- በተጭበረበረ ውል ደብሩን ከ3 ሚልዮን ብር በላይ በማሳጣትና ሰነድ በማሸሽ ይጠየቃሉ
- ከጥቂት የሙዳይ ምጽዋት ገቢ ምርመራ ብቻ ከ2 ሚልዮን ብር በላይ ጉድለት ተገኝቷል
- የአብዛኛዎቹ የደብሩ ሕንጻ ሱቆች የኪራይ ውል በትክክለኛ ሰነድ የተፈጸመ አይደለም
- ለማተሚያ ቤት አገልግሎት በተከራየው ክፍል በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የማይታወቅ ሞዴላሞዴል እንደሚታተምበት ተጠቁሟል
- የፕሮቴስታንት ቤተ ጸሎት እንደሚያዘወትሩ የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተዋል
በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ዋና ጸሐፊ ዲያቆን ምሩፅ ትኵዕ በተጭበረበረ ሰነድ ከተፈጸመ የኪራይ ውል እና ለሒሳብ ምርመራ የሚፈለጉ የሙዳይ ምጽዋት የገንዘብ ቆጠራ ቃለ ጉባኤዎችን ከማሸሽ የሙስና ወንጀል ጋራ በተያያዘ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ፡፡
ዋና ጸሐፊው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት ባለፈው ሳምንት ዐርብ፣ ሐምሌ ፲፪ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ረፋድ ላይ በደብሩ ጽ/ቤት ባሉበት ሲኾን ከዋና ጸሐፊው ጋራ በተጭበረበረው የኪራይ ሰነድና ውል ለደብሩ የሚገባውን ክፍያ ሳይፈጽሙ የግል ጥቅማቸውን አካብተዋል የተባሉ ሌሎች ሁለት የሕንጻው የንግድ ቤቶች ተከራዮችም በተመሳሳይ ቀን መያዛቸው ተመልክቷል፡፡
በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋሉበት ቀን ጀምሮ በቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ የሚገኙት ዋና ጸሐፊው ዲያቆን ምሩፅ እና ሁለቱ ተጠርጣሪዎች፣ ሐምሌ ፲፮ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት መቅረባቸው ተገልጧል፡፡
ዋና ጸሐፊውና የጥቅም ተባባሪዎቻቸው ፈጽመውታል የተባለውን ማጭበርበርና ምዝበራ የሚያረጋግጡ የሰነድ ማስረጃዎችና የሰው ምስክሮች እንዳሉት ለችሎቱ የገለጸው ፖሊስ፣ በዋና ጸሐፊው ላይ ተጨማሪ ማስረጃዎችን ለማሰባሰብና የሰው ምስክሮችን ለማዘጋጀት የ14 ቀን ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ያቀረበችባቸው ክሥ እንደሌለና ከሣሻቸው እንደማይታወቅ በመጥቀስ የፖሊስን የተጨማሪ ጊዜ ጥያቄ በጠበቃቸው በኩል የተቃወሙት ዲያቆን ምሩፅ÷ የሰባት ቤተሰብ አስተዳዳሪ መኾናቸውን፣ የሚጠየቁትን ማስረጃ ቤተሰቦቻቸው እያቀረቡ መኾኑን፣ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሲውሉ ቢሯቸውን ለመዝጋት እንዳልተፈቀደላቸው እና ሐምሌ ፳፪ ቀን በደብሩ የቅዱስ ዑራኤል ክብረ በዓል በመኾኑ ሥራዎች እንዳይስተጓጎሉ በመጥቀስ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ጉዳያቸውን በውጭ መከታተል እንዲችሉ እንዲፈቀድላቸው አመልክተዋል፡፡ ዮሐንስ አይዳኝ እና ዓለም ፍሥሓየተባሉት ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው፣ እነርሱ ውል የያዙበት ሰነድ ከሌሎች ተከራዮች የተለየ እንዳልኾነ በመጥቀስ የዋስ መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