Wednesday, February 13, 2013

ሩጫው ማንን ለመቅደም ነው?


ከውሉደ አበው ዘተዋሕዶ
Patriarchal competition
የፕትርክናው መንበር
አሁን ፮ኛውን ፓትርያርክ ለመምረጥ የሚካሄደው ሩጫ እጅግ አስገራሚ ይመስላል። ምክንያቱም፣
፩. በርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ምእመናን እና የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ያገባኛል ብለው ቆርጠው የተነሡ የጡመራ መድረኮች ከምርጫው በፊት እርቀ ሰላም ይቅደም የሚለውን ፍጹም ክርስቲያናዊ አካሄድ በመደገፍ የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ባለበት ወቅት
፪. በራሳቸው ተነሳሽነት የማንንም ጉትጎታ ሳይፈልጉ አባቶች እንዲታረቁ እናም አንድ እንዲሆኑ ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውን እና ውድ ጊዜያቸውን በማበርከት ቀንና ሌሊት ሲለፉ የቆዩት የአስታራቂ ሽማግሎች “የእባካችሁ ታረቁልን” ልመና ባልቆመበት ወቅት
፫. የተለያዩ የአብያተ ክርስቲያናት እና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ጥምረቶች ከፓትርያርክ ምርጫ ይልቅ ታርቃችሁ እንያችሁ እያሉ የተለያየ ተማኅጽኖ እያሰሙ ባሉበት ጊዜ
፬. ከራሳቸው ከአባቶች መካከል የተወሰኑት ሳንታረቅ የምን ፓትርያርክ እያሉ በሚቃወሙበት ሰዓት


ካልመረጥን ሞተን እንገኛለን በሚል አካሄድ ተጸምደው ሩጫቸውን እያፋጠኑ መሆኑ ለተመልካች እጅግ አድርጎ ይገርማል። ምነው ይኽንን ሩጫ ለስብከተ ወንጌል፣ አብነት ትምህርት ቤቶችን ለማስፋፋት እና ለማስፋት፣ ገዳማቱ ከእነ ሙሉ ክብራቸው እና ማንነታቸው ተከብረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ፣ መናፍቃን ከቤተ ክርስቲያን እንዲወገዱ ለማድረግ፣ በቤተክህነት መዋቅር ቤቱን ሠርቶ እግሩን ዘርግቶ የተንሰራፋውን ሙስና ለማጥፋት፣ ለጾምና ለጸሎት…ወዘተ ለመሳሰሉት ክርስቲያናዊ ተግባራት ባሳዩት ኖሮ!
እንሩጥ ካልን ለምን መሮጥ እንዳለብን ተነግሮናል። “እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።” ዕብ ፲፪፥፩−፪። እንግዲያውስ የከበንን ኃጢአት ለማስወገድ ያለብንን ሸክም ለማራቅ እንሩጥ እንጂ እርቅን ለመግፋት አይሁን።
የሐዋርያው ሩጫ ስለ ስብከተ ወንጌል መሆኑን እና እኛም መሮጥ የሚገባን ለዚያው መሆኑን ነገሮናል። “በወንጌልም ማኅበረተኛ እሆን ዘንድ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ። በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት፥ ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ።”  ፩ቆሮ ፱፥፳፫−፳፬። ለሲመት አላለም።
ለመሆኑ የሚሾመው ማንን ሊመራ ነው?
፠     መራጭም አስመራጭም ነን የሚሉቱ እነርሱ እስካልመሩት ድረስ የሚመሩለት አይሆኑም። መልሰው በጭንቅላትህ ላይ ካልተቀመጥን ባዮች ናቸው። የመረጡት ተመልሰው ጠላት ሲሆኑበት ለማየት ሳምንታት በቂዎች ናቸውና!
፠     ይህ ሁሉ ሊቃውንት እና ምእመናን በየዘርፉ ከምርጫው እርቅ ይቅደም እያለ ጩኸቱን ከዳር ዳር አያስተጋባ የተመረጠ ፓትርያርክ የማን አባት ሊሆን ይችላል?
፠     በውጭ በሚገኘው ሲኖዶስ ሥር ነን ብለው የሚኖሩትስ ምእመናን ለዘለዓለሙ እንዲለዩ ተፈርዶባቸዋልን? መቼም እንደወጡ ይቅሩ ካልሆነ በስተቀር ተመራጩም እንደዚህ ያሉ ምእመናን መኖራቸውን እየሰማ ከማዘን በስተቀር ያውም ጥቂት መንፈሳዊነት ያለው የተገኘ እንደሆን ምን ብሎ ሊመራ ይችላል?
