ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በመጀመሪያው ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባው ስለሚያተኩርባቸው ጉዳዮች ዛሬ፣ ጥቅምት ፲፪ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ጥዋት በጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በቅዱስነታቸው መግለጫ መሠረት ምልአተ ጉባኤው÷ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት ምእመናንን ስለ መጠበቅና ማብዛት፣ የቤተ ክርስቲያንን የትምህርት ተቋሞች በጥራትና አደረጃጀት በመለወጥ ከመማርና መሠልጠን አልፎ መከራን ለመቀበል የተዘጋጁ ላእካነ ወንጌልን አብቅቶ ስለማውጣት፣ ፍጹም የዕድገት ለውጥ ለማምጣት ስለሚያስችለው የፋይናንስና የመልካም አስተዳደር ጅምር ጥናት ሂደት፣ በቅዱስ ሲኖዶሱ የውሳኔ አሰጣጥ የቤተ ክህነት ልዩ ልዩ ክፍሎች ሓላፊዎች፣ ካህናት፣ ሊቃውንት፣ ወጣቶችና ምእመናን ውክልናና ተሳትፎ ስለሚረጋገጥበትና የቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ሰፊ ድጋፍና ተቀባይነት ስለሚያገኝበት አሠራር ይመክራል፤ ውሳኔም ያሳልፋል፡፡
‹‹የአክራሪነት፣ አሸባሪነትና ጽንፈኝነት›› ተግባራትን በማውገዝ የክርስቶስ መልእክት የኾነውን ሰላምና እኩልነት፣ መከባበርና መቻቻል፣ አብሮ መልማትና ማደግ ለሕዝቡ በየቀኑ ማስተማርና መስበክ እንደሚገባ የገለጹት ፓትርያርኩ፣ ‹‹የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ችግሮችን በውይይትና በውይይት ብቻ የመፍታት ባህል መደገፍና ማጎልበት አለብን፤›› ሲሉም መክረዋል፡፡
አጀንዳዎቹ÷ በፍትሕ መንፈሳዊ በተደነገገው መሠረት የተሰበሰበው ምልአተ ጉባኤው መንፈስ ቅዱስ በሚገልጽለት መንፈሳዊ ጥበብ እየተመራ መፍትሔ ማግኘት ያለባቸው ጉዳዮች መፍትሔ እንዲያገኙ፣ በጥልቀት፣ በማስተዋልና የሓላፊነት መንፈስ በተላበሰ ወኔ በመወያየት ሊወስንባቸውና ለተግባራዊነታቸው ሊረባረብባቸው እንደሚገባ ምልአተ ጉባኤውን በርእሰ መንበርነት የሚመሩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በመግለጫቸው አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም ፓትርያርኩ፣ መንፈስ ቅዱሳዊና ሐዋርያዊ ዐቢይ ጉባኤው በስብሰባው መጨረሻ የሚደርስበት ውሳኔና የሚያወጣው መመሪያ በውጤቱ÷ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስፋፋ፣ ማኅበረ ካህናቱንና ማኅበረ ምእመናኑን የሚያስደስት፣ በሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን ተከታዮች ዘንድ በናፍቆት የሚጠበቀውን የለውጥና የዕድገት ጎዳና የሚከፍት እንዲኾን በመግለጽ መግለጫቸውን ደምድመዋል፡፡
የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባመክፈቻጋዜጣዊ መግለጫ ዐበይት የትኩረት ነጥቦች
በድንበር የለሽ ስብከተ ወንጌል በርከት ያሉ በጎችን የማርባትና የመጠበቅ ሥራ
