Tuesday, October 29, 2013

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ በ28 የመነጋገርያ አጀንዳዎች ውይይቱን ቀጥሏል

Ethiopian_Orhodox church bilden addis_Abeba_2
  • ዐሥር አህጉረ ስብከት የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እንደሚደረግባቸው ተጠቁሟል፤ በፓትርያርኩ፣ ብፁዕ ዋና ጸሐፊውና ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ የተያዙና በቁጥር ከ10 – 12 የሚኾኑ የታሳቢ ዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት ዝርዝር ለምልአተ ጉባኤው እንደሚቀርብ ይጠበቃል፡፡
  • በተጭበረበረ የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ማስረጃና የዶክትሬት መመረቂያ ጥናትን አስመስሎ መቅዳት/plagiarism/ ክሥና ወቀሳ እየቀረበባቸው የሚገኙት፣ ሓላፊነትን በተገቢው ኹኔታ ባለመወጣትና በትጋት ባለመሥራት የተገመገሙት ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም መለሰ፣ በከባድ እምነት ማጉደል በተቀሰቀሰባቸው የካህናትና ምእመናን ተቃውሞ ከቅ/ላሊበላ ደብር አስተዳዳሪነት የሚነሡት አባ ገብረ ኢየሱስ መኰንንና የመሰሏቸው ቆሞሳት ከታሳቢ ዕጩዎች መካከል መገኘታቸው በምርጫው አግባብነት ላይ ጥያቄ አስነሥቷል፡፡
  • ‹‹የምንሾማቸው ኤጲስ ቆጶሳት በተለምዶ የተሾሙ ሳይኾኑ የተማሩ፣ የሠለጠኑ፣ ነገሩ የገባቸውና መከራ ለመቀበል የተዘጋጁ ሊኾኑ ይገባል›› ከሚለው የፓትርያርኩ የምልአተ ጉባኤ ጋዜጣዊ መግለጫ ጋራ በቀጥታ የሚጣረስ አይደለምን? የቤተ ክርስቲያንንስ አመራር ከወቀሳ ያድናል?
  • የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የመዋቅር፣ አደረጃጀትና ዝርዝር አሠራር ጥናትና የረዳት ሊቀ ጳጳሱ ተግዳሮቶች፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደራዊ ችግርና የሊቀ ጳጳሱ ዕጣ ፈንታ እንዲሁም በሊቃነ ጳጳሳቱ ዝርዝር እይታ ላይ የሚገኘው የሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ረቂቅ ምልአተ ጉባኤውን በስፋት እንደሚያነጋግ ተጠቁሟል፡፡
  • የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሕንፃን የጠቅላይ ቤተ ክህነት የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ያስተዳድራል፤ የመንፈሳዊ ኮሌጆች ልዩ ልዩ ገቢዎች በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሒሳብ ተካተው በሚመደብላቸው በጀት ብቻ ይሠራሉ፡፡
  • በመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ከኦዲት ምርመራ ጋራ በተያያዘ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የቀረበውን ግለሰባዊ ትችት ምልአተ ጉባኤው በከፍተኛ ድምፅ ውድቅ በማድረግ የዘገየው የማኅበሩ መተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ ተጠናቆ እንዲቀርብ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡
  • ሊቃነ ጳጳሳቱ በ‹‹መቻቻል›› ላይ የሰነዘሩት ትችት መንግሥትን አሳስቧል፤ የቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋራ ሌላ ዙር ውይይት እንደሚያስተናግድ ይጠበቃል፤ በደኅንነት ስም በየሊቃነ ጳጳሳቱ ቤት የሚዘዋወሩ ግለሰቦች ዝርዝር ለመንግሥት ይቀርባል፡፡
  • የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት ሓላፊነታቸውን ለቀው ወደ አሜሪካ ሄዱ፡፡ በአውስትራልያ በአሜሪካው ሲኖዶስ አስተዳደር ሥር የምትገኝ የአንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እልቅና በውዝግብመሾማቸው ተነግሯል፡፡


አራተኛ ቀኑን ያስቆጠረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ 28 የመነጋገርያ አጀንዳዎችን በማጽደቅ መወያየቱን እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ በመክፈቻ ሥርዐተ ጸሎት ተጀምሮ በጥብቅ ምስጢራዊነት በመወያየት ላይ የሚገኘው ምልአተ ጉባኤው መግባባትና ግልጽነት በሰፈነበት ኹኔታ ዓመታዊ ስብሰባውን እያካሄደ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡
ከዐርባ ያላነሱ የቅ/ሲኖዶሱ አባላት የተገኙበት ምልአተ ጉባኤው በቆይታው፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ያቀረቡትን ሪፖርት አዳምጧል፡፡ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የ፳፻፮ ዓ.ም. በጀትና በዕቅድና ልማት መምሪያ ተዘጋጅቶ በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ማቴዎስ የቀረበውን የበጀት ዓመቱን መሪ ዕቅድ ተመልክቷል፤ የማስተካከያ ሐሳቦችን በማከል ለዳግም እይታ እንዲቀርብም አዝዟል፡፡
ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከሚገኝበት የፋይናንስ አቅም ጋራ ተያይዞ ስለ በጀት ምንጮች መነጋገሩ የተዘገበው ምልአተ ጉባኤው÷ መንፈሳዊ ኮሌጆች የሚቆጣጠሯቸው ሕንጻዎች በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ሥር ኾነው ድርጅቱ እንዲያስተዳድራቸው፣ ሌሎች የገቢ ምንጮቻቸውም በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሒሳብ ተካተው ጠቅላይ ጽ/ቤቱ በሚመድብላቸው በጀት እንዲተዳደሩ ምልአተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
በዚህ የስምምነት ውሳኔ መሠረት በዕሥራ ምእቱ መባቻ በ57 ሚልዮን ብር ተገንብቶ የኪራይ አገልግሎት የሚሰጠውና የውስጥ ገቢ የሚያስገኘው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሕንጻ ከኮሌጁ አስተዳደር ቁጥጥር የሚወጣ ይኾናል፡፡ ኮሌጁ ከሌሎች የውስጥ ገቢዎቹ ማለትም ከቀን ተመላላሽ፣ ከማታ ተከታታይ፣ ከርቀት ትምህርትና ከድኅረ ምረቃ መርሐ ግብሮች፣ ከአዳራሽ፣ ከመማሪያ ክፍሎችና ከካፊቴሪያ ኪራይ በወር በድምር የሚያገኘው ከአንድ ሚልዮን ብር በላይ ገቢ ከሕንጻው ኪራይ በወር ይሰበስበዋል ከሚባለው ሌላ አንድ ሚልዮን ብር ያህል ገቢ ጋራ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሒሳብ ይዞራል፤ ኮሌጁም በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ አንቀጽ ፵፪/፭/መ መሠረት ሁሉም አህጉረ ስብከት ከጠቅላላ ገቢያቸው በሚመድቡለት የአምስት ፐርሰንት አስተዋፅኦ ተልእኮውን ይፈጸማል ማለት ነው፡፡
ፓትርያርኩን ጨምሮ በምልአተ ጉባኤው የተደገፈውን ይህን ስምምነት ከሥልጣናቸው እንዲገለሉ የተወሰነባቸው የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ኮሌጁ ሕንጻውን እንዲያስተዳድርና የውስጥ ገቢውን እንዲደጉምበት ጽፈውት የነበረውን ደብዳቤ በአስረጅነት በማቅረብ ተቃውመውታል፡፡ ተቃውሟቸው አንዳችም የምልአተ ጉባኤውን ተቀባይነት ሳያገኝ በተባበረ ድምፅ ውድቅ ተደርጓል፡፡
የሕንጻው አስተዳደር ከኮሌጁ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በመዞሩ ያልተደሰቱ ወገኖች ‹‹ተወሰደበት›› በሚል ውሳኔውን ነቅፈዋል፡፡ በአንጻሩ ግዙፉ ሕንጻ የኮሌጁን የፋይናንስ አቅም ለማሳደግ ቢገነባም ኮሌጁ ከገቢው ሳይጠቀምና ከበጀት ችግሩ ሳይላቀቅ መቆየቱን፣ የደቀ መዛሙርት አልጋ፣ ፍራሽ፣ ብርድ ልብስ ሳይቀየር፣ ለመምህራኑ በፍትሐዊነት ደመወዝ ሳይስተካከል ጥቂት የቢሮ ሠራተኞች ብቻ የደመወዝ ጭማሪ ያገኙበትን ኹኔታ በመጥቀስ ውሳኔውን የደገፉም ብዙዎች ናቸው፡፡
የምልአተ ጉባኤው ውሳኔ፣ ለኮሌጁ አስተዳደር መበላሸት ብዙዎች ግንባር ቀደም ተጠያቂ የሚያደርጓቸውን የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ከቦታው የማግለል ጅምር አልያም ከዛሬው ስብሰባ እንደሚጠበቀው፣ ቀደም ሲል በተላለፈው ውሳኔ መሠረት ብፁዕነታቸውን በበላይ ጠባቂነት ወስኖ ብቁ ዋና ዲን የመሠየም አካሄድ መኾኑም ታምኖበታል፡፡ ከዚሁ ተያይዞ የደቀ መዛሙርት ምልመላና አቀባበል መስፈርት ከሌሎች ተመሳሳይ የተቋሙ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋራ በአንድነት እንደሚታዩ ተጠቅሷል፡፡
የፓትርያርኩ በዓለ ሢመት ቀን በጾም የሚውልባቸው ጊዜያት በመኖራቸው ቀኑን በለውጥ ስለ መበየን በጽ/ቤታቸው የቀረበውን አጀንዳ በተመለከተ ምልአተ ጉባኤው የተለያዩ አማራጮችን አይቷል፡፡ ከአማራጮቹ መካከል፡- ሢመተ ፕትርክናው የተፈጸመበት የካቲት ፳፬ ቀን ዐቢይ ጾምን ሊነካ ስለሚችል በሱባኤው ለአክብሮ በዓል ከምንወጣ በርክበ ካህናት/በዓለ ትንሣኤ በዋለ በ፳፭ው ቀን/ አድርገን በዚያው የምልአተ ጉባኤውን ስብሰባ እናድርግ የሚለው አንዱ ነው፡፡
በሌላ በኩል፣ በዓለ ሢመትን የምናክበረው ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ፕትርክና ራስዋን የመቻሏን የነጻነት በዓል ለመዘከርም በመኾኑ ቀኑ በወርኃ ጾም መዋሉ አይከለክለንም የሚሉ በበኩላቸው፣ የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን በፊልጵስዩስ የታነፀችበትን(ሕንጸታ ለቤተ ክርስቲያን) እንዲሁም የመጀመሪያው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የተሾሙበትን ሰኔ ፳፩ ቀን በአማራጭነት አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም ሁሉም ክንውን በየራሱ ታሪክ ስላለው ድርጊቱ የተፈጸመበት የመጀመሪያው ቀን መጠበቅ ይኖርበታል በሚለው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በፕትርክና የተሠየሙበት የካቲት ፳፬ ቀን ዕለቱን እንዳይለቅ በዚያው ጸንቷል፡፡
ቋሚ መንፈሳዊ ት/ቤቶችና ኮሌጆች ወጥነት ያለው ቋሚ ሥርዐተ ትምህርት እንዲኖራቸው፣ የሚያግዘው የትምህርትና ሥልጠና መምሪያ ያቀረበው መሪ ዕቅድ የቅዱስ ሲኖዶሱን አጽድቆት አግኝቷል፡፡ መሪ ዕቅዱ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በመክፈቻ ጋዜጣዊ መግለጫቸው እንዳመለከቱት÷ የአብነት ትምህርት ቤቶቻችን፣ ማሠልጠኛዎቻችንና የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን በብዛትም በጥራትም በአደረጃጀትም ደቀ መዛሙርቱን በትክክል ለመለወጥና ለመቅረጽ የሚያስችል አዲስ አሠራር ይዘረጋ እንደኾን በሂደት የምናየው ይኾናል፡፡
ለመንፈሳውያን ማኅበራት ራሱን የቻለ መተዳደርያ ደንብ ስለማዘጋጀትና ከዚሁ ጋራ በተገናኘ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን በ፴፪ው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ሂደት እንዲሁም በአጠቃላይ ጉባኤው የአቋም መግለጫና የውሳኔ ሐሳብ ላይ የተነሡት ነጥቦች ምልአተ ጉባኤውን ያወያየ ሌላው የመነጋገርያ አጀንዳ ነበር፡፡ የአጠቃላይ ጉባኤው የአቋም መግለጫና የውሳኔ ሐሳብ፣ ማኅበሩ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ባሉት ማእከላትና የግንኙነት ጣቢያዎች በየሀገረ ስብከቱ ያበረከተውን ሁለንተናዊ ልማት ጉባኤው ከየሪፖርቱ በማወቁ አገልግሎቱን እንደተቀበለው ጠቅሷል፡፡
በትላንቱ የምልአተ ጉባኤው ስብሰባ÷ ማኅበሩ የገቢና የወጭ ሒሳቡን በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቁጥጥር አገልግሎት እንደማያስመረምር፣ አሠራሩ አቅጣጫ የሳተና ግራ አጋቢ እንደኾነ ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ አቡነ ፋኑኤልና አቡነ ሳዊሮስ ትችት ተሰምቷል፤ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩም ‹‹በሕጉ መሠረት መሥራት አለበት›› በማለት አክለውበታል፡፡ ለእነዚህ ትችቶች ምላሽ የሰጡት የተቀሩት ብፁዓን አባቶች በተለይም ብፁዕ አቡነ ገሪማ፣ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፣ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስና ብፁዕ አቡነ ገብርኤል÷ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን ከአባላቱ አልፎ የምእመናን ሁሉ/ማኅበረ ምእመናን ኾኖ አገልግሎቱን በታማኝነት እየፈጸመ ነው፤ ከእኛው ሳይጠየቅ ቀርቶ ካልኾነ በቀር ማኅበሩ ሒሳብ አላስመረምርም አላለም፤ ለማስመርመርም ተዘጋጅቶ ሲጠብቅ አልታየለትም፤›› ሲሉ ሒሳቡንም በቁጥጥር አገልግሎቱ አላስመረምርም ብሏል በሚል የቀረበውን ክሥ ውድቅ አድርገውታል፡፡
ቅ/ሲኖዶሱ ማኅበሩ አገልግሎቱን የሚፈጽምበት መተዳደርያ ደንብ አጽድቆ እንደሰጠው ያስታወሱ ሌሎች ብፁዓን አባቶች ይዘጋጃል የሚባለው የማኅበራት መተዳደርያ ደንብ እንደማይመለከተውና እነርሱ የሚያውቁት በዚሁ የመተዳደርያ ደንቡ መሠረት በመሥራት ላይ እንዳለ መኾኑን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ ይልቁንም የሚሻሻልለት መተዳደርያ ደንብ በመዘግየቱ ይህንኑ ማኅበሩ በደብዳቤ መጠየቁ በጉባኤው ላይ የተጠቀሰ ሲኾን፣ በእጅጉ የዘገየው የማኅበሩ መተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ ለግንቦት የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ተጠናቅቆ እንዲቀርብ ታዝዟል፡፡
ምልአተ ጉባኤው በዛሬውና በቀጣዮቹ ቀናት ውሎው፣ በ፳፻፭ ዓ.ም. የጥቅምት ምልአተ ጉባኤ ከቤተ ክርስቲያን ዕድገትና ከሚያስፈልጋት ተቋማዊ ለውጥ አንጻር ተገናዝቦ እንዲሻሻል ባዘዘው መሠረት በአርቃቂ ኮሚቴው ተዘጋጅቶ የቀረበለትን የ፲፱፻፺፩ ዓ.ም. ሕገ ቤተ ክርስቲያን የማሻሻያ ረቂቅ ይመረምራል፡፡ ረቂቁ በትላንትናው ዕለት ለምልአተ ጉባኤው አባላት የተሰራጨ ሲኾን በኮሚቴው አማካይነት ሰፊ ውይይት እንደሚደረግበት ይጠበቃል፡፡
በተጨማሪም ምልአተ ጉባኤው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር አገር አቀፍ የምሥረታ ጉባኤውን ያካሄደውን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የመተዳደርያ ደንብ መርምሮ ያጸድቃል፡፡ ደንቡ ሰንበት ት/ቤቶች ወጥ በኾነ ሥርዐት መልካም አገልግሎት እንዲያበረክቱ፣ አንድነት እንዲኖራቸውና ሁለገብ አገልግሎታቸው እንዲጠናከር ያበቃቸዋል ተብሎ ታምኖበታል፡፡
በለውጥ የሽግግር መዋቅር ውስጥ ለቆየው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የተጠናቀቀው የለውጥ አመራር መዋቅር፣ አደረጃጀትና ዝርዝር አሠራር ጥናት ሂደትም በምልአተ ጉባኤው ይገመግማል፡፡ የሽግግሩ አፈጻጸም በምልአተ ጉባኤው የሚመዘን ሲኾን ከዚሁ ጋራ ተያይዞ የሀ/ስብከቱን ወቅታዊ የለውጥ ተግዳሮቶች በማጤን ከፍተኛ ውሳኔ ሊተላለፍ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
ምንጭ: ሐራ ዘተዋሕዶ
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment