አቶ በጋሻው ዛሬም የውዝግብ ማዕከል ሆኗል
- ወደ ሉንድ፣ስዊድን የገባበት ሰነድ በራሱ አወዛጋቢ ሆኗል፣
- ሉንድ፣ስዊድን የሚገኘው ቴዎሎጂ ዩንቨርስቲ የግለሰቡን ወደ ስዊድን መምጣት እንደሚያውቅ ተደርጎ የተገለፀውን ደብዳቤ ሐሰት መሆኑ እየተነገረ ነው፣
- ዩንቨርስቲው ስለጉዳዩ እንደማያውቅ ለማወቅ ተችሏል፣
- በአውሮፓ የሚኖሩ በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ አባቶች ስር የሚገኙ አጥብያ አብያተ ክርስቲያናት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የበጋሻውን አወዛጋቢ የሀገር ቤት ታሪክ የሚያውቁ አባቶች እና ምዕመናን በብርቱ እያስጠነቀቁ ነው፣
- ''ከሀገር ቤት አቡነ ማትያስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ እና ቋሚ ሲኖዶስ እንዳስተምራችሁ ፍቃድ ሰጥተውኛል'' በጋሻው ለሉንድ፣ስዊድን ምዕመናን የነገራቸው።
በጋሻው መድረኩን በጉልበት ከነጠቀ በኃላ መድረክ ላይ ቆሞ
ሉንድ፣ስዊድን ደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከሁለት ሳምንታት በፊት የግንቦት 21 የደብረ ምጥማቅ የቅድስት ድንግል ማርያምን በዓል ለማክበር ዝግጅት ይጀምራሉ።በእዚህ መሰረት ከስዊድን እና ኖርዌይ የሚገኙ አባቶች በአቡነ ኤልያስ ተመድበው ለአገልግሎት ይሄዳሉ።ጉባኤው ሲካሄድ ቀደም ብሎ በጋሻው በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ በማገልገል ላይ በሚገኘው ዲ/ን ያሬድ አማካይነት የግብዣ ደብዳቤ ተልኮለት ስዊድን ገብቶ ነበር።ሆኖም ግን ምእመኑን በመፍራት በዕለቱ በቦታው ዝር ሳይል ይቆያል።
በሳምንቱ ግን በቦታው የዶክትሬት ዲግሪውን በመስራት ላይ በሚገኘው እና ያለውን ትርፍ ጊዜ በሙሉ በቤተ ክርስቲያኒቱን በነፃ በቅዳሴ፣በማስተማር እና ምዕመናንን በመምከር የሚያገለግለው ቀሲስ መንግሥቱ በቦታው የዕለቱን ትምህርት ለመስጠት ሲዘጋጅ ከበጋሻው በኩል ትዕቢት በተሞላበት እና የቤተ ክርስቲያንን ስርዓት ፈፅሞ በተፃረረ መልክ ካህኑን እላፊ ንግግሮችን ከመናገሩም በላይ መርሃ ግብሩን የሚመራው እና ቀደም ብሎ በጋሻውን ለማስመጣት ደብዳቤዎችን መላኩ የተነገረለት ዲ/ን ያሬድ የድምፅ መናገርያውን ከካህኑ ነጥቆ ለበጋሻው ሲሰጥ እና ቀሲስ መንግስቱ እና ምዕመናን ቤተ ክርስቲያኑን ጥለው እያለቀሱ ሲወጡ ተስተውሏል።ይህ ጉዳይ የበርካታ ምእመናንን ልብ ያሳዘነ ከመሆኑም በላይ ጉዳዩ በእዚህ ሳይቆም ለቅዳሜ ሰኔ 6/2007 ዓም አሁንም በድጋሚ ምእመናንን የሚጠራ ፖስተር ተዘጋጅቶ እንዲሰራጭ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል።