- የቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ በፍርድ ቤቶች ያለው ተቀባይነት ማነስ ያስከተለው ችግር፣ ልዩ እምነት ያላቸው አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያደርሱት ሕገ መንግሥቱን የጣሰ ተጽዕኖ፣ ወደ ዐረብ አገሮች እየሔዱ እምነታቸውን ወደ እስልምና የሚለውጡ ኦርቶዶክሳውያን ቁጥር መበራከትና ከእኒህም የካህናት ሚስቶች መኖራቸው፤ የአብነት ት/ቤቶች ህልውና ቀጣይነትና በተለይም የመጻሕፍተ ሊቃውንት ጉባኤያት በብዛት መታጠፍ፤ የመንፈሳዊ ኮሌጆች አስተዳደር፣ የደቀ መዛሙርቱ ምልመላና ምደባ፤ በጠረፋማ አህጉረ ስብከት የአብያተ ክርስቲያን መራራቅ፣ በበጀትና በካህናት እጥረት ለችግራቸው ቶሎ መድረስ አለመቻልና የብዙዎቹ መዘጋት፣ በሰሜን ጎንደርና ቦረና አህጉረ ስብከትየአስተዳደር ችግራቸው ያልተፈታላቸው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን የአህጉረ ስብከቱን 20 በመቶ ፈሰስ አንከፍልም ማለታቸው፣ ባልታወቁ ሰዎች የአብያተ ክርስቲያን መቃጠል፣ የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች (ዐደባባዮች፣ መካነ መቃብሮች፣ የልማት ቦታዎች) መደፈርና ወደ ግል የማዞር ችግር ጉባኤውን እያወያየ ነው፡፡
- ‹‹የቤተ ክርስቲያን ቀዳሚ ሀብቶች ምእመናን ናቸው፡፡ ብዙ ገቢ ማፍራታችን እሰየኹ ሊባል የሚገባው ቢኾንም ምእመናንን በማብዛት በኩል የተሠራው ሥራ አመርቂ አይደለም፤ የሰበካ ጉባኤያት ዋናው ትኩረት ከገንዘብ ይልቅ በገንዘብ ባለቤቶች ምእመናን ላይ መኾን ይኖርበታል፡፡›› /የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ/
- ኀምሳ አህጉረ ስብከት በ፳፻፭ ዓ.ም. ከገቢያቸው ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ፈሰስ ያደረጉት 35 በመቶ ከ89 ሚልዮን ብር በላይደርሷል፤ ከእዚህ ውስጥ 55‚256‚651 ብሩ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ለመንበረ ፓትርያርኩ ያስገባው ነው፡፡ ኀምሳው አህጉረ ስብከት በበጀት ዘመኑ ለመንበረ ፓትርያርኩ ፈሰስ ያደረጉት የአጠቃላይ ገቢያቸው 35 በመቶ ፈሰስ ከ፳፻፬ ዓ.ም የፈሰስ መጠን ጋራ ሲነጻጸር የታየው ጭማሪ 27‚273‚309 ያህል ነው፡፡ የፈሰሱ መጨመር አጠቃላይ የገቢ ዕድገትን ቢያሳይም የመንበረ ፓትርያርኩ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የሒሳብ አሠራሩን ትክክለኛነት የሚያረጋግጥበት ስምሪትና በጀት የለውም፡፡
- ‹‹በደቡብ ሱዳን አምስት ያህል አብያተ ክርስቲያን ተተክለው አገልግሎት እየሰጡ ከጋምቤላ ሀ/ስብከት ጋራ እየተዳደሩ ነው›› በሚል በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ተካትቶ የቀረበው የሀ/ስብከቱ ሪፖርት ፍጹም ሐሰት ኾኖ መገኘቱየአንዳንድ አህጉረ ስብከት መረጃዎች በጥንቃቄ መታየት እንደሚገባው ያመላከተ ኾኗል፡፡
- ፴፪ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ፥ በተሳታፊዎች አቀባበል፣ በአዳራሽ ዝግጅትና መስተንግዶ፣ በጉባኤ ሰነዶች አደረጃጀት፣ በጥናታዊ ጽሑፎችና የቡድን ውይይቶች መርሐ ግብሮች ይዘቱ መሻሻል ታይቶበታል፤ ይኹንና ለአንገብጋቢ ጉዳዮች ትኩረትና ሰፊ ጊዜ ሰጥቶ ከመወያየት ይልቅ ሪፖርቶችን ለማዳመጥ የተመደበው ሰዓት የዓመታዊ ስብሰባውን አብዛኛውን ጊዜ የሚወስድ መኾኑ ይታያል፡፡ ለስብሰባው ብር 652‚000 ወጪ ይደረጋል፡፡
- ሊቃነ ጳጳሳትን ጨምሮ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያዎችና ድርጅቶች ሓላፊዎች፣ ከኀምሳ በላይ የአህጉረ ስብከት ሥራአስኪያጆች፣ የካህናት፣ ምእመናን፣ ሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና የስብከተ ወንጌል ተወካዮች፣ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት 160 ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቃነ መናብርት በአጠቃላይ ከ900 በላይ ተሰብሳቢዎች ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
የዜናው ዝርዝር ይቀጥላል
Source: ሐራ ዘተዋሕዶ
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment