- ከጉጂ ቦረናና ሊበን ዞኖች ሀገረ ስብከትና ሌሎች አብያተ ክርስቲያን በዘረፉት ገንዘብ ‹‹ሺበሺ›› በሚለው አስከፊ የሙስና ስያሜ የሚታወቁትና በነፍስ ግድያ ወንጀሎች የሚጠረጠሩት አቡነ ሳዊሮስ የሚያስተባብሯቸው የግብር አምሳሎቻቸው፣ መልአከ ገነት አባ አፈ ወርቅ ዮሐንስ እና መልአከ ገነት አባ ዮናስ ታደሰ ዋነኛ ተጠያቂዎች ይኾናሉ ተብሏል፡፡
- ማኅበረ ቅዱሳንን ‹‹የዐፄ ምኒልክ ሥርዐት እንዲመለስና የዐፄ ምኒልክ ባንዴራ እንዲሰቀል የሚፈልጉ ናቸው›› ብለው በመንግሥታዊ ስብሰባ ላይ በይፋ በመክሰስ ርምጃ እንዲወስድበት የጠየቁት የወሊሶ ሀ/ስብከት ሥ/አስኪያጅ መልአከ ገነት አባ አፈ ወርቅ፣ በመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ‹‹አጥቢያዎች ፐርሰንት እንዳይከፍሉ ሕዝቡን ይከፋፍልብናል፤ ወጣቶችን ያደራጅብናል›› በሚል መሠረተ ቢስ ክሥ በቅ/ሲኖዶስ እንዲታገድ ጠይቀዋል፡፡
- የደቡብ ምዕራብ ሸዋ – ወሊሶ ሀገረ ስብከትን በሊቀ ጳጳስነት ይኹን በሥራ አስኪያጅነት ለመምራት ችሎታውም ሥነ ምግባሩም እንደሌላቸው ተቃውሞ የቀረበባቸው አቡነ ሳዊሮስ እና መልአከ ገነት አባ አፈ ወርቅ ዮሐንስ ለ፴፪ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ባቀረቡት ‹ሪፖርት›፣ የአስተዳደራቸውን ብልሹነት የተቃወሟቸውን አገልጋዮችና ምእመናን ‹‹ሥራ ዐጦች እና ተራ ዱርዮዎች›› በማለት ዘልፈዋል፡፡
- ምግባረ ብልሹው ሥራ አስኪያጅ በነሐሴ ወር ፳፻፭ ዓ.ም. የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የጸጥታ ቢሮ በአዳማ ከተማ ባዘጋጀውና ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት በተሳተፉበት ‹‹የፀረ አክራሪነት›› ስብሰባ÷ ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በተሰጠው መተዳደርያ ደንብ መሠረት የተማረው ትውልድ በትምህርትም ኾነ በሥራ ምክንያት በሄደበት በሰንበት ት/ቤትና በሰበካ ጉባኤ ታቅፎ በገንዘቡ፣ በዕውቀቱና በጉልበቱ ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግል የሚያከናውነውን አገልግሎት በጣልቃ ገብነት ከሰዋል፡፡ የስብሰባው መሪም ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ of tooltoota ነው፤›› ሲሉ በግልጽ ተባብረዋቸዋል፡፡
- የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከነሐሴ ፳፩ – ፳፫ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም. ባዘጋጁት ‹‹አገር አቀፍ የሰላም ዕሴት ማጎልበቻ ጉባኤ›› ላይ÷ ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በተሰጠው መተዳደርያ ደንብ መሠረት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያት የሚያከናውነውን አገልግሎት ከተቀበረ ፈንጂ ጋራ ያመሳሰሉት መልአከ ገነት አባ ዮናስ ታደሰ፣ በጉጂ ቦረናና ሊበን ዞኖች ሀ/ስብከት የሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቀሲስ ነበሩ፡፡
