| የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ለዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ነዋሪዎች በሙሉ! |
ዋልድባ ገዳም በሰሜን ኢትዮጵያ በቀድሞው የጎንደር ክፍለ ሀገር ወይም በአሁኑ በአማራና በትግራይ ክልሎች አዋሳኝ የሚገኝ በመጀመሪያ በኢየሱስ ክርስቶስ የስደት ዘመን በእርሱ በራሱ የተባረከና በኋላም በ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በእርሱ በጌታ መሥራችነት የድንጋይ ቆብ ቀርጾ ባመነኮሳቸው መነኮሳት አፅናነት የተመሰረተ ታላቅና ታሪካዌ ገዳም ነው፡፡እመቤታችን ከልጇ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመዋዕለ ስደት ወቅት በኪደተ እግር ከረገጧቸው መካናት አንዱ ሲሆን፣ የእመቤታችን ስም የሚያመሰግኑ ቅዱሳን እንደ አሸን የሚፈሉበት ቦታ መሆኑንም ለእመቤታችን ትንቢት የተናገረው እዚሁ ገዳም ነው፡፡
ይህ ገዳም በስፋቱ፣በመነኰሳት ብዛቱ፣በፍጹማን ባሕታውያን መሸሸጊያነቱ፣ ለስዉራን ቅዱሳን መናኸርያነቱ፣ በበረሃነቱና በመሳሰሉት ሁኔታዎች በኢትዮጵያ ካሉት ገዳማት ታላቁ ገዳም ሲሆን፣ በዓለም ደረጃም ሲታይ ከግብጹ አስቄጥስ ገዳም ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ጥንታዊና ታሪካዊ የቅዱሳን በአት ነው፡፡በአሁኑ ሰአት የተሰወሩ ቅዱሳንን ሳይጨምር ከ3000 በላይ መነኰሳት በቋሚነት ለመላው ዓለምና ለአገራቸው ቀን ከሌሊት ስብሐት ወአኮቴት ወደ አምላካቸው የሚያቀርቡበት ቦታ ነው፡፡
በዚህ ገዳም እልፍ አእላፍ የተሰወሩ መናንያን እንዳሉ በአንድ ወቅት የግብፅ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ ስለተሰወሩ መነኮሳት ተጠይቀው የሰጡትን መልስ ማንሳቱ በቂ ነው፡፡እንዲህ ነበር ያሉት፤ "ግብፅ ውስጥ የማይታወቅ (የተሰወረ) መነኩሴ በአሁኑ ጊዜ የለም፤ ኢትዮጵያ ብትሄዱ ግን ብዙ የተሰወሩ መናንያንን ታገኛላችሁ" ነበር ያሉት፡፡እነዚህ የዋልድባ መነኰሳት የሚመገቡት ጌታ የባረከላቸውን በቀን አንድ ጭብጥ ቋርፍ ሲሆን፣ የዓመት ልብሳቸውንም የሚሸፍኑት ከበጎ አድራጊ ምእመናን ከሚያገኙት ስጦታ ነው፡፡ ታዲያ በዓይን የማይታይ ምግብ ይሁን እንጂ ሰማያዊውን ምስጋና እየተመገቡ ፀባ አጋንንቱን፣ ግርማ አራዊቱን በተለይም አንድ ቀን ለመዋል እንኳ የሚከብደውን ያን ከባድ የበረሃ ዋዕይ ታግሰው ለራሳቸውና ለዓለም ድህነትን (ህ ይዋጣል) ሲለምኑ ኖረዋል ፣እየኖሩም ነው፣ይኖራሉም፡፡
የዋልድባ ገዳም እንዲህ በቀላሉ ዘርዝረን የማንጨርሰው ብዙ ታሪክና ቃልኪዳን ያለው ቦታ ነው፡፡ጌታም ዋልድባን "እህልና ኃጢያት አይሻገርብሽ"ብሎ ለመናንያን መጠጊያና የምስጋና ማቅረቢያ ቦታ እንድትሆን ምግባቸውም መራራው ጣፋጭ እንዲሆን በቦታው ተገኝቶ ባርኮላቸዋል፡፡በዚህም ምክንያት ላለፉት እስራ ምእት (2000 ዓመታት) ለገዳሙ መነኰሳት ምግብነት ከተፈቀደው የሙዝ ተክል ውጭ ምንም አይነት እህል መሬቱን ሳይደፍር ቃልኪዳኑ ተጠብቆ እስካሁን ቆይቷል፡፡