- ከትንሹ የሥልጣነ ክህነት ሹም ጀምሮ እስከ ትልቁ የቤተ ክርስቲያን ባለሥልጣን ድረስ ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት ተልእኮ በንቃት፣ በሙሉ ዕውቀት፣ በተነሣሽነት፣ በፍጹም ፈቃደኛነት እንዲነሣሣና እንዲሰለፍ የሚጠበቀውን ያህል አልተሠራም፡፡
- ቤተ ክርስቲያን በጥምቀት ወልዳ፣ በሥጋ ወደሙ አሳድጋ፣ ወልደ ማርያም፣ ገብረ ሚካኤል ብላ የሠየመቻቸው ልጆቿከጉያዋ እየተነጠቁ ወደ ሌላ ካምፕ ሲወሰዱ እርስዋ የወላድ መሐን የኾነችበት፣ ያልወለዱና ያላሳደጉ ባለብዙ ቤተሰብ የኾኑበት ክሥተት እያጋጠመ ነው፡፡
- የቅዱሳን ሐዋርያት ሥልጣን ወራሾች እንደመኾናችን ቁጥር አንድ ሥራችን በድንበር ሳይገደቡ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በሥሩ ያሉትን በጎች መጠበቅ ብቻ ሳይኾን ድንበር የለሽ ትምህርትና ስብከት በማካሄድ ከዛሬ ጀምሮ በየዓመቱ በርከት ያሉ በጎችን የማርባትና የመጠበቅ ሥራ ሊያሠራው የሚችል አሠራር መቀየስ አለበት፡፡
የትምህርት ተቋሞቻችንን በብዛትም በጥራትም በአደረጃጀትም በመለወጥ ትንሣኤዎቻቸውን ማብሠር፤
- የምንሾማቸው ዲያቆናት፣ ቀሳውስትም ኾኑ ኤጲስ ቆጶሳት በተለምዶ የተሾሙ ሳይኾኑ ጌታችን እንዳደረገው የተማሩ፣ የሠለጠኑ፣ ነገሩ የገባቸውና መከራውን ለመቀበል የተዘጋጁ ሊኾኑ ይገባል፡፡
- የአብነት ት/ቤቶቻችን፣ የካህናት ማሠልጠኛዎቻችንና የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን በብዛትም በጥራትም በአደረጃጀትም ተማሪውን በትክክል ለመለወጥና ለመቅረጽ በሚያስችል አዲስ አሠራር ማስተካከልና ማብቃት አለብን፡፡
- ቤተ ክርስቲያናችን የሃይማኖት እንከን ሳይኖራት፣ ሞያ ሳያንሳት፣ ተቆርቋሪ ምእመናን እያሏት በአያያዝና በአመራር ምክንያት የምትወቀስበትና ልጆቿን የምታጣበት ታሪክ መገታት አለበት፡፡ ይህን በወሳኝ መልኩ ለማስተካከል የትምህርት ቤቶቻችንን ትንሣኤ የሚያበሥር፣ ዕድገታቸውንና ጥራታቸውን የሚያፋጥን ጠንካራ መሠረት ዛሬ ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡
ስለ ዘመናዊ የፋይናንስ አሠራርና መልካም አስተዳደር የተጀመረው ጥናት ሂደት
- ምእመናን የሚፈለገውን ዐሥራት፣ በኵራትና ቀዳምያት በሕጉ መሠረት እየሰጡ አይደለም፤ የሚሰጡትም ስጦታ በየመንገዱ እየተንጠባጠበ ወፎች የሚለቃቅሙት ይበዛዋል፡፡ የሚፈለገውን ያህል ተደራጅተን፣ መስለን ሳይኾን ኾነን፣ በሁሉም ነገር ተዘጋጅተን ማስተማር፣ ዘመኑ በሚፈቅደው የፋይናንስ ቁጥጥርና አያያዝ መጠቀም አለብን፡፡
- ከወገንተኝነትና አድሏዊነት በአግባቡ ያልተላቀቀው አስተዳደራችን የቤተ ክርስቲያናችንን ተሰሚነት ክፉኛ እየጎዳው ነው፡፡ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ጉባኤው የማፍረስ ሳይኾን የመገንባት ግብ ያለው ራእይ አንግቦ ሥር ነቀል የኾነ ፍጹም የዕድገት ለውጥ ለማምጣት የሚያስችለውን አሠራር መቀየስ ይገባዋል፡፡
በቅዱስ ሲኖዶስ የውሳኔ አሰጣጥ የካህናትና ምእመናን ተሳትፎ ስለማረጋገጥ
- ቅ/ሲኖዶስ በጉዳዮች ካህናትንና ምእመናንን እያሳተፈና በሐዋርያዊ ሥልጣኑ እያጸደቀ የውሳኔውን ተቀባይነትና ድጋፍየሚያሰፋበትንና የሚያረጋግጥበትን አሠራር ይተክላል፡፡
ምንጭ: ሐራ ዘተዋሕዶ
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment