- ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ በኮሚቴው ስብሰባ አልተገኙም
- ቅ/ሲኖዶሱ የኮሚቴውን ሊቃነ መናብርት ሠይሟል
- በኮሚቴው እና በቅ/ሲኖዶሱ ሥልጣን መካከል ጥያቄዎች ተነሥተዋል
- ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ወደ ዋና ጸሐፊነት ሓላፊነታቸው ተመልሰዋል
ቅ/ሲኖዶስ ለ፮ኛው ፓትርያሪክ ምርጫ የሠየመው አስመራጭ ኮሚቴ የመጀመሪያ ስብሰባውን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አካሄደ፡፡ የኮሚቴው ቀዳሚ ስብሰባ የተካሄደው ኮሚቴው በአወዛጋቢ ውሳኔ ታኅሣሥ 6 ቀን 2005 ዓ.ም ከተሠየመ ከአንድ ወር በኋላ በእጅጉ ዘግይቶ ነው፡፡ የመዘግየቱ መንሥኤ ከምርጫው በፊት ለዕርቀ ሰላሙ ፍጻሜ ቅድሚያ ከመስጠት፣ ውጤቱን ከመጠበቅና ለውጤቱ ከመሥራት አኳያ በቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ላይ በታየው ከፍተኛ ውዝግብ ምክንያት ነው፡፡
ጥር 6 ቀን 2005 ዓ.ም የቅ/ሲኖዶሱ አስቸኳይ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ሲጀመር በሚበዙት አባቶች ከፍተኛ ድጋፍ የተሰጠው ይኸው የሰላምና አንድነት አጀንዳ በቀጣዩ የስብሰባው ቀን በውጭ ተጽዕኖ ጭምር ከተቀለበሰ በኋላ የዕርቅና ሰላም ጉባኤው ተስፋ ጨልሞ የምርጫው ሂደት እንዲቀጥል ውሳኔ ተላልፏል፡፡