- ለአቡነ ሳሙኤል የተካሄደው የጠቋሚዎች ዘመቻ የኮሚቴውን አባላት አስጨንቋል
- በቡድን የተሰጡ ጥቆማዎች ተቀባይነት አላገኙም
- ዕጩዎችን ለመለየት ከምርጫ ሕገ ደንቡ በተጨማሪ አለ የተባለው አሠራር አነጋግሯል
- ከሀገር ውጭ ስምንት አህጉረ ስብከት መራጭ ተወካዮቻቸውን ይልካሉ ተብሏል
- ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ በኮሚቴው አባላት መካከል ተገኝተዋል
የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ዛሬ፣ የካቲት ስምንት ቀን 2005 ዓ.ም ከቀኑ 10፡00 ላይ ሁለተኛ ዙር ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም ከተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ በተለየ አኳኋን በሦስት ዙር ከጋዜጠኞች ለቀረቡት በርካታ ጥያቄዎችም የኮሚቴው አባላት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ኮሚቴው በመግለጫው እንዳመለከተው፣ ካህናትና ምእመናን ስድስተኛው ፓትርያሪክ ይኾናል የሚሉትን አባት በአካልና በፋክስ እንዲጠቆሙ በተላለፈው መልእክት ከየካቲት 1 – 8 ቀን 2005 ዓ.ም በርካቶች ጥቆማቸውን ሰጥተዋል፡፡ ‹‹መላው የቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን የቤተ ክርስቲያንን ድምፅ ሰምተን ጸሎታችንን ለፈጣሪያችን በማቅረብ ላይ ነን›› ያለው መግለጫው በቀሪው ጊዜ በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ጸሎቱ የምርጫው ሂደት እስከሚጠናቀቅ ድረስ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ካህናትንና ምእመናን አሳስቧል፡፡
የካህናቱና ምእመናኑ ጥቆማ የመስጠቱ የጊዜ ሰሌዳ በዛሬው ዕለት ከ10፡00 በኋላ የተጠናቀቀ ሲኾን ከነገ የካቲት 9 ቀን ጀምሮ እስከ የካቲት 14 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ዕጩዎችን የካቲት 16 ቀን 2005 ዓ.ም ለሚካሄደው ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለማቅረብ አስመራጭ ኮሚቴው ውይይቱን እንደሚቀጥል በመግለጫው ላይ ተመልክቷል፡፡ ኮሚቴው ለዕጩዎች ልየታ በሚያካሂደው ውይይት ከካህናትና ምእመናን የተሰጡ ጥቆማዎችን በግብአትነት ብቻ እንደሚጠቀምበት ነው የገለጸው፡፡
መላው የኮሚቴው አባላት በተገኙበት የተሰጠው ሁለተኛ ዙር መግለጫ፣ በሰብሳቢው ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ከተነበበ በኋላ ከጋዜጠኞች ጥያቄዎች ተሰንዝረዋል፡፡ ጥያቄዎቹ ጠቅለል ተደርገው ሲታዩ÷ የምርጫው ሂደት የተለያየ ፍላጎት ካላቸው አካላት ተጽዕኖ የጸዳ ስለመኾኑ፣ ኮሚቴው የተሰጡ የካህናትና ምእመናን ጥቆማዎችን በግብአትነት ብቻ የሚጠቀምና የራሱን ተጨማሪ አሠራሮች የሚከተል በመኾኑ የጥቆማው ፋይዳ ምን ያህል እንደኾነ፣ ስለ ጥቆማ መስጠቱ ያልሰሙ፣ መረጃው ያልደረሰባቸው አህጉረ ስብከት እንደሚበዙና እንቅስቃሴው በአዲስ አበባ የተገደበ ስለመኾኑ፣ ይህም በቀጣይ ኮሚቴው መልእክቱን ለካህኑና ምእመኑ ለማድረስ ያለበትን ውስንነት እንደሚያሳይ፣ በኮሚቴው የዕጩ ልየታ ሂደት ለዕጩ ፓትርያሪክነት መስፈርቱን ያሟሉት አባቶች ከአምስት የሚበልጡበት ኹኔታ ቢኖር እንዴት ወይም በምን አሠራር ይጣራሉ/ይወዳደራሉ፤ በጥቆማው ስለተሳተፈው ሰው ብዛት መረጃው ይታወቃል ወይ፤ በፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቡ የተለዩ ዕጩዎችን መረጃ ለሕዝብ ይፋ በማድረግ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን ለመቀበል የሰፈረው ድንጋጌ በኮሚቴው የጊዜ ሰሌዳ ለምን አልተከበረም ወይስ ተለዋጭ አሠራር ተዘርግቷል ወይ፤ በምርጫው እንደሚሳተፉ የተገለጹት መራጮች ብዛት 800 ነው – ትክክለኛ ስሌት ነው ወይ፤ ይህ አኀዝ ከዚህ በፊት በተከናወኑት ፓትርያሪኮች ምርጫ ከተሳተፈው መራጭ በእጅጉ እንደሚበልጥ የተደረገው ንጽጽር በሦስተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ምርጫ ጊዜ ከተመዘገበው 1133 መራጭ (990 ተሳትፈዋል ተብሏል) የሚያንስ በመኾኑ መረጃው ትክክለኛ ነው ወይ የሚሉ ናቸው፡፡
ጋዜጣዊ ጉባኤው በአቶ ባያብል ሙላቴ የተመራ ሲኾን ለጥያቄዎቹ ምላሽ በመስጠት በዋናነት÷ የኮሚቴው ዋና ጸሐፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ፣ የኮሚቴው የሚዲያና ሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ አቶ ባያብል ሙላቴ፣ የኮሚቴው ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ የኮሚቴው አባላት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፣ መልአከ ሰላም ዓምደ ብርሃን ገብረ ጻድቅ፣ ቀኝ አዝማች ኀይሉ ቃለ ወልድ ከእነርሱም ጋራ በመግለጫው ላይ የተገኙት ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል እየተፈራረቁ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ኮሚቴው የተለያየ ፍላጎት ካላቸው አካላት ተጽዕኖ ምን ያህል ነጻ ነው ለሚለው ጥያቄ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ በሰጡት ምላሽ÷ እኛ እስከምናውቀው ድረስ ይህ ዓለማዊ ምርጫ አይደለም፤ እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማገልገል የሚካሄድ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ምርጫ ነው፤ ምንም ዐይነት ተጽዕኖ የሌለበት፣ ከምንም ዐይነት ተጽዕኖ የጸዳ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ብቻ ተብሎ የሚካሄድ ምርጫ ነው ብለዋል፡፡ የኮሚቴው አባል ቀኝ አዝማች ኀይሉ ቃለ ወልድ በበኩላቸው፣ የምርጫው ሂደት በቀኝም በግራም ከማንኛውም አካል ተጽዕኖ የለበትም፤ ይህን ላረጋግጥላችኹ እወዳለኹ በሚል አጽንዖት ተናግረዋል፡፡
የዜናው ዝርዝር ይቀጥላል
Source: http://haratewahido.wordpress.com/
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment