‹‹እናንተ ደፋሮች ይህን ጉዳይ ብላችሁ የአንድን ሀገር መሪ ልታናግሩ መጣችሁ ›› ለዋልድባ ገዳም መነኮሳት ከ4ኪሎ ቤተመንግስት የተሰጠ ምላሽ
(አንድ አድርገን የካቲት 28 ፤ 2004ዓ.ም)፡- ከቀናት በፊት በዋልድባ ገዳም አካባቢ መንግስት ላሰበው ትልቅ የስኳር ፋብሪካ ለማቋቋም ስራውን መጀመሩን አስመልክቶ የገዳሙ መነኮሳት ጥያቄያቸውን ይዘው ወደ ጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ(ቤተመንግስት) መምጣታቸውን ከደጀ ሰላም ፤ እና ከተለያዩ ጋዜጦች ላይ አንብባችሁ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ የተባለው ስኳር ፋብሪካን ለመገንባት ብዙ አብያተክርስትያናት እንደሚፈርሱ ለገዳሙ መነኮሳት መረጃ ደርሷችዋል ፤ መንግስት የሚለው ነገር ‹‹ተለዋጭ ቦታ ይሰጣችኋል መንግስት ተለዋጭ ቦታ ሳይሰጥ ምንም አይነት የቤተክርስትያኗ ቦታ ለልማት አያውልም ›› የሚል ሲሆን ፤ መነኮሳቱ ‹‹እኛ ከአባቶቻችን የተረከብነውን የቤተክርስትያ ቅዱሳት ቦታዎችን በገንዘብ እና በሌላ ተለዋጭ ቦታ አንለውጥም›› የሚል ነበር፡፡ እውነት ነው ይህ የቤተክርስትያኗ የእምነት ቦታ በምንም አይነት አላፊ እና ጠፊ በሆነ ነገር አንለውጥም ፤ ደብረሊባኖስ ገዳም እና አካባቢው ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለኃይማኖት በህይወት በኖሩባቸው 98 ዓመታት ብዙ ገቢረ ተዓምራትን በእግዚአብሔር ረዳትነት ያደረጉበት እና እኛም ቦታውን ረግጠን ፤ ቤተክርስትያኗን ስመን ፤ ቦታው ላይ የፈለቀውን ጸበል ጠጥተን እና ተጠምቀን ከስጋ በሽታችን እንድንፈወስ ለእኛ ለሃጥያተኞቹ የተሰጠን ድንቅ ቦታ ነው፡፡ መንግስት እያለ ያለው ይህን የመሰለውን በዋልድባ አካባቢ የሚገኙትን የቅዱሳን ቦታዎችን በሌላ ቦታ ልቀይራችሁ ተመጣጣኝም ብር ልስጣችሁ ነው የሚለው፡፡