- የአጠቃላይ ጉባኤው ዓመታዊ ስብሰባ ተሳታፊ የኾኑት መልአከ ገነት አባ ዮናስ፣ የአባ አፈ ወርቅ ዮሐንስን የውንጀላ ሪፖርት ‹‹ወንድ! ያበጠው ይፈንዳ!›› በማለት ከሊቀ ጳጳሱ ጋራ በከፍተኛ ስሜት ሲደግፉ ተስተውለዋል፡፡ አባ ዮናስ በከምባታ ሃድያ ስልጢና ጉራጌ ዞኖች አህጉረ ስብከት የሦስት አብያተ ክርስቲያናትን አስተዳደር ከወረዳ ቤተ ክህነቱ ጋራ ደራርበው የሚመሩ፣ በጠበኛነትና ከሙስሊም ሴቶች ጋራ ሳይቀር ዝሙት በመፈጸማቸው የሙስሊም አዛውንቶች ስሞታና ክሥ ያቀረቡባቸው ቆሞስ ነኝ ባይ ስመ መነኩሴ ናቸው፡፡
- መሰላቸው መልአከ ገነት አባ አፈ ወርቅ ዮሐንስ ደግሞ በምዕራብ ሸዋ ሀ/ስብከት የአምቦ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ወቅት በተካሄደ የኦዲት ምርመራ በከፍተኛ የገንዘብ ጉድለት በተነሣ አለመግባባት ከተወገዱ በኋላ በቀድሞው ፓትርያርክ ትእዛዝ የሆሮ ጉድሩ (ሻምቡ) ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅነት የተሾሙ፣ በሻምቡ ብልሹ አሠራራቸውንና ምግባራቸውን ያጋለጡ ቀናዒ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችንና የማኅበረ ቅዱሳን አባላትን በአሸባሪነት በመክሰስ ስም ዝርዝራቸውን ጠቅሰው ለመንግሥት የከሰሱ፣ ይህንኑ ተግባራቸውን በ፳፻፬ ዓ.ም. በተካሄደው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ በሪፖርት እንዲያቀርቡ በቀድሞው ፓትርያርክ ትእዛዝ መበረታታቸውን የገለጹና በማቅረባቸውም የተሸለሙ ናቸው፡፡ ምግባረ ብልሹው አባ አፈ ወርቅ በኢጃጂ እና ሻምቡ ከተሞች እንዲሁም በሰበታ ቤተ ደናግል ሴት መነኩሲትን በዝሙት በማሳሳት በወለዷቸው ልጆች ምንኵስናቸውን ያዋረዱ፣ እንደ አባ ዮናስም የኦሕዴድም የኦነግም የአባልነት መታወቂያዎች ይዘው ንግዳዊ ፖሊቲካ በማራመድ የሚታወቁ ናቸው፡፡
- በቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት÷ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በተገበረው የሽግግር መዋቅርና ለቀጣይ የለውጥ አመራር ባካሄደው የመዋቅር፣ አደረጃጀትና ዝርዝር የአሠራር ጥናት የማኅበረ ቅዱሳን ሞያተኞች ግንባር ቀደም ተሳትፎ በማድረጋቸው ሕገ ወጥ ጥቅማቸው የሚነካባቸው አንዳንድ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳደር ሓላፊዎች የመንግሥትን የአክራሪነት ውንጀላ አመካኝተው ማኅበሩን ለማሸማቀቅ በከፍተኛ ደረጃ እየተንቀሳቀሱ ነው፤ ፴፪ኛውን የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በቅሰቀሳ መድረክነት እየተጠቀሙ ነው፡፡
- በግንቦት ፳፻፭ ዓ.ም. የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት ለአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የተጠናው የለውጥ አመራር መዋቅር፣ አደረጃጀትና ዝርዝር አሠራር ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አልፎ ለመላው አህጉረ ስብከት በመነሻ ሞዴልነት የሚጠቀስ እንደኾነ ፓትርያርኩም ረዳት ሊቀ ጳጳሳቸውም መስክረዋል፤ በትውፊታዊውም ይኹን በዘመናዊ ትምህርት ደክመው ተጨባጭ ሞያዊ ክሂል ያላቸው ባለሞያ ሠራተኞችና አገልጋይ ካህናት ሁሉ ትክክለኛ ቦታቸውን የሚያገኙበት፣ አቅማቸውን በቀጣይነት የሚያሳድጉበትና ጥቅማቸውን የሚያረጋግጡበት፣ የምእመናን ገንዘባቸው ከዘረፋ ተጠብቆ በአግባቡ የሚለማበት መኾኑን በመጥቀስ አመስግነዋል፡፡
- ወቅቱ ሀ/ስብከቱ ጥናቱን (የለውጥ አመራር አስተሳሰብና ተግባሩን) መላው የሀ/ስብከቱ ሠራተኞች፣ ካህናት፣ ሊቃውንት፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና ምእመናን በሚገናኙበት የጋራ መድረክ በማቅረብ ጥልቅ ግንዛቤ ለመፍጠርና ለማዳበር የሚዘጋጅበት ነው፡፡ ይህ ኾኖ ሳለ የሀ/ስብከቱን የሙስና ኔትወርክ ተቆጣጥረው የኖሩ የጥቂት አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን በለውጥ ስም ካህናቱን በማግለልና ቀውስ በመፍጠር ቤተ ክርስቲያኒቱን ሊቆጣጠር ነው›› በሚል ሂደቱን በሚያደናቅፍ አሉታዊ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ (blackmailing strategy) ተጠምደው ይገኛሉ፤ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ በማወቅም ይኹን ባለማወቅ የሠሯቸውን አስተዳደራዊ ስሕተቶች በመለጠጥ እንዲሁም የመንግሥትን ‹‹የፀረ አክራሪነት እንቅስቃሴ›› አጀንዳ በመጠቀም ማኅበረ ቅዱሳንን በጽንፈኛነት ለማስመታት ‹‹የፀረ አክራሪነት ሰልፍና ስብሰባ›› ለመጥራት ተዘጋጅተዋል፡፡
- የቀድሞው የሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በነበሩትና ዛሬም በሕገ ቤተ ክርስቲያን ባልተደገፈውና አስፈላጊነትም በሌለው‹‹የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅነት›› ስም በፓትርያርኩ ጽ/ቤት ከትመው የጥፋትና ድለላ (ለጵጵስና ለሚቋምጡ ቆሞሳት) ተግባራቸውን በሚያጧጡፉት ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ይታገዛሉ፡፡ ከእኒህ ቀንደኛ የሙስና ጌቶች የኾኑ የአድባራት አስተዳዳሪዎች መካከል÷ ቀድሞ የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል አሁን የደብረ ጽጌ ቅ/ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ መንክራት ኃይሌ ኣብርሃ፣ የሲ.ኤም.ሲ፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የየካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል አብያተ ክርስቲያን፣ የደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን አለቆች ይገኙበታል፡፡
- ከኀምሳው አህጉረ ስብከት የሚበዙት ማኅበረ ቅዱሳን በተቋማዊ ለውጥ አመራር፣ በቅዱሳት መካናትና አብነት ት/ቤቶች ድጋፍና ክብካቤ፣ በስብከተ ወንጌል መስፋፋትና መጠናከር ያደረገውን አስተዋፅኦ በሪፖርታቸው በማካተት እየገለጹ ባለበት ኹኔታ፣ እንደ መልአከ ገነት አባ ዮሐንስ አፈ ወርቅና መሰሎቻቸው የሚያቀርቡት የውንጀላ ሪፖርት ለአንዳንድ ጥቅመኛ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳደር ሓላፊዎች የቅስቀሳ መሣርያነት መዋሉ የአጠቃላይ ጉባኤውን ተሳታፊዎች እያስቆጣ ነው፤ የስብሰባ አመራሩም እያጠያየቀ ነው፡፡
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment