/ውሉደ አበው ዘተዋሕዶ/
ቤተ ክርስቲያን ከፓትርያርክ ምርጫና ከአንድነት የትኛውን ልታስቀድም ይገባታል? ስለምን?
ክፍል አንድ
ለሺህ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ የሚለውን የቆየ ብሂል ስንሰማው ወይም ስንናገረው የኖርነው ነውና አዲስ አይሆንብንም። ለፍልጥ ብቻ ሳይሆን ተበታትነው ላሉ የተለያዩ ነገሮች ሁሉ ልጥም ባይሆን በመልክ በመልካቸው አንድነት እንዲቆሙ ለማድረግ የሚያስችል አንድ ማሰሪያ አይጠፋም። የማሰሪያው መኖር አንድነቱን ያጸናዋል። አንድ የሆነ አካል ወርዱም ስፋቱም ርዝመቱም ይታወቃል። ቅርጽና ጠባዩም ይለያል። የአንዱ መኖር የሌላውም የሕልውና መሠረቱ ነውና አንዱ ሌላውን እንደ ዐይኑ ብሌን ይጠብቀዋል። አንዱ ለሌላው ውበቱም ጥንካሬውም ማንነቱም ሥልጣኑም ነው። ከሺሁ መካከል አንድ ስትጎድል የታሰረው ፍልጥ ይላላል። አንዲት ስትጎድል አንድነት አደጋ ላይ ይወድቃል። ስለሆነም አንዲትም ስንኳ እንዳትሾልክ የሁሉም ፍልጦች ሓላፊነት ነው። ካመለጠችና ከሾለከች ግን ሌሎቹም ጠብ ጠብ እያሉ መሹለካቸው አይቀርም። ሰለሆነም አንዷን ማጣት ሁሉንም ከማጣት አይተናነስም። በመሆኑም አንዷ እንዳትነጠል ወይም እንዳትባዝን የሚከፈለው መሥዋዕትነት ሰለሁሉም ተደርጎ ይወሰዳል።
ለዚሀም ነው ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱሰ ክርስቶስ ከመቶ በጎች አንዲት ብትጎድልበት ዘጠና ዘጠኙን ትቶ የባዘነችውን ወይም የጠፋችውን አንዲት በግ ለመፈለግ ከሰማያዊ መንበሩ ከየማነ አብ ከዘባነ ኪሩብወደዚሀ ዓለም የመጣው። መምጣት ብቻ አይደለም ሊነገር የማይችል ግፍ የደረሰበት። የተበደለ እርሱ የካሠም እርሱ በፍቅር ማሰሪያ የተበተኑት ልጆቹን አንድ ለማድረግ ከቤተልሔም እስከ ቀራንዮ የሄደም እርሱ! ክብር እና ምስጋና ይግባውና ከልደቱ እስከ ትንሣኤው የሰበከው ”እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው።” ያለውን ነው። ዮሐ ፲፯፥፲፩። ከጌታችን ጸሎት የምንረዳው ዐቢይ ቁም ነገር አንድነትን መግፋት ከጌታ ፈቃድ ውጪ መሆን ማለት መሆኑን ነው።አንድነት ካለ ሰላም አለ ሰላምም ካለ አንድነት አለ። ሁለቱ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። በምድር ያሉ የሰው ልጆች ያጡት ይኽንን ሰላም ነበረና ከቤተልሔም እስከ ቀራንዮ ከዚያም እስከ ትንሣኤ በጌታችን የተሰበከው እርሱ ነው።
+ ገና በትንቢት ሲነገርለት የሰላም አለቃ ተብሎ ተጠርቷል። ኢሳ ፱፥፮።
+ በተወለደም ጊዜ የሰማይ መላእክት በምድር ካሉ አረኞች ጋር “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ-በሰማይ ለአግዚአብሔር ምስጋና፣ በምድርም ሰላም፣ ለሰው ልጆችም በጎ ፈቃድ” ብለው ዘምረዋል። ሉቃ ፪፥፲፬።
+ የመጣው ሰላሙን ሊተውልን ሰላሙን ሊሰጠን መሆኑንም ነግሮናል። ዮሐ ፲፬፥፳፯።
+ በቀራንዮ አደባባይ እንደ ብራና ተወጥሮ በመልእልተ መሰቀል ላይ ሆኖም ያደረገው ታርቆ በማሰታረቅ ሰላምን መስጠት ሰላምን ማድረግ እንደሆነ ተነግሮናል። ገብረ ሰላመ በደመ መስቀሉ እንዲል። ቆላ ፩፥፳።
+ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በገዛ ሥልጣኑ ሞትን በሞቱ ሽሮ ለቅዱሳን ሐዋርያት ሲገለጥላቸው “ሰላም ለሁላችሁ ይሁን” እያለ ነው። ዮሐ ፳፥፲፱።
በጥቂቱ ከአነዚህ የመጽሐፍ ክፍሎች ስንነሣ ጌታችን ከቤተልሔም እስከ ቀራንዮ የሰበከው ሰላምን ተፋቅሮን እርቅን መሆኑን ማበል አይቻልም። የቤተ ክርስቲያን የአንድነት ልጥ ሰላም ነውና። ሰላም ስንል በቤተ ክርስቲያን አባቶች አና አባቶች፣ ወንድሞች እና እኅቶች፣ አባቶች እና ልጆች መካከል ሊኖር ስለሚገባውማለታችን መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አባቶች መካከል ለሃያ አንድ ዓመታት የኖረው መቋሰል እና መቆራቆስ አሁንም አነጋጋሪ አንደሆነ ይገኛል። በዚህ ወቅት እነማን ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ክብር እንደቆሙ፣ እነማን ደግሞ ከቤተ ክርሰቲያን ይልቅ ለሆዳቸው፣ ለፍቅረ ሢመታቸውና ለግትርነታቸው ዘብ እንደሆኑ ለማየትም ለመታዘብም ችለናል። የመጀመሪያዎቹ በቁጥር የሌሉ እስኪመሰሉ ድረስ ትንፋሻቸውን እንኳ ጆሯቸው እንዳይሰማባቸው የሚጠነቀቁ፣ በፍርሃት የተሸበቡ ሲሆኑ ሁለተኛዎቹ ደግሞ ከቁጥራቸው በላይ አብጠውና ገንነው ጥቅማቸውን ለማርካት ጠብ ርግፍ እያሉ ናቸው።
የሁለተኞቹ መልካቸው ብዙ ሲሆን የተወሰኑት መለካውያን ወይም ፈጻምያነ ፈቃደ መኳንንት ሲሆኑ ውለው ባደሩ ቁጥር አለቆቻቸውን ምን ደባ በመፈጸም እንደሚያሰደስቱ የሚጨነቁ ናቸው። ወንድሞቻቸውን አንኳ ሰውተው ቢሆን አለቆቻቸውን በማስደሰት ተደላድለው ለመኖር የሚቋምጡ በየሥራ ቦታቸው ያለባቸውን የሥራ ድክመት እና ሌላ የጉድ ጅራት ለማለባበስ ስተው በማሳሳት የተሰማሩ ናቸው። የተቀሩት ደግሞ በፍርሃታቸው እምነታቸውን አስጨንቀው አስረው ወደሞቀበት እየደነበሩ አቧራ የሚያስነሱ ገላግልት ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ በዐይነ ስውር ቤት አንድ ዐይና ብርቅ ነው እንዲሉ ጥቂት የማንቆለጳጰስ ሥራ እንዲሠሩ የተመደቡ በቻሉት አጋጣሚ የእርቁ ሂደት ወማ እንዲበላው የሚጋረፉ የስድብ አፍ የተሰጣቸው ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ፈርተው የሚያስፈሩ ደንግጠው የሚያስደነግጡ ደንብረው የሚያስደነብሩ የፍርሃት መንፈስን የተቀቡ የአበው በረከት የተለያቸው እንደ እሽኮኮ ዘወትር በስጋት የተወጠሩ ናቸው።
እንዲህ እና እንዲያ እያልን ብንፈነካክታቸው ብዙ ቁርጥራጮች ይወጣቸዋል እንጂ ወጥነት አይገኝባቸውም። እነርሱን ግን አንድ ነገር አገናኛቸው እንጂ ስምምነት እንደሌላቸው ሩቅ ሳንሄድ የተንገበገቡለት ምርጫ ደርሶ ብትንትን ብለው ዞረው የእርስ በእርስ የጦር ዐውድማ ላይ ሲተጋተጉ ማየታችን አይቀርም። ሌቦች ሲሰርቁ ተስማምተው ሲከፋፈሉ ተጣልተው ይላል የአገራችን ሰው።
እንደነዚህ ያሉ ማሽንክ አስተሳሰብ ያላቸው መንፈሳውያን መሳይ ያሉትን ያኽል ደግሞ እስከ መጨረሻው ለማተባቸው የታገሉ መኖራቸውን አንክድም። በዚህ ጎራ ያሉት በሁለት መልክ የሚታዩ ናቸው። እስከመጨረሻዋ ሰዓት ለእርቀ ሰላሙ ቅድሚያ ይሰጥ በሚለው የጸኑ፣ ቁጥራቸው ቢያንስም መዓዛቸው ከሩቅ የሚጣራ ዉሉደ ሰላም ናቸው። ባልተሸራረፈ ጽናታቸው ትውልዱም ታሪክም በወርቅ ቀለም የጻፋቸው በረከተ አበው የደረሳቸው ጀግኖች ናቸው። በሌላ በኩል ያሉት ደግሞ መጋፈጡን ችላ ብለው ግን እርቀ ሰላሙ ይቅደም የሚለውን ከመደገፍ የማያባሩ አባቶች ናቸው። እንደ መጀመሪያዎቹ ፊት ለፊት ሲታገሉ አልታዩ ወይ አልተሰሙ ይሆናል እንጂ ድምፃቸውን ለቤተ ክርስቲያን አንድነት የገበሩ በመሆናቸው ሳናመሰግናቸው አናልፍም። ስለነዚህ አባቶች ስንናገር ግን እንዲያ ወይም እንዲህ ማለት ወይም ማድረግ ነበረባቸው እያልን አንገት እንዳናስደፋ ልንጠነቀቅላቸው ይገባል። በዙሪያቸው ያለውን እንቅስቃሴም መረዳት ግድ ይላልና።
ማንም በአንድ ቀን የታጠበ አና የጸዳ ሊሆን ከባድ ነውና ከነባራዊው ሁኔታ ተነሥተን የደረሱበትን ተረድተን ከጎናቸው ልንቆምላቸው ይገባል። የፍጹማንን ሥራ ከእነርሱ በመጠበቅ ብቻ የድርሻችንን ሳንወጣ እንዳንቀር ደጋግመን ማሰብ ይጠበቅብናል። ሳኦል እያለ ብላቴናውን ዳዊትን ያሰነሣውን አምላክ የምናምን ነንና። ብርቱዎቹ እያሉ በደካሞቹ ሥራ መሥራት ልማዱ የሆነ ጌታ በተናቁት የሚሠራውን ማን ያውቃል? ስለሆነም የምናውቀውን አምላክ እንደማናውቀው ሁሉ በአመክንዮአዊ አካሄድ ተስበን አባቶች ዝም ያሉትን እኛ ምን ልናደርግ እንችላለን? በማለት ተስፋ አንቁረጥ።
ነቢዩ ዳንኤል እያለ በሠለስቱ ደቂቅ ሥራውን የሠራ ፈጣሪ፣ ባርቅ፥ ዛብሎንና ንፍታሌም እያሉ ዲቦራን ያሥነሳ እግዚአብሔር፣ ቅድስት እየሉጣ ሳለች በሕፃኑ ቂርቆስ ሰማዕትነት የተመሰገነ ጌታ፣ ሊቃውንቱ እያሉ ዓሣ አጥማጆችን የጠራ መድኃኔዓለም በማን አድሮ ምን እንደሚያደርግ ማን ያውቃል? በእርሱ ዘንድ የተናቀው ልቡ የደነደነ እያወቀ የማያውቀው እንጂ የልብ ንጽሕና ካላቸው ዘንድ መቼ ርቆ ያውቅና።
እውን ዛሬ ለምናያት ቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋት የትኛው ነው? የፓትርያርክ ምርጫ ወይስ ዕርቅ
አባቶቻችንን እንዲህ ከፋፍለን እንድናያቸው ያደረግን ሌላ ሳይሆን ለእናት ቤተክርስቲያናችን አንገብጋቢ እና ጊዜ የማይሰጥ ችግሯ እየሰጡት ያሉት ምላሽ እንደሆነ ግልጽ ነው ብለን እናምናለን፡፡ሰው ያልበላውን ቢያኩለት እንዴት መፍትሔ ሊሆነው ይችላል? እንዲያውም ያልበላውን ያከኩ ጊዜ ሌላ ሕማም ወይም ስቃይ ጨመሩለት እንጂ እንዴት መድኃኒቱ ይሆናል? እግሩ ቆስሎ ሐኪም ቤት የሄደን ሰው እጁን ቢዳስሱለት ምን ይበጀዋል? ወይስ ዐይኑን ለታመመ ወገቡን ቢያክሙት ምን ይጠቅመዋል? ይህንን ጌታችን በወንጌል እንዲህ ሲል ገልጦታል። አባት ከሆናችሁ ከእናንተ ከማንኛችሁም ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ እርሱም ድንጋይ ይሰጠዋልን? ዓሣ ደግሞ ቢለምነው በዓሣ ፋንታ እባብ ይሰጠዋልን? ሉቃ ፲፩፥፲፩። የሚያስፈልገው ሌላ የተሰጠው ሌላ። መፍትሔው ሌላ በመፍትሔነት የቀረበው ደግሞ ሌላ። ዓሣ መፍትሔው ሲሆን የሚሰጠው እባብ ከሆነ ሰጪውስ ሰጪ ነውን?
ቅድስት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ያዘነችበት የተጎዳችበት ዋና ጉዳይ እያለ እርሱን ሁለተኛ ወይም መጨረሻ አድርጎ በመመልከት ቤተ ክርስቲያን እፎይታ ልታገኝ አትችልም። ዓሣ ስትጠይቅ እንዴት እባብ እንሰጣታለን? ባጎረሰች እንዴት ትነከሳለች። ለመሆኑ ለወቅታዊው የቤተ ክርስያን ችግር ትክክለኛው መፍትሔ የቱ ነበር? ምንም እንኳ ሂደቱ ከፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ነጻ ነው ለማለት ባይቻልም ከላይ እንደገለጽነው የአባቶቻችን ልዩነት ጎልቶ የወጣው ለዓሣው ጥያቄ ምላሹ እባብ ሆኖ በቀረበው የፓትርያሪክ ምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ በአንደኛ ወገን ያሰቀመጥናቸው ወገኖች እርቀ ሰላሙ እየቀጠለ ነገር ግን ያለምንም መዘግየት የፓትርያሪክ ምርጫ መካሄድ አለበት ሲሉ ሁለተኞቹ ምናልባትም ድምፃቸው ባልፈለጉት መንገድ የታፈነባቸው ደግሞ ያልታረቀች ቤተ ክርስቲያን እንዴት ለሹመት ትጣደፋለች በማለት ልዩነታቸውን ቢያስቀምጡም ለጊዜውም ቢሆን የመጀመሪያዎቹ ያሸነፉ በሚመስል መልኩ የብዙዎቹን ፍላጎት እነደረመጥ በማዳፈን የምርጫ ሽርጉዱ ተጀምሯል፡፡
ለመሆኑ የየትኛው ወገን አስተሳሰብ ሊደገፍ ይገባዋል?
ይቆየን፡፡
Source: http://haratewahido.wordpress.com/
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment