Tuesday, November 8, 2011

አቡነ ጳውሎስ አባ ሰረቀን የጠ/ቤ/ክ/ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አድርገው ሾሙ

  • ሹመቱን የተቃወሙት ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ከሓላፊነታቸው እንደሚለቁ አሳውቀዋል:: 
  • የሹመቱ ደብዳቤ ፓትርያኩ በሚቆጣጠሩት ጽ/ቤት በኩል የወጣ ነው::
(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 27/2004 ዓ.ም፤ ኖቬምበር 7/2011/ PDF)፦ ባለባቸው ከፍተኛ የአቅም ማነስ እና በተጠረጠሩበት የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅነት ሤራ ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊነት ተወግደው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በሚገኙበት የሊቃውንት ጉባኤ ምርመራ እንዲካሄድባቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተወሰነባቸው አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል ዛሬ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው መሾማቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ በፓትርያሪኩ ማኅተም እና ፓትርያሪኩ በብቸኝነት በሚቆጣጠሩት ልዩ ጽ/ቤት በኩል ደርሷቸዋል፤ ዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሹመቱን በአድራሻ ለ‹አባ› ሰረቀ በደረሳቸው ደብዳቤ ግልባጭ እንዲያውቁት መደረጉ ተዘግቧል፡፡

ሕገ ቤተ ክርስቲያንን፣ የቋሚ ሲኖዶስን እና የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤን ሥልጣን ባስተሐቀረ ሁናቴ ለተጠርጣሪው አባ ሰረቀ የተሰጠውን ሹመት አጥብቀው ሲቃወሙ የቆዩት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በቅዱስ ሲኖዶስ ከተሾሙበት የጠቅላይ ሥራ አስኪያጅነት ሥልጣናቸው እንደሚለቁ ተናግረዋል፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ አራት መሠረት ሦስት ዓመት የአገልግሎት ዘመን ያላቸውና ለተጨማሪ አንድ የምርጫ ዘመን መቆየት የሚችሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ አባ ሰረቀን የመሾም ጉዳይ ከተነሣበት ጊዜ ጀምሮ ተቃውሟቸውን ሲያቀርቡ መቆየታቸው ታውቋል - ልዩነታቸው እንደ ዛሬው በግልጽ ጎልቶ/louder and bolder/  ባይሰማም፡፡

የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ በሚጠናቀቅበት ዋዜማ፣ ጥቅምት 24 ቀን 2004 ዓ.ም፣ አባ ሰረቀን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ለማድረግ ሐሳብ ላነሡት አቡነ ጳውሎስ “አይሆንም” የሚል ተቃውሞ ላሳዩት ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ “እኔ አዝዛለሁ፤ የማዝዘው እኔ ነኝ” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ምንጮች ተናግረዋል፡፡ አቡነ ፊልጶስም፣ “የሚያዝዙት እርስዎ ከሆኑ እኔ ለሾመኝ ሲኖዶስ ሥልጣኔን አስረክባለሁ፤ አባቶች ሳይሄዱ [የምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ሳይጠናቀቅ ማለታቸው ነው] የሚሆን ም/ሥራ አስኪያጅ እንሹም” የሚል ጥያቄ አዘል ምላሽ ያቀርባሉ፡፡ ሌሎችም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትም፣ “የሃይማኖት ችግር እያለባቸው አንሾማቸውም፤ ሃይማኖቱን ነው እንጂ ቅድሚያ የምንመረምረው ሥራ አንሰጠውም፤ ስንኳን ም/ሥራ አስኪያጅ ሊሆን ስድስት ዓመት ሙሉ የሠራው ሥራ የለም፤ ከማበጣበጥ በቀር፡፡ ሥራው ይህን የሚያጠናው ኮሚቴ ሪፖርት ካቀረበ በኋላ የምናየው ነገር ነው” በማለት ከብፁዕ ሥራ አስኪያጁ ጎን ቆመው እንደ ነበር ተገልጧል፡፡
አቡነ ጳውሎስ እና አቡነ ፊሊጶስ (በመካከል ያሉት አቡነ ገሪማ ናቸው)
በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ ሰባት ንኡስ አንቀጽ 15 መሠረት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊን፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅንና ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅን፣ የልማት ኮሚሽን ኮሚሽነርን፣ የውጭ ጉዳይ መምሪያ ሓላፊንና የልዩ ልዩ የሥራ ዘርፎችን ቦርድ አባላት እየመረጠ የመሾም የቅዱስ ሲኖዶስ ሥልጣንና ተግባር እንደሆነ ተደንግጓል:: ፓትርያሪኩ ይህን ሕግ ተላልፈው ለ‹አባ› ሰረቀ የማይገባቸውን ሥልጣን ቢሰጡም ከሕገ ወጡ ተሽዋሚው ደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጋራ የተያያዘውን ሂደት በተመለከተም ያለሥልጣናቸው በሰው ኀይል አስተዳደሩ ላይ ጣልቃ በመግባት መጨረሻ የሌለው ስሕተት መሥራታቸውን ይቀጥላሉ፡፡

ይኸው የአባ ሰረቀ ሕገ ወጥ ሹመት ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ከምልአተ ጉባኤው ስብሰባ አስቀድሞ ጀምሮ፣ በስብሰባው ሂደት እና ፍጻሜ ለሕገ ቤተ ክርስቲያን እና ለቅዱስ ሲኖዶሱ ሥልጣን ባለመገዛት፣ የተለያዩ የማዳከሚያ ስልቶችን በመጠቀም እንደ አባ ሰረቀ ያሉ ጥቅመኛ እና በሃይማኖታዊ ደዌ የተለከፉ ግለሰቦችን በመከላከል የሚያሳዩትን ያልተገባ አቋምና አካሄድ ወደ ከፋ ደረጃ ያደረሱበት አሳሳቢ ሁኔታ ተደርጎ ተወስዷል፤ ከፕሪንስተን ኮሌጅ የፒ.ኤች.ዲ የመመረቂያ ጽሑፋቸው ጋር በተያያዘ ወደ ራሳቸው ወደ ፓትርያሪኩ የሚያነጣጥርና በሃይማኖታዊ ሕጸጽ ከአባ ሰረቀ ጋራ የሚያመሳስላቸው ሌላም የሚፈራ ነገር መኖሩ አልቀረም፡፡

አባ ሰረቀ
አባ ሰረቀ ከሓላፊነታቸው ተወግደው ምርመራ እንዲካሄድባቸው ከተወሰነባቸው ቀን አንሥቶ “በበሉበት ሆዳቸው የወሰኑት ውሳኔ ነው” እያሉ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ስም በየመንገዱ ሲያጠፉ ሰንብተዋል፤ በአንዳንዶቹ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ ቤት ጎራ እያሉም ለሊቃነ ጳጳሳቱ ‹ጉቦ አብልቶ አስወሰነብኝ› በሚል የሚከሱትን ማኅበረ ቅዱሳንን “የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እና የዘርዐ ያዕቆብ ናፋቂ ነው” በሚል ሲወነጅሉ መደመጣቸው ታውቋል፡፡ 
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነገረ መለኮታዊ ይዘቱ ተደፍቆ የወቅቱ ፖሊቲካዊ ቀለም የተሰጠው ይኸው የውንጀላ አነጋገራቸው ዐይነተኞቹ መናፍቃንና መፍቀሬ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ብሎጎች ከሚያቀነቅኑት ጋር በይዘቱ አንድ መሆኑን ልብ ይሏል፤ በሕገ ወጥ መንገድ በሚያገኙት ሥልጣናቸው እንዲቀጥሉ ከተፈቀደላቸውም የመጀመሪያ ዒላማቸው ማኅበረ ቅዱሳንንና ከማኅበሩ ጋር ፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ የሚያካሂዱ አደረጃጀቶችን የማዳከም የቤት ሥራን ማከናወን እንደሚሆን የታዛቢዎች አስተያየት ይጠቁማል፡፡
 
በጉዳዩ ላይ ከመጪው ኅዳር ወር ጀምሮ እስከ ጥር መጨረሻ የሚቆየውና አቡነ አረጋዊ፣ አቡነ ስምዖን፣ አቡነ ዮሴፍ እና አቡነ እንድርያስ በአባልነት የሚገኙበት ቋሚ ሲኖዶስ ምን አቋም እንደሚወስድ ለማወቅ ባይቻልም አሁን የሥራ ጊዜውን በማጠናቀቅ ላይ የሚገኘው ቋሚ ሲኖዶስ፣ ያለጽ/ቤቱ እና ዋና ጸሐፊው ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ዕውቅና ስለተፈጸመው የማናለብኝነት ድርጊት ከአቡነ ጳውሎስ ጋራ ከፍተኛ ንትርክ እንደሚጠብቀው ተገምቷል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስም ሥልጣን ከመልቀቅ ይልቅ፣ የ‹አባ› ሰረቀ ሹመት ሕገ ወጥ መሆኑን በመግለጽ ለመንግሥት ደብዳቤ እንዲጽፉ፣ ግለሰቡ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ለሃያ አራቱም መምሪያዎች እና አህጉረ ስብከት ሰርኩላር ደብዳቤ እንዲያስተላልፉ፣ የሹመቱን ደብዳቤ ውድቅ በማድረግ ‹አባ› ሰረቀን ከሥልጣን እንዲያግዱ፣ በሕገ ወጥ ሹመታቸው አንዳችም ደመወዝ እና ጥቅማጥቅም እንዳያገኙ ማድረግ እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡

የሆነው ሆኖ ፓትርያሪኩ ያለተጠያቂነት በጥፋት ጎዳና/Impunity/ ተጨልጠው በቀጠሉበትና ዛሬ ከቀትር በኋላ ለ‹አባ› ሰረቀ የቤተ ክህነቱን ከፍተኛ የሥራ አስፈጻሚ ሥልጣን በመስጠት ባሳዩት ወደር የለሽ ዕብሪት ከፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ቤተሰቦች/አካላት የማያባራ ተቃውሞ እንደሚጠብቃቸው፣ ዋጋም እንደሚከፍሉበት እየተገለጸ ነው፡፡
የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

1 comment:

  1. እረ እኝህ ሰውዬ ጤና ያላቸው አይመስሉም፣ ኧረ አንድ በሉ

    ReplyDelete