- ጥቂት አማሳኞች በማንጨብጨብ ሲከተሏቸው፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ጨምሮ ብዙኃን ጉባኤተኞች በድንጋጤና በተደምሞ አዳምጠዋቸዋል፡፡ ፓትርያርኩ በቀቢጸ ተስፋ ውስጥ እንዳሉም አመላካች ኾኗል፡፡
- ማኅበረ ቅዱሳን÷ በጉባኤያት፣ በኅትመትና በኤሌክትሮኒክስ የስብከተ ወንጌል ስርጭት፣ በቅዱሳት መካናት ልማት፣ በአብነት ት/ቤቶችና በካህናት ማሠልጠኛዎች ድጎማና ሞያዊ እገዛዎች ያከናወናቸው ተግባራት በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት በስፋት ተዳስሰዋል፤ ጉባኤተኞች ማኅበሩ ላስመዘገባቸው የሥራ ፍሬዎች ደማቅ ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡
ዛሬ፣ ጥቅምት ፭ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብሰባ አዳራሽ በተጀመረው ፴፫ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ላይ የጉባኤ መክፈቻ ቃለ በረከት እንዲሰጡ የተጋበዙት ፓትርያርክ አባ ማትያስ፣ ማኅበረ ቅዱሳንን ‹‹የቤተ ክርስቲያን ቅኝ ገዥ›› በማለት ‹‹በቁጥጥር ሥር እንዲውል›› ቅስቀሳ እንዳካሔዱበት ተሰማ፡፡
ፓትርያርኩ የጉባኤ መክፈቻ ‹ቃለ በረከታቸው› ማሳረጊያ ላደረጉት ቅስቀሳ መሰል ንግግራቸው መግቢያ ያደረጉት፣ ‹‹ስለ ቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ኹኔታ ልገልጽ እፈልጋለኹ፤ ይህ ጉባኤ በዓመት አንዴ የሚገኝ ነው፤ ዕድሉ እንዲያመልጠኝ አልፈልግም፤›› በሚል ቃለ አጽንዖት ነበር፡፡
ከዚያም ‹‹ቤተ ክርስቲያናችን በቅኝ ገዥዎች ተይዛለች›› ካሉ በኋላ ‹‹ቅኝ ገዥው ማን ነው?››ሲሉ ጠይቁ፡፡ ምላሹን ራሳቸው ሲሰጡ፣ ‹‹ኹላችኁም የምታውቁት አንድ ማኅበር ነው›› ሲሉ ጠቆሙ፡፡ ‹‹በምን?›› ሲሉ ዳግመኛ ጠየቁና ‹‹በገንዘብ፤ በራስዋ ገንዘብ፤ ይኼን እንድታውቁ እፈልጋለኹ›› ሲሉ መለሱ፤ ‹‹እኔ ይኽን ጉዳይ ከራሴ አወርዳለኹ፤ የቤተ ክርስቲያናችን ገንዘቧ፣ ክብሯ ተወስዷል፤›› በማለትም አስረገጡ፡፡
በአምናው ዓመታዊ ስብሰባ፣ ‹‹ማኅበሩ በቁጥጥር ሥር እንዲውል›› አጠቃላይ ጉባኤው ውሳኔ አሳልፎ ነበር ያሉት ፓትርያርክ አባ ማትያስ፣ ‹‹ገንዘቡ፣ ንብረቱ በቁጥጥር ሥር እንዲውል የወሰናችኁት አንድም አልተፈጸመም፤ እነርሱም ፈቃደኛ አልኾኑም፤ ማን ጠይቆ?›› ሲሉ ኹኔታው ከአቅማቸው በላይ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
አስከትለውም ‹‹ቤተ ክርስቲያን ከቅኝ ተገዥነት ትውጣ፤ ካህናቱ ከመከራ ይውጡ›› በማለት መልእክታቸውን በማንኛውም ቦታ እንደሚያስተላልፉ ከተናገሩ በኋላ፣ በሓላፊነት የተቀመጡት ‹‹ይህችን ቤተ ክርስቲያን ለመጠበቅ፤ አንዷን ቅድስት፣ ኦርቶዶክሳዊትና ታሪካዊት ቤተ ክርስቲያን ልመራ እንጂ ኹለት ቤተ ክርስቲያን የለችም፤›› ብለዋል፡፡
|
እሾም ባዩ ቄስ ዘካርያስ (ከአጨብጫቢዎቹ አንደኛው) |