- ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ራሳቸውን ሸሽገዋል
- የዕጩ ፓትርያሪኮችን የሕይወት ታሪክ የያዘው መጽሔት ለዛሬም አልደረሰም
- ምርጫው ነገ በ1፡00 ሰዓት መራጮች በሚፈጽሙት ቃለ መሐላ ይጀመራል
- ፓትርያሪኩ በድምፅ ብልጫ ይመረጣል፤ እኲል ድምፅ ያገኙ አባቶች በዕጣ ይለያሉ
- የምርጫው ውጤት ነገ ከቀኑ 11፡00 ላይ ይታወቃል
- ‹‹ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እረኛና ታማኝ አገልጋይ ይኾናል ብዬ የማስበውን አባት ብቻ የምመርጥ መኾኔን በቅድስት ሥላሴ ፊት ማእምረ ኅቡአት በኾነው በኀያሉ በእግዚአብሔር ስም ምያለኹ፡፡ ቃል የገባኹትን ባላደርግ በዚህ ዓለምም ኾነ በሚመጣው ዓለም በታላቁ የፍርድ ቀን በእግዚአብሔር ፊት እጠየቅበታለኹ፡፡›› /ከባዱ የመራጮች ቃለ መሐላ/
በገለጻው መራጮች ከኅሊናቸውና ከእግዚአብሔር ጋራ ብቻ በመምከር፣ ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እረኛና ታማኝ የእግዚአብሔር አገልጋይ ይኾናል ብለው የሚያስቡትን አባት እንዲመርጡ፣ ድምፃቸውን ዋጋ አልባ ከሚያደርጉ አሠራሮችም እንዲጠነቀቁ ተነግሯቸዋል፡፡ የምርጫው ሂደት ነገ ከጠዋቱ 1፡00 በዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ መሪነት ጸሎተ ማርያም ተደግሞ፣ ስለ ዕጩ ፓትርያሪኮችና ስለ ምርጫው አካሄድ አስመራጭ ኮሚቴው በሚሰጠው አጭር ማብራሪያ የሚጀመር በመኾኑ መራጮች በተለይ ለቃለ መሐላው አፈጻጸም ከ1፡00 በፊት ተጠቃለው እንዲገኙ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡
በፓትርያሪክ ምርጫ ሕጉ አንቀጽ 11/ለ እንደተመለከተው÷ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ በሹመት ቅድምና ያላቸው ሁለት ሊቃነ ጳጳሳት ሦስቱም የመፆር መስቀል ይዘው ከመራጮች ፊት ለፊት በመቆምና መራጮች በኅብረት ድምፃቸውን አሰምተው እንዲናገሩ በማድረግ ነው ቃለ መሐላውን የሚያስፈጽሟቸው፡፡
የቃለ መሐላው ይዘት÷ ‹‹ፓትርያሪክ ለመምረጥ ስቀርብ ክፋትን፣ ተንኮልን፣ ጥላቻን፣ ቅናትንና ምቀኝነትን ከሕሊናዬ አርቄ፣ የዝምድና ወይም የጓደኝነት ትስስር እንዳይኖርብኝ አድርጌ፣ በአጠቃላይ ያለምንም አድልዎና ግላዊ ፍላጎት በማስተዋልና በጥንቃቄ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እረኛና ታማኝ አገልጋይ ይኾናል ብዬ የማስበውን አባት ብቻ የምመርጥ መኾኔን በቅድስት ሥላሴ ፊት ማእምረ ኅቡአት በኾነው በኀያሉ በእግዚአብሔር ስም ምያለኹ፡፡ ቃል የገባኹትን ባላደርግ በዚህ ዓለምም ኾነ በሚመጣው ዓለም በታላቁ የፍርድ ቀን በእግዚአብሔር ፊት እጠየቅበታለኹ፡፡››
የቃለ መሐላው ይዘት በሃይማኖት አንጻር ያለው ከባድነት፣ በዛሬው ዕለት ለመራጮቹ የተሰጠው ገለጻ፣ የድምፅ አሰጣጡ፣ ቆጠራውና ውጤቱ የሚገለጽበት አጠቃላይ ኹኔታ በመራጮች ላይ ተፈጥረው የቆዩ ጫናዎችን፣ ጥርጣሬዎችንና ድምዳሜዎችን በማቃለልና በማስወገድ ረገድ አዎንታዊ አስተዋፅኦ መጫወቱን የምርጫው ሂደት ተከታታዮች ተናግረዋል፡፡ ጥቂት በማይባሉ የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆችና የዞን የደኅንነት መዋቅርን በሚጠቀሙ ቡድኖችና ግለሰቦች÷ ‹‹ለሀገር ደኅንነትና ለሕዝብ ሰላም የሚጠቅሙ፣ ሕዝቡም የሚፈልጋቸው አቡነ ማትያስ ናቸው፤ አቡነ ማትያስን ምረጡ፤›› በሚል ከፍተኛ ቅስቀሳ መካሄዱን የሚናገሩ መራጮች እርስ በርሳቸው በመመካከርና ወደ አዲስ አበባ ከመጡም በኋላ ባገኙት መረጃና በተፈጠረላቸው ግንዛቤ ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እረኛና ታማኝ የእግዚአብሔር አገልጋይ ይኾናል ያሉትን ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
የዜናው ምንጮች ያነጋገሯቸው መራጮች÷ በትምህርታቸው፣ በመንፈሳዊነታቸውና ባላቸው የአስተዳደር ልምድ ስለ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ እና ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በብዙ እየተነጋገሩ፣ ከተለያዩ መመዘኛዎች አንጻርም መረጃዎችን እየተለዋወጡ መኾናቸውን አስታውቀዋል፡፡ የብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የኦሮሞ ተወላጅነት (ኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪነት) በሰፊው የኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አህጉረ ስብከት የመጡ መራጮችን ቀልብ መሳቡ ተዘግቧል፡፡ በታሪክ የመጀመሪያውን ‹‹ኦሮሞ ፓትርያሪክ›› መምረጥም ከጊዜው ፖሊቲካ አንጻር የሚመልሳቸው ጥያቄዎች በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም – እንደ መራጮቹ አስተያየት፡፡ በሸዋና በደቡብ ኢትዮጵያ አህጉረ ስብከት ብቻ ሊወሰን ይችላል የተባለው የብፁዕ አቡነ ማቴዎስም ድጋፍ ጎጥንና ጎሳን ተሻግሮ የተለያዩ አህጉረ ስብከት መራጮችን ሊያካትት እንደሚችል ከመራጮች የቅድመ ምርጫ አስተያየት ለመታዘብ ተችሏል፡፡ለሁለቱ ብፁዓን አባቶች ድምፃችንን እንሰጣለን የሚሉ መራጮች ስለ ብፁዕ አቡነ ማትያስ የሚሰነዝሩት አስተያየት ተቀራራቢ ነው፡፡ ብፁዕነታቸው ለ30 ዓመታት ከሀገር ርቀው በመቆየታቸው ለብዙ ነገሮች የሚጠብቃቸው እንግድነት አንዱ ነው፡፡ ሌላው ምክንያት ደግሞ ብፁዕነታቸው በግል አወቋቸውም አላወቋቸውም፣ መንግሥት አሰማራቸውም አላሰማራቸውም፣ ደገፋቸውም አልደገፋቸውም እርሳቸውን ለማስመረጥ በሚል የሙሰኞችና የሕገ ወጦች ስብስብ የኾነው የፅልመት ቡድን ራሳቸውን በደኅንነት አባልነት በሚያስተዋውቁ ኀይሎች እየተረዳ በልዩ ልዩ መንገድ በመራጮች ላይ ጫና ሲፈጥር፣ ሽብር ሲነዛ መሰንበቱ ያሳደረው ጥላቻና መመረር ነው፡፡
‹‹ከውጭ የመጡ›› እና ‹‹በመንግሥት የሚደገፉ›› የሚለው የተወ ዳዳሪዎች ዘመቻ ተደማምሮ ከምርጫው በፊት ፓትርያሪክ እንደሚኾኑ በርግጠኝነት ሲነገርላቸው ከቆዩት ብፁዕ አቡነ ማትያስ ይልቅ ያልተጠበቀ ውጤት ሊሰማበት እንደሚችል መራጮች ያሳደሩት ግምት ከዕለት ወደ ዕለት እየተጠናከረ ሲሄድ እየታየ፣ እየተስተዋለ ነው፡፡
በነገው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት መራጮች የዕጩ ፓትርያሪኮችን ስም ዝርዝር የያዘውን የድምፅ መስጫ ወረቀት ከምርጫ አስፈጻሚዎች ይቀበላሉ፡፡ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ብዛት በመራጮች መዝገብ ከተመዘገቡት መራጮች ጋራ በእኩል ቁጥር የሚታተም ነው፡፡ መራጮች የድምፅ መስጫ ወረቀቱን ከተቀበሉ በኋላ በድምፅ መስጫ ክፍል ውስጥ እየገቡ በሚፈልጉት ዕጩ ፓትርያሪክ ስም አንጻር የ‹‹ራይት›› ምልክት በማድረግ የድምፅ መስጫ ወረቀቶቻቸውን አራት ቦታ አጥፈው ወደ ሣጥኑ ይከታሉ፡፡ ለድምፅ መስጫው የተዘጋጀው ሣጥን አንድ ሲኾን እርሱም ከመስተዋት የተሠራና ዙሪያው በግልጽ የሚታይ እንደኾነ ተገልጧል፡፡
ዋጋ ያላቸው ድምፆች በግልጽ እየተለዩ ይቆጠራሉ፤ የምርጫ ውጤቱም እስከ ቀኑ 11፡00 ሊታወቅ እንደሚችል ነው የኮሚቴው ምንጮች የሚገልጡት፡፡ የድምፅ አሰጣጡ እንደተጠናቀቀ ዋጋ ያለው የመራጮች ድምፅ ከተለየና ከተቆጠረ በኋላ የድምፅ ብልጫ ያገኘው አባት ለፓትርያሪክነት ይመረጣል፤ ከተወዳዳሪዎች መካከል እኩል ድምፅ ያገኙ አባቶች በዕጣ የሚለዩ ይኾናል፡፡
ከማኅበረ ቅዱሳን አባላት ተውጣጥቶ የተዋቀረው የቴክኒክ ቡድን÷ አስመራጭ ኮሚቴውን በመራጮች አቀባበልና ምዝገባ፣ በበጀትና ፋይናንስ አስተዳደር እንዲሁም የስብከተ ወንጌል አዳራሹን ለምርጫው ክንውንና ለድምፅ አሰጣጥ በሚመችበት አኳኋን በማዘጋጀት ረገድ ከፍተኛ እገዛ በማድረግ ላይ እንዳለ ተዘግቧል፡፡
በፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቡ አንቀጽ 8 መሠረት ምርጫው 12 ያህል ታዛቢዎች ይኖሩታል፡፡ እኒህም ከታዋቂ የአገር ሽማግሌዎች(3)፣ በመንግሥት የሚወከሉ(3)፣ ከአኀት አብያተ ክርስቲያን ከእያንዳንዱ አንድ፣ ከዓለም አብያተ ክርስቲያን አንድ፣ ከአፍሪቃ አብያተ ክርስቲያን አንድ ናቸው፡፡ ምርጫውን እንዲታዘቡ በቅዱስ ሲኖዶስ የተመረጡና በዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ደብዳቤ የተጠሩ ታዋቂ የአገር ሽማግሌዎች÷ ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት ኀይለ ገብርኤል፣ ኢንጅነር ጌታቸው ማኅተመ ሥላሴ እና አቶ ደርቤ ሥነ ጊዮርጊስ መኾናቸው ታውቋል፡፡ ከአኀት አብያተ ክርስቲያን መካከል የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አንድ ታዛቢ ከመላክ ባሻገር በሁለቱ አብያተ ክርስቲያን መካከል በተደረሰው የቆየ ስምምነት መሠረት በአራት ተወካዮቿ አማካይነት በምርጫው በድምፅ እንደምትሳተፍ ይጠበቃል፡፡
በሌላ ዜና በቅዳሜው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ በዕጩ ፓትርያሪክነት መመረጣቸውን ያልተቀበሉት የወላይታ ዳውሮ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ÷ ከስብሰባው ፍጻሜ ጀምሮ ከሰው መገናኘታቸውን በማቆም ራሳቸውን እንደሸሸጉ መኾናቸው ተገልጧል፡፡ በምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ወቅት÷ ‹‹በአበው ገዳማዊ ሥርዐት በዕጩነት መመረጥ አይገባኝም፤ እንኳን አይደለም ፕትርክናው ጵጵስናውም ከብዶኛል፤ ይህን ነገር ከሰማኹ ጀምሮ ብርክ ይዞኛል፤ እኔን ተዉኝ፤ እኔ እጠፋለኹ፤›› በማለት የተናገሩት ብፁዕነታቸው÷ በተወሰነ መልኩ ለስልክ ጥሪዎች ምላሽ ይሰጡ እንደነበር የዜናው ምንጮች የተናገሩ ሲኾን፣ የሕይወት ታሪካቸውን ለመቀበል ወደ ማረፊያ ቤታቸው የሄዱ የሥነ ጽሑፍ ኮሚቴ አባላት ሊያገኟቸው እንዳልቻሉ ነው የተዘገበው፡፡ ‹‹የብፁዕነታቸው የሕይወት ታሪክና የትምህርት ደረጃ እንዳይወጣ ለሚፈልጉቱ ጥሩ አጋጣሚ ኾነላቸው፤›› ይላሉ ወዳጆቻቸው በቁጭት፡፡
ሌሎች ዕጩ ፓትርያሪኮች በራሳቸው የተዘጋጀ የሕይወት ታሪካቸውን በፊርማና ቲተራቸው አስደግፈው ለኮሚቴው ሰጥተዋል፤ የብፁዕ አቡነ ማቴዎስን ግን በተመሳሳይ መንገድ ከራሳቸው ለማግኘት እንዳልተቻለ ነው የተመለከተው፡፡ ምንጮቹ አያይዘው እንደገለጹት፣ ብፁዕነታቸው የቀጣይ ወር የሀ/ስብከቱ ሠራተኞች ደመወዝ ፔይሮል አስቀድሞ እንዲዘጋጅ ለሀ/ስብከታቸው ዋና ሥራ አስኪያጅ ትእዛዝ ሰጥተው መፈረማቸውን፣ ከዚያ ወዲህ ግን በቤታቸው ዘግተው ይቀመጡ ወይም ከመንበረ ፓትርያሪኩ ወጥተው ወደ ሌላ ስፍራ ይሂዱ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ አስረድተዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የአምስቱን ዕጩዎች የሕይወት ታሪክ ይዞ ከወጣ በኋላ ‹‹የተመጣጠነ ዝግጅት አይደለም›› በሚል ሥርጭቱ እንዲታገድ የተደረገው ኅትመት በዛሬው ዕለትም ለምርጫው ተሳታፊዎችና ተከታታዮች ሳይደርስ መቅረቱ ታውቋል፡፡ የምርጫ ጣቢያ በኾነው የመንበረ ፓትርያሪኩ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ከቀትር በኋላ ለመራጮችና ለምርጫ ተከታታዮች በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት ቀኝ አዝማች ኀይሉ ቃለ ወልድ÷ ኅትመቱ ሳይደርስ የቀረው በማተሚያ ቤት ችግር መኾኑን ገልጠው ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡
በነገው ዕለት ጠዋት ኅትመቱ ለመራጮች ከደረሰ በኋላ የዕጩዎችን ታሪክ ለማንበብና ግንዛቤ ለመጨበጥ ከምርጫው መጀመር በፊት የተወሰነ ደቂቃ ሊሰጥ እንደሚችልም ቀኝ አዝማቹ አመልክተዋል፡፡ በምርጫ ሕጉ ድንጋጌ መሠረት ኮሚቴው የዕጩዎችን የሕይወት ታሪክ፣ የትምህርት ደረጃ፣ ልምድና ብቃት ከምርጫው ቀን በፊት ለሕዝብ ግልጽ ማድረግ ይገባው ነበር፡፡ በአንዳንድ ምንጮች ጥቆማ÷ ችግሩ እንደተገለጸው በዋናነት የማተሚያ ቤቱ ሳይኾን ብፁዕ አቡነ ማትያስን አጉልተው፣ ሌሎች ዕጩዎችን አሳንሰው ለማሳየት የሚፈልጉ ቡድኖች የመራጮችን አረዳድና ሚዛን ለማዛባት የሚያሤሩት ተንኰል አካል/መገለጫ ነው፤ ድንጋጌውን ተፈጻሚ ለማድረግ ከልብ ከታሰበበት ኅትመቱ ባይሳካ ስለ ዕጩዎች ለመራጮችና ለሕዝቡ መረጃ ከመስጠት አንጻር ሌሎች ብዙ አማራጮች ነበሩና፡፡
Source: http://haratewahido.wordpress.com/
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment