማ በደብረ ማዕዶት ቅድስት አርሴማ ገዳም በመግባት ሲያገለግል እንደነበር መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ገዳም የሚመጡ በርካታ እህቶችን በማታለል ዝሙት ለመፈጸም ሲንቀሳቀስ ስለተደረሰበት ይህን ድርጊቱን እንዲያቆም ከወንድሞች ምክር ተሰጥቶትም ነበር፡፡  በቤተመቅደስ ውስጥ ድፍረትና ክህደት የተሞላበት የአማኙን እምነት የሚቀንስና ለትልቅ ድፍረት የሚያደፋፍር እንቅስቃሴዎች ሲያደርግ እንደነበር በጊዜው በቦታው የነበሩ የአይን እማኞች  ገልጸዋል ፤ ገዳም ሲገባ አብራው የመጣች ወለተ መስቀል የምትባል  መነኩሴ የነበረች ሲሆን ፤ በገዳሙ በነበረው ቆይታ ለገዳማውያን አገልጋይ ካህናት ‹‹ከአንድ እናት ማህጸን የወጣን እህቴ ነች›› እያለ ሲያወራ እና ሲያስወራም ነበር ፡፡(ሴትየዋ በአሁኑ ሰዓት ከአባ በረከት የልጅ እናት ሆናለች)፡፡ ይህ ሰው አውደ ምህረት አግኝቶ የለሰለሰ የኦርቶዶክስ የሚመስል ውስጡ እሾህ የሆነ ትምህርት ባያስተምርም እንኳን ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፤ ስለ ቅዱሳን መላእክት ፤ ስለ ጻድቃን ሰማዕታት ያማልዳሉ? አያማልዱም? የሚል አርእስት በማንሳት በርካታ እህቶች ፤ ወንድሞችና የአብት ተማሪዎች ላይ ውስጥ ውስጡን ምንፍቅና ሲዘራ እንደነበር ከእሱ ጋር ከተወያዩ ጥቂት ምዕመና አማካኝነት ለማወቅ ተችሏል ፡፡

ይህ ሰው በደነባ በዓታ ለማርያም አንድነት ገዳም አባ ገብረ ሥላሴ በሚል አዲስ መጠሪያ ስም ተቀጥሮ አንድ ወር በገዳሙ በመቆየት  የገዳሙን በርካታ ንዋየ ቅዱሳን በመስረቅ ነሀሴ 19 ቀን 2004 ዓ.ም በፖሊስ እንደተያዘ እና ፖሊስም ባደረገው ማጣራት በርካታ የቤተክርስቲያኒቱ ንብረቶች ፤ በተለያዩ ስሞች የወጡ መታወቂያዎች ፤ የገዳማትና የአብያተክርስቲያናት ሕገ-ወጥ ማህተሞች እና መሰል ለወንጀል የሚገለገልባቸው ቁሳቁሶች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ነበር፡፡ ፖሊስ ይህን ማስረጃ በመያዝ ለደነባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ በመመስረት ከሙሉ ማስረጃ ጋር በማቅረብ በወቅቱ የፍርድ ውሳኔ አሰጥቶበት እንደ ነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

ይህ ቀበሮ መነኩሴ ፍርዱን ጨርሶ ከእስር ሲወጣ ወደ ቀድሞ የማጭበርበር ተግባሩ ለመመለስ ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ ፍርድ ቤቱ ያሳለፈበት የፍርድ ውሳኔም ቅንጣት ያህል ከጥፋቱ እንዲማር እና እንዲታረም አላደረገውም፡፡ ከሳምንት በፊት ከወደ ጎንደር የደረሰን መረጃ ይህን ሰው የሚመለከት ነበር ፡፡ ይህ ሰው ደብረ ብርሐን ቅድስት አርሴማ እና በደነባ በዓታ ለማርያም ገዳም ስራው ሲታወቅበት ሀገር በመቀየር ወደ ናዝሬት በመሄድ ጥቂት ጊዜ ከቆየ በኋላ ከናዝሬት ወደ ጎንደር በማምራት መሰል የማጭበርበር ሥራውን ቀጥሎበታል፡፡ በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ማክሰኝት ከተማ ቀድሞ ስለዚህ መሰሪ ሰው አንድ አድርገን ብሎግ ያወጣችውን መረጃ አንብበው በነበሩ የሰንበት ተማሪዎች ከአካባቢው ፖሊሶች ጋር በመተባበር በመሰል ተግባር ተይዞ ዘብጥያ መውረዱን የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህ ሰው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከመዋሉ በፊት ቆብና ቀሚሱን አድርጎ መስቀሉን ይዞ መጠጥ ቤት ቢራ ሲጠጣ በቅርብ ሆነው ሲከታተሉት ከነበሩት ወንድሞች ለማወቅ ተችሏል ፡፡ ደስ ሲለውም ቆቡንና ቀሚሱን በማውለቅ በጅንስ ሱሪና በጃኬት  ይህን ተግባር ሲፈጽም እንደነበር ከአይን እማኞች የደረሰን ማስረጃ ያስረዳል፡፡

ፖሊስ ይህን ሰው በአካባቢው ፍርድ ቤት በማቅረብ  የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆበት በሰውየውን ጀርባ የወንጀል ታሪክ በማጥናት ፤ የሰራቸውን ወንጀሎች በመሰብሰብ ፤ ስለሰራው ወንጀል የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ምንኩስናን ከተቀበለበት ገዳም እና ከተለያዩ ቦታዎች በመውሰድና በማጠናቀር ጠንከር ያለ ክስ ለፍርድ ቤት አቅርቧል፡፡ ሰንበት ተማሪዎች ስለዚህ ሰው ከአንድ አድርገን ብሎግ ላይ ያነበቡትን መረጃ ለፖሊስ በሀርድ ኮፒ በመስጠት ፖሊስ በመረጃ መልክ ተጠቅሙ የራሱን ማጣራት እንዲያካሂድ መንገድ ማመላከት ችለዋል ፤ ፖሊስም የተሰጠውን መረጃ በመቀበል ስለ ትክክለኝነቱ ከደነባ ፖሊስ እና ከደነባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጋር በመነጋገር ትክክለኝነቱን ከማረጋገጥ በተጨማሪ ያስፈልጉኛል ያላቸውን ማስረጃዎች በፊት ከተከሰሰበት ወረዳ ፖሊስ እንደወሰደ ለማወቅ ችለናል፡፡ አንድ አድርገን ብሎግም መረጃ ፈላጊና ተፈላጊ እንዲገናኙ መንገድ አመላክታለች ፡፡ የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ፖሊስ ክሱ የቀረበለት ፍርድ ቤት የሚሰጠውን የፍርድ ውሳኔ በመያዝ ከፖሊስ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ጋር በመተባበር ፍርዱን ለሕዝቡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለማስተላለፍና ምዕመኑ ከመሰል ሰዎች ራሱን እንዲጠብቅ የሚያስችል ትምህርት የሚሰጥ ፕሮግራም ለመስራት ሃሳብ እንዳለውም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የአንድ አድርገን መልዕክት
ቤተክርስቲያንን በዘበኛ ብቻ መጠበቅ አይቻልም ፤ ቤተክርስቲያንን በሰንበት ተማሪዎች ፤ በዲያቆናት ፤ በቀሳውስትና በጳጳሳት ብቻ መጠበቅ አይቻልም፡፡ ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ የሚቻለው በሁላችን ሙሉ በሆነ ተሳትፎ ብቻ ነው ፡፡ ዛሬ ደብረ ብርሐን ላይ የተሰራው ስራ ነገ ወደ እኛ ሀገረ ስብከት ይመጣል ብለን በማሰብ ቤተ ክርስቲያንን ከእኩይ ሰዎችና ስራዎች የመጠበቅ ሃላፊነቱ የሁላችንም መሆን መቻል አለበት ፡፡ ትላንት ሀዋሳ ላይ የተከናወነው ነገር ነገ እኛ ያለንበት ቦታ እግር አውጥቶ እንዳይመጣ ቀን ከሌት የመጠበቅ ሃላፊነት በጫንቃችን ላይ መሸከማችንን መዘንጋት የለብንም ፤ ዛሬ በእንግሊዝ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የተከሰተው አለመግባባት ነገ ወደ መሰል ሀገሮች እንደማይተላለፍ እርግጠኞች ሆነን መናገር ስለማንችል አሁን ሁላችን ባለንበት ቤተክርስቲያን ያለውን ሰላም በመጠበቅ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ሃላፊነት እንዳለብን መዘንጋት መቻል የለብንም ፤  ሀገር ውስጥ ትላንት ደብረ ብርሀንና ደነባ ከተማ ላይ የተሰራውን ስራ የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ማክስኝት ከተማ የሰንበት ተማሪዎች መረጃውን ስላነበቡ አካባቢያቸው ላይ ያሉትን አብያተክርስቲያትን ከዚህ ቀበሮ መነኩሴ ከመከላከል በተጨማሪ በሕግ እንዲጠየቅ ከፖሊስ ጋር አብረው ትልቅ የወንጀል መከላከል ስራ መስራት ችለዋል፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያናችንን ዘመኑን ከዋጁ አገልጋይ መሳይ ሌቦች ፤ ሰባኪያን መሳይ መናፍቆች ፤ ተዋህዶ መሳይ ተሃድሶዎች ፤ የቤተ ክርስቲያንን ማዕረግ በገንዘብ ካገኙ መጋቢ ሀዲሶች   መጠበቅ የእኛ እና የእኛ ሃላፊነት መሆኑን መገንዘብ መቻል አለብን፡፡ እያንዳንዳችን የመረጃ ሰው ሆነን ቤተክርስቲያንን ካልጠበቅን ማንም መጥቶ የእኛን ስራ ሊሰራልን እንደማይችልም ልናውቅ እና ልንገነዘብ ይገባናል፡፡ 

ሁላችሁም የቤተክርስቲያናችሁን ሰላም ጠብቁ፡፡ የዚህን ሰው የፍርድ ቤት ሂደት ተከታትለን መረጃዎችን የምናደርስ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

ቸር ሰንብቱ

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment