ነገ በሚጠናቀቀው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ፴፪ኛ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ‹‹የሃይማኖት መቻቻል›› በሚለው መርሐ ግብር ‹‹የብዝኃነት አያያዝ፣ አክራሪነት/ጽንፈኝነት ዝንባሌዎቹና መፍትሔዎቹ›› በሚል ርእስ አቶ ገዛኸኝ ጥላሁን፣ አቶ ታዴዎስ ሲሳይ እና አቶ ጣሰው ገጆ በተባሉ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሦስት ከፍተኛ አማካሪዎችና ባለሞያዎች ጽሑፍ መቅረቡና ውይይት መካሄዱ ተዘግቧል፡፡
በውይይቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ከየአህጉረ ስብከታቸው ተጨባጭ ኹኔታ በመነሣትና ጽሑፉ በቀረበበት ይዘቱ በመገምገም በተለይ በመቻቻል፣ በመንግሥትና ሃይማኖት ግንኙነትና በኢትዮጵያ የክርስትና ታሪክ ዙሪያ ጥያቄ አንሥተዋል፤ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ቃል በተነገረበት አኳኋን ወደ ጽሑፍ ተመልሶ ቢቀርብ በተለይ በስፍራው ላልነበሩና በሌሎችም መንገዶች ለመከታተል ዕድል ላላገኙ ወገኖች ይጠቅማል በሚል በጡመራ መድረኩ ተስተናግዷል፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ በጉዳዩ ላይ የሰነዘሩት ትችት፣ ያቀረቡት ጥያቄና የሰጡት ምስክርነት በሁሉም የዓመታዊ ስብሰባው ተሳታፊዎች ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን የመንግሥትን ተቋማት በሚመሩ ዓላውያንና መናፍቃን ጫናዎች መማረሯን ከመግለጽ ባሻገር በደሎችና ተጽዕኖዎች እስካልተወገዱ ድረስ መጪውን የከፋ አደጋ የጠቆመችበት፣ የመንግሥቱንም ተወካዮች በብርቱ የመከረችበት ታሪካዊ አጋጣሚ ስለመኾኑ ከፍተኛ መግባባት ተደርሶበታል፡፡
ይልቁንም የውይይቱ ቁም ነገሮች፣ መንግሥት የፀረ አክራሪነት እንቅስቃሴዎቹን በሚያብራራባቸው ሰነዶቹ እንደሚያትተው፣በፕሮቴስታንት ሃይማኖት ሽፋን የጠባብነት አመለካከት ፖሊቲካ ከሚያራምዱ አካላት ጋራ ትስስር መፍጠሩና ሽፋን መስጠቱ፣‹‹ከማቆጥቆጥና አዝማሚያነት›› አልፎ በገሃድ መገለጹን የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ ‹‹የመልካም አስተዳደርና ሴኩላሪዝም ጥያቄን እንደ መንሥኤ ወስዶ ሕዝብን የጽንፈኝነት አመለካከት በማስያዝ›› ሰላማዊ መስተጋብሩን የማናጋት ሙከራው ለማቃናት አዳጋች ወደሚኾንበት ዳርቻ እየነጎደ መኾኑን ነው፡፡ ስለዚህም ‹‹ለመንግሥት መዋቅር የሚቀርቡ ጥያቄዎች ከአድሏዊ አሠራር በጸዳ መልኩ እንዲሰጡና ፍትሐዊ ጥያቄዎች አለምንም ማጉላላት እንዲፈጸሙ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግ›› በቃል የሰፈረው በተግባር ተተርጉሞ መታየት ይኖርበታል፡፡
* * *
ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ
የሰሜን ወሎና ዋግ ኽምራ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ
ስላስተማሩን እናመሰግናለን፡፡ እንግዲህ ቤተ ክርስቲያኗ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የምትነፍገው ነገር የለም፤ ያላትን ሁሉ ታበረክታለች፤ ታገለግላለች፡፡ አክራሪነት፣ ጽንፈኝነት የሚለውን ቋንቋ እናንተ ናችኹ ያስተዋወቃችኹን፤ እናንተው ናችኹ ያሰማችኹን፤ ከዚያ በፊትም አይታወቅም፤ በደርግም ይኹን በሌላ፡፡ እንደገና ደግሞ ብዙ ጊዜ ጽንፈኝነት፣ አክራሪነት እያላችኹ ዕድሜ ሰጥታችኹ ያበለጸጋችኋቸው እናንተው ናችኹ፡፡
አባቶቻችን፣ የእረኛ ሰነፍ ከቅርብ ሲሉት ከሩቅ ይላሉ፡፡ ወዲያው በአጭሩ መቅጨት ሲገባ ታሪካቸው እየተተረከ፣ እየተተረከ፣ እየተተረከ ብዙ ሕዝብ አተራመሱ፡፡ አዎ፣ ጥያቄዬ÷ ‹‹መረባቸውን በላይ ዘርግተዋል፤ መሬት ግን አልነኩም፤›› አሉ፡፡ እንዴ፣ ነክተው አይደለም ይህ ሁሉ የሚተራመሰው! መረባቸውንማ መሬት ዘርግተው ሕዝብ መካከል ገብተው፣ ሙስሊሙ ሕዝብ እንኳ ‹‹እኛ አናውቃቸውም፤ የእኛ አይደሉም›› እያለ እየጮኸ፣ እየጮኸ መረባቸውንማ መሬት አስነክተው ወጣቱን ትውልድ የመረዙት እነርሱ ናቸው፡፡ እንዴት መሬት አልነኩም፤ መረባቸው ወደ ላይ ነው ይላሉ? እንደ እናንተ መረባቸው መሬት ሲነካ እንዴት ሊያረጉን ይኾን?