፠     ባለፉት ሃያ አንድ ዓመታት በገጠማቸው የተለያየ ችግር ምክንያት ከዚህም ከዚያም አንሆንም በማለት “ገለልተኛ” በሚል ስም እየተጠሩ ያሉትስ በዚያው እንደወጡ ሊቀሩ ካልሆነ ተመራጩ በምን ሥልጣን ሊመራቸው ይችላል?
ምናልባትም ቀሪ ዘመኑን ሁሉ ስሙ የሚብጠለጠል፣ በየጋዜጣው እና በየመድረኩ እንደተሳቀለ የሚኖር፣ በአደባባይ በኩራት የማይቆም፣ እንደተሸማቀቀ ቀኑን የሚገፋ ሰው ማስቀመጥ ይቻል ይሆናል። እኛ የምንፈልገው በሀገርም በዓለማቀፍ መድረክም በመንፈሳዊነት የሚያኮራን አባት እንጂ በብዙ ለቅሶ እና እንባ ታጥቦ ቤተ ክርስቲያን እያዘነች የሰውን ሁሉ እንባ ገፍቶ በመሾም አንገቱን ደፍቶ አንገት የሚያስደፋንን አይደለም።
ሌላውን ታረቁ ብለው የሚማልዱ እነርሱ አይታረቁምን? ከእንግዲህስ በእርቅ መድረክ ጫፍ ለመድረስ ምን የሞራል ብቃት ይኖራቸዋል? ሐዋርያው “እንግዲህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን? አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን? ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህን? በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታሳፍራለህን? በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና ተብሎ እንደተጻፈ።” ያለው አይተረጎምባቸውምን? ሮሜ ፪፥፳፩-፳፬። ክርስትና የተረት ተረት መድረክ ሳትሆን የተግባር ቤት ናት። የሚናገሩትን መኖርን ግድ ትላለች። ወንጌል ጠባብ አንቀጽ የተባለችውም ለዚሁ ነው።
በሐዋርያው ቃል የማንኖር ከሆንን ሌላውን ታረቁ እያልን የበደላችሁን ሁሉ ይቅር በሉ እያልን መጽሐፍ እየጠቀስን በታሪክ እና በገድለ አበው እያዋዛን የምንሰብክ ያሁሉ በእኛ ሕይወት በተግባር ካልተተረጎመ በእኛ ምክንያት የእግዚአብሔር ስም ይሰደባል። ለስሙ የእግዚአብሔር ነን ይላሉ ነገር ግን ውሸታሞች ናቸው ከመባላችን አልፎ በእኛ ምክንያት እግዚአብሔር የሚሰደብ ከሆነ ሞት ይሻላል። እንዴት በእኛ ምክንያት አምላካችን ይሰደብ? አስተምራለሁ እያሉ የማይማሩ ከሆነ እንግዲህ ምን እንላለን? ሩጫውን ገትቶ በሰከነ ኅሊና በሰቂለ ልቡና ሰለ ቤተክርስቲያን ለማሰብ ዛሬም አልመሸም። ያለዚያ ግን ከፊታችን ለመቆም አይቻላችሁም። የፈጸማችሁት ግድፈት ይቅርታ አይኖረውም። መስቀላችሁ የማን እንደሆነ ስላላወቅን ለመሳለም እንቸገራለን። ለሚያልፍ ስሜታችሁ የማይሽር ጠባሳ በቤተክርስቲያን ላይ እንደ ታርጋ ለጥፋችሁ ዝም የምትባሉ አይምሰላችሁ።
አንቀጸ ብፁዓን እየተባለ በሚጠራው የአምላካችነ የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ውስጥ የሚከተሉት መመሪያዎች ይገኛሉ። “የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፥ ይማራሉና።… የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና።” ማቴ፭፥፯−፱። ምናልባትም ሌሎች በድለዋችሁ ከሆነ ብፁዓን ለመባል የግድ ምሕረት ማድረግ አለባችሁ። እንኪያስ እናንተ ምን እያደረጋችሁ ይሆን? ብፅዕና በከንቱ የሚገኝ አይደለም። ሰዎች በማንቆለጳጰስ ብፁዓን እያሉ ሊጠሩ ይችሉ ይሆናል። ፈታሔ በጽድቅ ጌታችንስ? እንዲሁም የሚያስተራርቁም ባለማዕርግ እንደሆኑ ተነግሮናል። ይቅር ማለትም ይቅረ ማባባልም ለብፅዕና የሚያበቃ ምግባረ ሰናይ ነው። አንታረቅም የሚሉት ደግሞ በተቃራኒው። ኧረ ተው ተገልገሉ ማጣፊያው ይቸግራል አባቶች!
በምድራዊ ፍርድ ቤት ብዙ ማምለጫ ይኖራል። ሰማያዊው ፍርድ ቤት ግን እንዲህ አይደለም። ፈራጆቹም ሥራዎቻችን ግብሮቻችን ራሳቸው ናቸው እንጂ ሌላ አይሆንም። ዛሬ ያልተሠራው ነገ ከየት ይመጣል?
ለመንጋው የማይራራ አባት ከቶ ለማን ይሆናል? መንጋው እየጮኸ የፈለገው ይሁን ሲፈልግ ማኅተቡን ይበጥስ ሲፈልግ ገደል ይገባ እያለ አርዌ ብርት ለመጨበጥ የሚሮጥ እርሱ ከማን ወግኖ ሊቆም ይችላል? እውነተኛ እረኛማ ነፍሱን ስለ በጎቹ አሳልፎ የሚሰጥ ነው። ዮሐ ፲፥፲፩። እንዴት ይህ ሁሉ መንጋ ጥያቄው አይሰማም? በእርግጥ በእነ አፌ ወለፌ ይኽ የብዙዎች ሳይሆን የጥቂቶች ጩኸት ነው እየተባለ ሲነገር ይሰማል። እስኪ መድረኩ ይከፈትና የጥቂቶች መሆን አለመሆኑ ይታይ? ዝም ብሎ ለማድበስበስ በሚደረግ የቃላት ግልምጫ ሳይሆን አብዛኛው ምእመን አንገት የደፋበት ጥቂት የማይባሉት ደግሞ ሃይማኖታቸውን እየተው የተሰደዱበት ጉዳይ ነው። የእነዚህን ሁሉ ደም እግዚአብሔር ከእጃቸው ይፈልግባቸዋል።
ጥር ፴ ቀን ፳፻፭ ዓም የተሰማው ነገር እውን ለቤተ ክርስቲያን የወገነ ነውን? አዚህ ላይ “ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።” ሲል የተናገረውን የመጽሐፍ ቃል ለማስታወስ እንገደዳለን። ሥራ ፳፥፳፱። ስንኳንስ የዚህ ሁሉ ሰው ድምጽ ቀርቶ ከአምስት ገበያ በላይ የሚሆን ሕዝብ በሚጋፋበት በዚያ ስፍራ ጌታችን የአንዲት የተበደለች ሴትን ድምጽ አልሰማምን? ለመንጋው የሚራራው እረኛ እንዲህ የሚያደርገው ነው። ኖላዊ ትጉኅ መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የቁጥርን ብዛት ሳይሆን የአንዲቱን በግ ከመንጋው መነጠል ምክንያት አድርጎ ቃል ሥጋ መሆኑን ለምናውቅ ለእኛ ቁጥር መጥቀሱን ትተው ወደ መስመር ቢገቡ በተሻለ።
የመንጋውን ጩኸት ችላ ማለታቸው ሲገርመን ሩጫቸው ደግሞ የበለጠ አስደመመን። ለምን መሮጥ እንዳለባቸው አያውቁም ወይም አልተጋባባቸውም? ዶሮ ብታልም ያው ጥሬዋን እንደሚባለው ሆነና የሚሰሙት የእነርሱ ብቻ የሆነውን ቅዠታቸውን ብቻ ሆነና እንዴት እንደማመጥ? እውን አበ ብዙኀን አብርሃም አንደተናገረው በእነርሱ እና በእኛ መካከል ያለው ገደል ታላቅ አየሆነ ነው እንዴ?
እስከዛሬ በተለያዩ ስብከቶች የተነሣ የአባቶቼን ገበና አውጥቼ ሰድቦ ለተሳዳቢ አልሰጥም እያለ ታግሶ እና አንገት ደፍቶ እቅፍ ድግፍ አድርጎ የያዘ ምእመን ነበረ። ነገ ተነገበስቲያ ግን ይህንን የምታገኙ አይምሰላችሁ። እሰኪበቃን በመታገስ ከበለስ ወይን ለመልቀም ብዙ ጠብቀናል። የበለሱ መቆረጫ እየደረሰ ይመስላል። እውነተኛው ጉንደ ወይን መተከል ይኖርበታል። ምእመኑ ልብ ገዝቶ ሲገላግል ቆየ ሰሚ አልተገኘም። በለሱን እያየ ተው ወይኑ ይመጣል እያለ ጠበቀ ይባስ ብሎ የጎመዘዘ መርዛማ ሆነ። መርዙን እየበላ የሚጠፋ ይኖራል ብሎ መገመት ከእንግዲህ ያበቃ ይመስላል።
ገዳማችሁን እየተዋችሁ ከእኛ መንደር ጉርብትና ስትመጡ መሬት እየተጋፋችሁ ስትገዙ ይሁን እነርሱም ሰዎች ናቸው እያለን ታገስን። መኪና እያማረጣችሁ የመኪናውን ገበያ ስታጣብቡ ለስብከተ ወንጌል ነው እያልን አሽሞነሞንናችሁ። ጎደለን ባላችሁን ጊዜ ሌላ ሰው አይስማ እያልን ኪሳችንን እያራገፍን አጋደድናችሁ። ይኸኛውን ስታደርጉ ግን እንደምን ዝም እንበላችሁ። እናት ቤተ ክርስቲያንን ለጠላት መሳቂያ እና መሳለቂያ ስታደርጉ እንዴት  በምን አንጀት እንቻለው?
ለመስፍኑ ኢያሱ ያዘቀዘቀችው ፀሐይ ቆማለታለች። ለአባ ዜና ማርቆስ ኢትዮጵያዊ ያችው ፀሐይ ከአቆለቆለች በኋላ ቆማለች። ያም ጠላቶቹን ድል እስኪመታ እኒህም የጌታቸውን ሥጋና ደም ለማቀበል። ለደግ ሥራ መሽቶ አያውቅም። ለሰማዕታትም ጨልሞ አያውቅም። ያለው ጊዜ ሩቅ ለመሄድ ብዙ ነው። በቀረው ጊዜ እግዚአብሔርን ይዘን እንገስግስ! ልብ ያላችሁ ሁሉ እዘኑ። ቅድመ ፈጣሪ የሚደርስ ንጹሕ እንባ አፍስሱ። እግዚአብሔር በአንድ የራሔል እንባ የእስራኤልን ታሪክ ለውጧል። አንዲት ራሔል ካለሽበት እንባሺን ወደ መንበረጸባዖት ርጪ። ኢትዮጵያዬ አልቅሺ። እመ ብርሃን አስራትሺን አትርሺ።
ለምእመናን
ክርስትና ሲመች ሳይሆን በመከራም ጊዜ ቢሆን የሚኖሩት ሕይወት ነው። የምንሰማው እና የምናየው ሊያስበረግገን አያስፈልግም። ክርስተና የሚለካው ከፍ ሲል በተግባር ባሳየን በጌታችን ዝቅ ሲል ደግሞ በቅደየሳኑ እና በሰማዕታቱ ነው። ማነነት የሚለካው በችግር ወቅት ነው። ማመንም የሚገባን በዚህ ወቅት ነው። ክረምት ካልመጣ ሁሉ ቤት እንግዳ ከሌለ ሁሉ ሴት እንዲሉ ሃይማኖት የምትፈተው በጭንቅ ጊዜ ነው። ተስፋ ያደረግናቸው አንገት ቢያስደፉንም በአምላካችን እና በእምነታችን ግን ጨርሶ ተስፋ አንቆርጥም።
ጊዜው ጽናታችን የሚፈተንበት ማንነታችን የሚለካበት ነውና በእድሉ እንጠቀምበት እንጂ ተስፋ በመቁረጥ ወደ ግል ውሣኔ አንገፋፋ። እምነት ለመለወጥ የሚዳዳችሁ ካላችሁ ልክ አይደለምና ታቀቡ። ማመናችሁ ይፈተን ዘንድ በሆነው ነገር ወደ ሌላ ጥፋት እንዳትገቡ አደራ እንላለን። ነቢዩ “ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፥ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራ ሥራ ቢጐድል፥ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፥ በጎች ከበረቱ ቢጠፉ፥ ላሞችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ፥ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ።” ያለው ለዚሀ ነውና። ዕንባ ፫፥፲፯።
አኛ በእርሱ እንመካ። እየተመካን እንጸልይ። እየጸለይን አንድነታችንን እናጠንክር። መልስ ከሰው ጠብቀን ከነበረ ተሳስተናል። መልሱ ፍጹም የሚሆነው ከእግዚአብሔር ከሆነ ብቻ ነው። የማን ማንነት የተገለጠበት ጊዜ ነውና እርስ በእርስ በመተዋወቅ ለደጉ ዘመን ሥራ አንድነት እንቁም። የማይሠራ እምነት የለንም እና አንሸማቀቅ። የተዋረዱት ሌሎች እንጂ እኛ አይደለንም።
Source: http://haratewahido.wordpress.com/ 

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment