የ፮ኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ዛሬ፣ ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም በጽ/ቤቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ቡራኬ ሥራውን እንደጀመረ ያስታወቀውና በብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ሰብሳቢነት የሚመራው አስመራጭ ኮሚቴው፣ ዛሬ ከቀትር በኋላ በሰጠው ባለዘጠኝ ነጥብ ጋዜጣዊ መግለጫ ለ፮ኛው ፓትርያሪክ ምርጫ ሂደት የወጣውን የምርጫ መርሐ ግብር ይፋ አድርጓል፡፡
በዐቃቤ መንበሩ ጸሎት የተከፈተው የዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫው አስፈላጊነት÷ ‹‹የምርጫውን ሂደትና 6ኛው ፓትርያሪክ የሚሾሙበትን ቀን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን ግልጽ ለማድረግ›› እንደኾነም ተመልክቷል፡፡
ኮሚቴው ባወጣው የምርጫ መርሐ ግብር መሠረት፡-
- እግዚአብሔር የወደደውን በመንበሩ ያስቀምጥ ዘንድ ከየካቲት 1 – 8 ቀን የጸሎት ጊዜ ነው፡፡
- ከየካቲት 1 – 8 ቀን ከሊቃነ ጳጳሳት መካከል የዕጩ ፓትርያሪክ ጥቆማ ይካሄዳል፡፡
- የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በአስመራጭ ኮሚቴ ተጣርተው በቀረቡለት ዕጩ ፓትርያሪኮች ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ለመወሰን የካቲት 16 ቀን ይሰበሰባል፡፡
- በአስመራጭ ኮሚቴው ቀርበው የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤን ይኹንታን ያገኙት አምስት ዕጩ ፓትርያሪኮች የካቲት 18 ቀን 2005 ዓ.ም ለሕዝብ ይፋ ይደረጋሉ፡፡
- የ፮ኛው ፓትርያሪክ ምርጫ ኀሙስ የካቲት 21 ቀን ተካሂዶ በዚሁ ዕለት ምሸት 12፡00 የተመረጠው አባት በብዙኀን መገናኛ ይፋ ይደረጋል፡፡
- የተመረጠው አባት በዓለ ሢመት የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያን መሪዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች፣ የኢ/ኦ/ተ/ቤያን ካህናትና ምእመናን በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል፡፡
- አስመራጭ ኮሚቴው መሪ ዕቅዱን ለቋሚ ሲኖዶስ አቅርቦ አጸድ ቋል፡፡
- በምርጫ የሚሳተፉት ብ ፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጥንታውያን ገዳማትና አድባራት፣ ካህናትና ምእመናን፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እንዲሁም የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ጠቅላላ ቁጥር 800 ነው፡፡
- የ6ኛው ፓትርያሪክ መራጮች ቁጥር ካለፉት አምስት የፓትርያሪክ መራጮች ቁጥር ጋራ ሲነጻጸር በእጅጉ የላቀ ነው፡፡
- በውጭ የሚገኙ ካህናትና ምእመናን ለዕጩ ጥቆማ በፋክስ ቁጥር 011- 156-77-11 እና 011-158-0540 መጠቀም ይችላሉ፡፡
- የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በወሰነው መሠረት የአራቱ አኀት አብያተ ክርስቲያን፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያን ማኅበር፣ የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያን ም/ቤት ተወካዮች እና በቋሚ ሲኖዶስ የሚመረጡ ምእመናን የአስመራጭ ኮሚቴ በሚሰጣቸው ልዩ መታወቂያ ምርጫውን እንዲታዘቡ ይጋበዛሉ፡፡
- ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ሠራተኞች፣ ከአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ከሰንበት ት/ቤት እና ከማኅበረ ቅዱሳን የተውጣጡት 13 አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ የተቋቋመው ታኅሣሥ 10 ቀን ነው፡፡
ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ (ሰብሳቢ)፣ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ (ምክትል ሰብሳቢ)፣ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ (አባል)፣ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ (ጸሐፊ)፣ መልአከ ሰላም ዓምደ ብርሃን ገ/ጻድቅ፣ ጸባቴ ኀይለ መስቀል ውቤ፣ ንቡረ እድ አባ ዕዝራ ኀይሉ፣ አቶ ዓለማየሁ ተስፋዬ፣ ቀኝ አዝማች ኀይሉ ቃለ ወልድ፣ አቶ ታቦር ገረሱ፣ አቶ ባያብል ሙላቴ (ጋዜጣዊ መግለጫውን አስተናብረዋል) እና ዲያቆን ኄኖክ ዐሥራት ናቸው፡፡
ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መካከልም ብፁዕ አቡነ ኢሳይያስ፣ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ፣ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ እና ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ተገኝተዋል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው መጨረሻ የተለያዩ ስሜቶች ተነበዋል፤ ተደምጠዋል፡፡ አብዛኞቹ ጋዜጠኞች መርሐ ግብሩ በእጅጉ የተቻኮለ መኾኑን ሲተቹም ተሰምተዋል፡፡
ተጨማሪ ዜናዎችን ይከታተሉ፡፡
የመግለጫውን ሙሉ ቃል እዚህ ይመልከቱ
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment