Friday, April 5, 2013

የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበር አባላት የተሐድሶ ኑፋቄን እንዲዋጉ ፓትርያሪኩ አሳሰቡ


  • ማኅበሩ በሦስት አህጉረ ስብከት ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ከፍቷል
  • የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ሥራ አስፈጻሚን በዳግም ምርጫ አጠናክሯል
  • መናፍቁ አሰግድ ሣህሉን ለማስመረጥ የተደረገው ሙከራ ተቀባይነት አላገኘም
  • ሁለት የፀረ – ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሰባክያንና ዘማርያን ጥምረት አባላት በሥራ አስፈጻሚነት ተካተዋል
  • ማኅበሩ ሕጋዊ ዕውቅናና ተቀባይነት ካላቸው የቤተ ክርስቲያናችን አካላት ጋራ ሁሉ ተባብሮ ለመሥራት ያለውን ዝግጁነት ዳግም አረጋግጧል
Theology Association Logoበቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እና በቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ምሩቃንን በአባልነት በመያዝ የተመሠረተ ነው፤ ዋና ዓላማው÷ የወንጌል ትምህርት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ሐዋርያዊ አገልግሎት መስጠት፣ የቤተ ክርስቲያናችን ዶግማ፣ ሥርዐት፣ ትውፊት እና ንዋያተ ቅድሳት በአግባቡ እንዲጠበቁ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ ነው – የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበር፡፡
ማኅበሩ ዓላማውን የሚተገብርባቸውየስብከተ ወንጌል፣ የትምህርት፣ የኅትመትና ሥርጭት፣ የሕግ፣ የልማት፣ የመረጃና መዛግብት፣ የሒሳብና ንብረት አስተዳደር እንዲሁም የቁጥጥር ክፍሎችን አዋቅሯል፤ እኒህን ተግባራት የሚያስፈጽሙ 12 የሥራ አስፈጻሚና አፈጻጸሙን በበላይነት የሚመሩ 12 የሥራ አመራር አባላት እንዳሉትም ማኅበሩ ያሰራጫቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡


ሁለቱ የነገረ መለኰት ኮሌጆች በዘረጓቸው የቀን መደበኛና ተከታታይ የማታ ትምህርት መርሐ ግብሮች ከሠለጠኑትና በቁጥር ከ1700 በላይ ከሚኾኑት ምሩቃን የሚበዙትን በአባልነት ያቀፈው ማኅበሩ÷ ከአባላቱ በሚሰበስበው ወርኀዊ አስተዋፅኦና ከበጎ አድራጊ ኦርቶዶክሳውያን በሚያገኘው ድጋፍ አገልግሎቱን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ማኅበሩ በቀድሞው ፓትርያሪክ መልካም ፈቃድና በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቡነ ፊልጶስ ጥረት በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እንደ ዋና ጽ/ቤት የሚገለገልበት ቢሮ የተሰጠው ሲኾን በአዲስ አበባ፣ መቐለ እና ጅማ አህጉረ ስብከት ሦስት ቅርንጫፍ ቢሮዎችን መክፈቱ ተዘግቧል፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሑሩ ወመሀሩ፤ ሂዱና አስተምሩ›› /ማቴ.፳፰÷፲፱/ ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸውን የትእዛዝ ቃል በአደራነት ከተቀበሉና በተለይም በመደበኛው መርሐ ግብር ከሠለጠኑ ተመራቂዎች መካከል ‹‹አብዛኛዎቹ በቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ መሠረት በዕጣ በተደለደሉበት አህጉረ ስብከት በማገልገል ላይ ይገኛሉ፤›› ይላል ለማኅበሩ አራተኛ ጠቅላላ ጉባኤ የቀረበው ሪፖርት፡፡ በተከታታይ መርሐ ግብር ከሠለጠኑት ተመራቂዎች ከፊሎቹ አስቀድሞም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በማገልገል ላይ እንደነበሩ ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ አሁንም በዚያው የተሻለ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንዳሉ ገልጧል፡፡
ከማኅበሩ ምሩቃን አባላት መካከል÷ 2 በሊቀ ጵጵስና ማዕርግ፣ 10 በአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነት፣ 16 በጠቅላይ ቤተ ክህነትና በሦስቱ ኮሌጆች በከፍተኛ ሓላፊነት፣ 50 በአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪነት ሌሎች ብዙዎችም በአህጉረ ስብከትና በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌልና የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ ክፍሎች ውስጥ በሓላፊነት ተመድበው እንደሚያገለግሉ የማኅበሩ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
የምሩቃን ማኅበሩ አገልግሎቱን ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ በተለያዩ አህጉረ ስብከት ባከናወነው ሐዋርያዊ ተግባር ከ7100 በላይ ሰዎች በኦርቶዶክሳዊ እምነት መጠመቃቸው በማኅበሩ ሪፖርት ተገልጧል፡፡ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ለተካሄደው የማኅበሩ አራተኛ ጠቅላላ ጉባኤ የቀረበው ሪፖርት እንደሚዘረዝረው፣ ከጥር 21 – 22 ቀን 2003 ዓ.ም በከምባታ አላባ ጠምባሮ ሀ/ስብከት በዱርጊ ማኅደረ ስብሐት ቅድስት ማርያምና በአምቡኩ ቅዱስ ገብርኤል አብያተ ክርስቲያን ለ2500 ሰዎች ሥርዐተ ጥምቀት ተፈጽሞላቸዋል፡፡ በሁለት ቀናት በተከናወነው ሥርዐተ ጥምቀት የሀ/ስብከቱን ሥራ አስኪያጅና ዋና ጸሐፊውን ጨምሮ የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የመርሐ ግብሩ ተካፋዮች ነበሩ፡፡
የካቲት 20 ቀን 2003 ዓ.ም በሐዲያና ስልጤ ሀ/ስብከት በሊሙ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን 170 ሰዎች ኦርቶዶክሳዊ እምነትን ተምረውና አምነው ሥርዐተ ጥምቀት ተፈጽሞላቸዋል፡፡ የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ሥርዐተ ጥምቀቱ በሚፈጽበት ዋዜማ በስፍራው ተገኝተው የማበረታቻ አባታዊ ትምህርት መስጠታቸውን ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ አብዛኛዎቹ ተጠማቂዎች ከፕሮቴስንታንት እምነት የተመለሱ መኾኑን ጠቅሷል፡፡
በየካቲት ወር አጋማሽ 2003 ዓ.ም በአሶሳ ሀ/ስብከት በተፈጸመው ሐዋርያዊ አገልግሎት በኦርቶዶክሳዊ እምነት ላመኑ 4500 ሰዎችሥርዐተ ጥምቀት መፈጸሙን ያተተው የማኅበሩ ሪፖርት፣ ይኸው ተግባር ለወደፊቱም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክቷል፡፡
Theology Graduates Association 4th Gen Assembly
(ፎቶ ፳፻፬ ዓ.ም – የማኅበሩ ፬ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በተካሄደበት ወቅት
ዲ/ን ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ ሲናገሩ)
ማኅበሩ ከትላንት በስቲያ እሑድ የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ቅርንጫፉን በአዲስ የቅርንጫፍ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ለማጠናከር በአህጉረ ስብከቱ የስብሰባ አዳራሽ ባካሄደው የምርጫ ሥነ ሥርዐት ላይ፣ ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት መጠናከርና መስፋፋትበዓላማው በግልጽ ያስቀመጠውን አቋም፣ ሕጋዊ ዕውቅናና ተቀባይነት ካላቸው የቤተ ክርስቲያናችን አካላት ሁሉ ጋራ በመተባበርና በመግባባት ለማገልገል ባለው ዝግጁነት ዳግም አረጋግጦታል፡፡
ይኸው የጉባኤተኛው አቋም የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ብሎጎች የምሩቃን ማኅበሩን በማኅበረ ቅዱሳን ቅጥያነት በመፈረጅ፣ በየሰበቡ በከንቱ ከሚወነጅሉትና በእጅጉ ከሚሰጉት አንድ አገልጋይ ጋራ በማጣበቅ የሚያናፍሱትን አሉባልታ ‹‹ዕርቃኑን ያስቀረ ነው፤›› ይላሉ አስተያየታቸውን ለሐራዊ ምንጮች የሰጡ የጉባኤው ተሳታፊዎች፡፡ ገንዘባቸውንና ጊዜያቸውን ሰጥተው በበጎ ፈቃድ የሚያገልግሉ የማኅበሩ አመራርና አስፈጻሚ አባላት በዋናው የማኅበሩ ጽ/ቤቱ በአንድ የሙሉ ጊዜ ጸሐፊ ብቻ በመታገዝ ለሚሰጡት አገልግሎትና ለሚያሳዩት ትጋት ጉባኤው በምስጋና ቃላት አበረታቷቸዋል፡፡
የማኅበሩን የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ቅርንጫፍ በአዲስ የሥራ አስፈጻሚ አባላት ለማጠናከር በተካሄደው ምርጫ÷ ስምንት ተጠቋሚዎችበማኅበሩ ሥራ አመራር አባላት፣ አምስት አባላት ደግሞ በጉባኤተኛው ከተጠቆሙ በኋላ ለቅርንጫፍ ቢሮው ሥራ አስፈጻሚነት የሚያስፈልጉት ሰባት አባላት በውዳሴ ማርያም ጸሎት በዕጣ እንዲለዩ ተደርጓል፡፡ በዕጣ ከተለዩትና ለቀጣይ. . . እንዲያገለግሉ ከተመረጡት ሰባት የቅርንጫፉ ሥራ አስፈጻሚ አባላት መካከል ሁለቱ፣ የፕሮቴስንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አደጋዎችን በማጋለጥና ፈጥኖ በመመከት ላይ አተኩሮ የሚያገለግለው የፀረ – ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሰባክያንና ዘማርያን ጥምረት አባላት መኾናቸው ተጠቅሷል፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት በቀናዒ ኦርቶዶክሳውያን ሰባክያንና ዘማርያን በጎ ፈቃድ የተመሠረተው ጥምረቱ÷ በቅርቡ በውስጡ ባካሄዳቸው ተከታታይ የእርስ በርስ መተያያ ውይይቶችና የወቅታዊ ኹኔታዎች ግምገማ ራሱን አጥርቶ፣ ከፍተኛ አቅምና ጠንካራ ትስስር ፈጥሮ ለሰፊ አገልግሎት መዘጋጀቱ ታውቋል፡፡
በአንጻሩ መናፍቁ አሰግድ ሣህሉ ከተመራጮች እንዲካተት በአንድ የእምነትም የምግባርም ደዌ ባለበት መሰሉ የቀረበው ጥቆማ የጉባኤተኛውን ተቀባይነት አለማግኘቱ ተገልጧል፤ የመናፍቁ ጥቆማ ውድቅ የተደረገበት አቋምም በቤቱ የጋለ ድጋፍ መጽናቱ ተዘግቧል፡፡ ጉባኤተኛው አሰግድ በሌለበት በሥራ አስፈጻሚነት እንዲመረጥ የቀረበውን ጥቆማ በጠንካራ ተቃውሞ ውድቅ ያደረገበትና በግልጽ ለተሰብሳቢው የቀረበው ምክንያት÷ የምሩቃን ማኅበሩን የአባልነት ቅጽ አለመሙላቱ፣ እንዲሞላም ተጠይቆ ያልፈቀደና አባል አለመኾኑ ነው፡፡
ከዚህ ቀጥተኛ ምክንያት ጀርባ ያለው ዋነኛው ጉዳይ ግን በሁለት ነጥቦች የሚጠቃለለው የአሰግድ መሠረታዊ ጉድለቶች ናቸው፤ ቀዳሚውበሃይማኖት ያለበት ጽኑ የመናፍቅነት፣ የመናፍቃን ምንደኝነትና አሽከርነት ችግር ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በተጭበረበረና በሙሰኝነት በቃረመው የድጋፍ ሰነድ በተከታታይ መርሐ ግብር ገብቶ ለአምስት ዓመት በተማሪነት ስም ኅቡእ የኑፋቄ ሥራ ሲሠራ የቆየበት መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደር ዲግሪውን እንዳይቀበል ያስተላለፈበት እገዳ ነው [እነዘላለም ረድኤት እንደለመዱት የዐይን ብርሃናቸው በዕርግናም በሕመምም የቀነሰውን ሊቀ ጳጳስ አሳስተው አስፈርመው ካላሰጡት በቀር]፡፡
His Hoiliness Abune Mathias
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ
የቤተ ክርስቲያናችንን ዶግማ፣ ሥርዐትና ትውፊት መጠበቅን ከዐበይት ዓላማዎቹ አንዱ ያደረገውየነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበር÷ የቤተ ክርስቲያናችንን ኦርቶዶክሳዊ ማንነት ለማጥፋትና ተቋማዊ አንድነቷን ለማፈራረስ የሚያሤሩትን የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ ከማጋለጥ አንጻር፣ ”Normal Theology”ን የተሻገረ፣ ዘመኑን የዋጀ የዕቅበተ እምነት/ዐቂበ ሃይማኖት(Apologetic) አገልግሎት በስፋት እንደሚፈጽም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩን ጨምሮ የሥራ ፍሬውን የሚያውቁ ወገኖች ሁሉ ተስፋ ያደርጉታል፡፡ እንደ ቀድሞው ፓትርያሪክ ሁሉ የምሩቃን ማኅበሩን በበላይ ጠባቂነት ሊንከባከቡ ቃል የገቡት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ በቅርቡ የማኅበሩን አመራሮች ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ‹‹በርቱ! ተሐድሶን ተዋጉ›› በማለት አባታዊ ምክርና ማበረታቻ እንደሰጧቸው ተዘግቧል፡፡
በባሕር ማዶ 108 ያህል ምሩቃን እንደሚኖሩ የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበሩ ባለፈው ዓመት ሪፖርቱ ገልጧል፡፡ ከእኒህም ውስጥ 51 በአሜሪካ፣ 29 በአውሮፓ፣ 11 በካናዳ፣ 11 በአፍሪካ እና አንድ፣ አንድ ተመራቂዎች በሕንድ፣ በእስራኤል፣ በኒውዝላንድ፣ በቻይና፣ በደቡብ ኮርያና በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ቀደም ሲል በአህጉረ ስብከት ደረጃ የተገለጸውና አሁን ደግሞ በባሕር ማዶ የተመለከተው የኮሌጆቹ ምሩቃን የሓላፊነት ደረጃና ስምሪት ሲታይ የምሩቃኑ ማኅበር በአሐቲ ቤተ ክርስቲያን መርሕ የሚያበረክተውን አገልግሎት በመላው አገሪቱና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋትና ለማጠናከር እንደሚያስችለው ታምኖበታል፡፡
ባለፈው ዓመት ጥር ወር በአዲስ አበባ በተካሄደው የኦርየንታል አብያተ ክርስቲያንና የሮም ካቶሊክ የነገረ ሃይማኖት ውይይት ወቅት ለአኀት አብያተ ክርስቲያን አባቶች የበኩሉን አቀባበል አድርጓል፤ ስለ ህልውናውና ዓላማው ሰፊ ገለጻ በመስጠት ግንዛቤ መፍጠሩም ተዘግቧል፡፡ በዚሁ አጋጣሚም የኦርየንታል አብያተ ክርስቲያን የነገረ መለኰት ምሩቃን የጋራ መድረክ በሚፈጠርበትና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከማጽናትና ከማስፋፋት አንጻር ሐዋርያዊ አገልግሎት በአንድነት በሚጠናከርበት፣ የቤተ ክርስቲያናችን የነገረ መለኰት ምሩቃን በአኀት አብያተ ክርስቲያን የቴዎሎጂ ኮሌጆች የከፍተኛ ትምህርትና ሥልጠና ዕድል በሚያገኙበት፣ የእርስ በርስ ልምድ ልውውጥ በሚዳብርበት ኹኔታ ላይም የሐሳብ ልውውጥ አድርጓል፡፡
ከዚህ የውጭ ግንኙነት ጋራ በተያያዘ ማኅበሩ በቀጣይ ከያዛቸው ዕቅዶች መካከል÷ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሚመለከተው አካል ጋራ በመተባበር እጅግ አነስተኛ የኾነው የምሩቃን ደመወዝ እንዲሻሻል፣ በተለይም በዕጣ በተመደቡበት ጠረፋማና በርሓማ አህጉረ ስብከት የሚያገለግሉ የነገረ መለኰት ምሩቃን፣ በግብጽ – ኮፕት ኦርቶዶክስ እና በሕንድ ኦርቶዶክስ አኀት አብያተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ኮሌጆች የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ አንዱ መኾኑ ተመልክቷል፡፡
የምሩቃን ማኅበሩ÷ በተደለደሉበት አህጉረ ስብከት ችግሩን ሁሉ ተቋቁመው ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚደክሙ አባላቱ የተመጣጠነ በጀት እንዲተከልላቸው፣ በተከታታይ ትምህርትና ሥልጠና አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ዕድል ማመቻቸቱ የሐዋርያዊ ተልእኮውን ቀጣይነት ከማረጋገጥ አንጻር ሊበረታታ፣ ሊደገፍ የሚገባው ነው፡፡ ከዚህም ጋራ ደግሞ ‹‹የተሐድሶ ኑፋቄን ተዋጉ›› የሚለውን ፓትርያሪካዊ ምክርና ማሳሰቢያ፣ ሕገ ወጥ ቡድኖችና የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞች በውስጥና በውጭ ተሳስረውና ተመጋግበው የሚፈጽሙትን ሤራ ባፍም በመጣፍም በማጋለጥና በማክሸፍ እንዲተገብረው ያስፈልጋል፡፡Untitled-30


Source: ሐራ ዘተዋሕዶ ብሎግ

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment