ቅዱስ ሩፋኤል ወኤልያስ ቤተክርስቲያን |
(አንድ አድርገን ሚያዚያ 15 2005 ዓ.ም)፡- በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 የሚገኝው የቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን በኢንደስትሪ ዞን ላይ የተሰራ ነው በሚል የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ለቅዱስ ሲኖዶስ በጻፈው ደብዳቤ 24 ሰዓት ሳይሞላው ማፍረሱን የደብሩ ኃላፊዎች አስወቁ፡፡
ሚያዚያ 9 ቀን 2005 ዓ.ም ከምሽቱ አንድ ሰዓት ሲሆን የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤልሳቤት መንግስቱ የደብሩን ኃላፊዎች በጽ/ቤታቸው እንዲገኙ የስልክ ጥሪ በማድረግ ቤተክርስቲያን እዲያፈርሱ የነገሯቸው መሆኑን ያስረዱት የደብሩ ኃላፊዎች ቤተ ክርስቲያን የማፍረስ ስልጣን የእነሱ አለመሆኑን በመግለጻቸው በማግስቱ ጠዋት 3 ሰዓት ወረዳው ለሲኖዶስ የላከው ደብዳቤ ይዘው ከወረዳው ተወካይ ጋር በሲኖዶስ ተገናኝተው እየተወያዩ ሳለ የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ በሶስት መኪና ፖሊስ በመታገዝ በሕገ ወጥ መንገድ እንዲፈርስ ማድረጋቸው የደብሩ ኃላፊዎች አስታወቁ፡፡
የቤተክርስቲያኗ ዋና ጸሀፊ መሪጌታ ይትባረክ ታከለ እንደገለጹት መጋቢት 30 ቀን 2001 ዓ.ም በአቶ ገመቹ ወርዶፋ እና ከአቶ ቦኬ ገመቹ ለቤተክርስቲያን መገልገያ ይሆን ዘንድ አንድ ሺህ ካሬ ሜትር ቦታን በስጦታ መረከባቸውን ለሶስት ዓመት ሙሉ የቤተክርስቲያን ስርዓት እየተደረገበት እና እንደ ሌሎች አብያተ ክርስትያናት ካርታ ለማግኝት በመጠባበቅ ላይ ሳለ ከስራ ሰዓት ውጪ በወረዳው ጽ/ቤት እንዲገኙ በማድረግና የጻፉት ደብዳቤ 24 ሰዓት ሳይሞላው ቤተ ክርስቲያቱን ማፍረስ ሕገ ወጥ በመሆኑ ወንጀል ነው ብለዋል፡፡
የደብሩ ንብረት ክፍል ዲያቆን እንደሻው አማረ እና ቄሰ ገበዝ አበበ ዘውዱ በበኩላቸው በቤተክርስቲያኒቱ ሕግ መሠረት የተያዘው አብይ ጾም እያጋመሱ ባሉበት እና ምንም አይነት ንብረት እንድናወጣ ሣይደረግ መፍረሱ ከግለሰብ መብት ባነሰ ሁኔታ አምልኮተ እግዚአብሔር የሚከናወንበት ቦታ በሕገ ወጥነት መፍረሱ ወንጀል ትልቅ ወንጀል ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ዋልድባ ገዳም ላይ በስኳር ፕሮጀክት ስም ለመፍረስ የተዘጋጁ ከ13 በላይ አብያተክርስቲያናት መኖራቸው ይታወቃል ፤ የእነዚህ ቤተክርስቲያናት የወደፊት እጣ ፈንታ ምን እንደሆነ ባይታወቅም እስከ አሁን ድረስ ምንም አይነት እርምጃ መንግሥት እንዳልወሰደባቸው ይታወቃል ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከዓመታት በፊት ከአስር የሚበልጡ አብያተ ክርስቲያናት በጣና በለስ የመስኖ ፕሮጀክት ስም ከቦታቸው ተነስተው ጥግ ጥጋቸውን በአነስተኛ መቃኞ እንዲቀመጡ መደረጋቸው ይታወቃል ፤ በቦታው ላይም ብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ስራውን በኃላፊነት በመውሰድ ከስሩ ካሉ ድርጅቶች ጋር በመሆን ከፍተኛ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት እያካሄደ መሆኑ ይታወቃል፡፡ አንድ አድርገን ፕሮጀክቶቹ አይሰሩ የሚል ጨለምተኛ አመለካከት ባይኖራትም በአሁኑ ሰዓት በልማት ስም ቤተክርስቲያናትን እያነሱ ቦታቸው ላይ የፕሮጀክቶችን ስራ መስራት ተገቢ ነው የሚል እምነት የላትም፡፡
ምንጭ ግብአት ፡- ኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ(ሚያዚያ 15 2005 ዓ.ም)
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment