- ሐዋሳው ስብሰባ የተጠበቀው የምዝገባ ዐዋጁ ረቂቅ ለውይይት ሳይቀርብ ቀረ
- የዐዋጁ ጉዳይ በቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ደረጃ ሊመከርበትና አቋም ሊያዝበት ይገባል
- የሰላም ዕሴት ግንባታ ሰነዱ በአወዛጋቢ ይዘቱ ለተጨማሪ ግምገማ እንዲዘገይ ተደረገ
የሃይማኖት ወይም እምነት ተቋማትን ለመመዝገብና የዕድሳት አገልግሎት ለመስጠት በሚል መዘጋጀቱ የተገለጸውን የዐዋጅ ረቂቅና አሠራሩን በመቃወም የሚካሔድ እንቅስቃሴ የአክራሪነትና ጽንፈኝነት ዝንባሌ መገለጫ መኾኑን የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም ተናገሩ፡፡
ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት፣ በሐዋሳ ለሁለት ቀናት በተካሔደውና የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ‹‹ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ›› ጋራ በመተባበር ባዘጋጀው ዐውደ ትምህርት ላይ ‹‹አክራሪነትና ጽንፈኝነት ከሕገ መንግሥታችን ጋራ ያለው የማይታረቅ መሠረታዊ ቅራኔና መፍትሔው›› በሚል ርእስ ባቀረቡት ጽሑፍ ነው፡፡
ይኸው የሚኒስትሩ ጽሑፍ ‹‹አክራሪነትና ጽንፈኝነት ማብራሪያና መፍትሔዎቻቸው››ተብሎ በስላይድ ታግዞ የቀረበ ሲኾን መንግሥትና የሃይማኖት ተቋማት በሰላምና ልማት ጉዳይ ጭምር መደራረስ የለባቸውም በሚል የሚካሔድ እንቅስቃሴ ስለመኖሩ ይገልጻል፡፡
ይኸው እንቅስቃሴም የአክራሪነትና ጽንፈኝነት ዝንባሌ እንደኾነ የሚኒስትሩ ጽሑፍ ያመለክታል፡፡ ‹‹የአክራሪነትና ጽንፈኝነት ዝንባሌዎች የጋራ ጉዳዮች›› በሚል የጽሑፉ ንኡስ ርእስ ሥር የተካተተው ይኸው የሚኒስትሩ ምልከታ፣ በስም ለይቶ ያነሣው አካል ባይኖርም ‹‹የሃይማኖት ተቋማት ምዝገባ ጉዳይ እና የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ›› የሚሉ ሁለት ጉዳዮችን በማውሳት ‹‹ለአክራሪነትና ጽንፈኝነት ዝንባሌው›› በማሳያነት ማቅረቡ ተዘግቧል፡፡
ይኹን እንጂ ቤተ ክርስቲያናችንን ጨምሮ ሰባት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አብያተ እምነቶች በተሳተፉበትና ጥር ፴ እና የካቲት ፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በሐዋሳ – ሌዊ ሪዞርት በዝግ በተካሔደው የምክክር መድረክ፣ ለውይይት እንደሚቀርብ ተጠብቆ የነበረው የሃይማኖት ወይም እምነት ተቋማት ምዝገባና የፈቃድ ዕድሳት አገልግሎት ዐዋጅ ረቂቅ አለመቅረቡን የስብሰባው ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
የዐዋጅ ረቂቁ ቀድሞ ለመንበረ ፓትርያርኩ ደርሶ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሊመከርበትና አቋም ሊያዝበት እንደሚገባ የቋሚ ሲኖዶሱን አባላት ጨምሮ ኻያ ያህል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ጥር ፳፯ እና ፳፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በተደረጉ አስቸኳይ ስብሰባዎች ጠንካራ ውሳኔዎች ተላልፈው እንደነበር ተገልጦአል፡፡
በጥያቄው መሠረት የተፈለገውን የዐዋጁን ረቂቅ ከሐዋሳው ስብሰባ በፊት ለማግኘት ለሚኒስቴሩ የቀረበው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ባያገኝም፣ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የተመራውና 19 ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የተገኙበት የቤተ ክርስቲያናችን ልኡካን ቡድን በሐዋሳው የምክክር መድረክ የተገኘው ይህንኑ ቀድሞ የተመከረበትን የቋሚ ሲኖዶሱን አቋም ይዞ እንደነበር ተዘግቧል፡፡
ቋሚ ሲኖዶሱና በርካታ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከሐዋሳው የምክክር መድረክ አስቀድሞ ባካሔዱት አስቸኳይ ስብሰባ፣ በዐዋጁ ረቂቅ ላይ ይዘው የገቡትን ጠንካራ አቋም ሳይረዱ አልቀሩም የተባሉት ሚኒስትሩ ዶ/ር ሺፈራው በከፍተኛ ጥንቃቄ መርተውታል በተባለው የሁለቱ ቀናት ስብሰባ፣‹‹ሌላ ነገር ጠብቃችኹ የመጣችኹ አላችኹ፤ ትኩረታችን በልዩነታችን አብሮ በሚያኖረን ጉዳይ ላይ እንዴት እንነጋገር ነው፤››ሲሉ መደመጣቸው ተሰምቷል፡፡
በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዐት የሕጎች ተዋረድ፣ ዝቅተኛ የሕግ ማህቀፍ ዕርከን ከኾነው – መመሪያ ወደ ከፍተኛው የሕግ ማህቀፍ ዕርከን – ዐዋጅከፍ ተደርጎ ዳግም መዘጋጀቱ የተነገረው ‹‹የሃይማኖት ወይም እምነት ተቋማት ምዝገባና የዕድሳት አገልግሎት›› ሕግ ረቂቅ፣ በአንድ ሚኒስቴር መሥ/ቤት ሓላፊነት ክልል ተወስኖ በመመሪያ መልክ በወጣበት ወቅት በርካታ ትችቶችን ማስተናገዱ ይታወሳል፡፡
ከትችቶቹም መካከል፡- በኢትዮጵያ ነባራዊ ኹኔታ የሃይማኖት ተቋማት በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ወሳኝ አገራዊ ሚና በመመሪያ ብቻ ማስተናገድ አግባብ አይደለም፤ ጉዳዩ በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በፍትሐ ብሔር ሕጉና ሕጉን መሠረት አድርጎ የወጣውን የሃይማኖት ተቋማት ምዝገባ ደንብ ይፃረራል፤ የሕግ ማርቀቅ መርሕንም ይጥሳል፡፡
በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ ተመሥርታና ኢትዮጵያን አቅንታ ለሁለት ሺሕ ዓመታት ከኖረችው ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊነትና ሉዓላዊነት ጋራአይሔድም፤ ነባርና ጥብቅ ሕግ ያላቸውን የምሥራቅ አገሮችን ልምድ ያካተተ አይመስልም፤ በተቃራኒው ነባሮቹን የእምነት ተቋማት ከአዲሶቹ የማይለይና ፕሮቴስታንታዊነት የተጫነው ምዕራባዊ ለመኾኑ መንፈሱና የቃላት አጠቃቀሙ ያረጋግጣል፡፡
በመኾኑም የቤተ ክርስቲያን አባቶችና ምእመናን በይበልጥም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በጥንቃቄ ሊመክሩበት፣ ሐሳባቸውን በግልጥ ሊሰጡበትና የቤተ ክርስቲያንን ሉዓላዊነት በሚያስከብር መልኩ እንዲሔድ ሊያደርጉት ይገባል የሚሉ ይገኙበታል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ምዝገባ ዐዋጅ ረቂቅ በመመሪያ ረቂቅነቱ ሳለ የተሰነዘረው ትችት ቁምነገሩ ይኸው ነው፡፡ ዝርዝሩ ይቆየንና ከመመሪያነት ይልቅ እንደቀደሙት ማህቀፎች የሃይማኖትን ጉዳይ በዐዋጅ ለማስተናገድ መወጠኑ አዎንታዊ ነው፤ ዐዋጅ መኾኑ፣ ሕጉ በብዙኃኑ እንዲታወቅም የተሻለ ዕድል ይፈጥራል፤ ለአድልዎና ብልሹ አሠራር ያለውን ተጋላጭነትም ይቀንሳል፡፡
ሚኒስትሩ ትችቱ፣ ‹‹መንግሥትና የሃይማኖት ተቋማት በሰላምና ልማት ጉዳይ ጭምር መደራረስ የለባቸውም›› የሚል መንቀሳቀስና ‹‹የአክራሪነትና ጽንፈኝነት ዝንባሌ›› እንደኾነ አድርገው በምሳሌነት መንቀሳቸው ግራ አጋቢ ነው፤ በርግጥም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ በኹለቱ ቀን ምክክር ላይ እንደተናገሩት÷ ‹‹በሰላም አብሮ መኖር ግዴታችን ቢኾንም የአክራሪነት፣ ጽንፈኝነትና ሽብርተኝነት ትርጉም አልገባንም፤ ለማስተማርም ተቸግረናል፤›› እንዳሉት ያሰኛል፡፡
በሚኒስትሩ የተጠቀሰው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጽ/ቤትን አስመልክቶ የሚሰነዘረው ትችት፣ ከአድሏዊነት የጸዳ ተቋማዊ ሚናውንና ነጻነቱን (በተለይም ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋራ ባለው ግንኙነት እና የአባል አብያተ እምነቶቹን የተሳትፎ ሚዛናዊነት)አስጠብቆ እንዲወጣ የሚጠይቅ እንጂ የአክራሪነትና ጽንፈኝነት ዝንባሌ ማሳያ ሊኾንና ሊባል አይችልም፡፡
በጥቅምት ወር ፳፻፫ ዓ.ም. ስድስት አብያተ እምነትን በመያዝ የተመሠረተው የጉባኤው ዋነኛ ተልእኮ÷ በሃይማኖቶች መካከል ግጭትን መከላከልና በሰላም አብሮ የመኖርን ዕሴት በማጎልበት ለተከታዩ ትውልድ ማስተላለፍ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊነትን ማእከል ወርቃማውን ሕግ (እንግዲኽ ሰዎች ሊያደርጉላችኹ የምትወዱትን ኹሉ እናንተ ደግሞ እንዲኹ አድርጉላቸው) መርሕ በማድረግ እንደ ዋና ተልእኮ የተያዘው አብሮ የመኖር ዕሴትን የማጎልበት የጋራ አጀንዳ ታሪክ በታሪክነቱ ተጠብቆ በመከባበርና በመገናዘብ እስከተፈጸመ ድረስ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በሐዋሳው የምክክር መድረክ ላይ እንዳሉት፣ ‹‹ለሕዝባችንና ለአገራችን ጤናማ ሕይወት የሚሰጥ ነው፡፡››
ይኹንና ግጭትና የሰላም መታጣት ከእምነት ልዩነት ብቻ እንደማይነሣ እስከታመነበት ድረስ የጋራ ጉባኤው÷ በሕግና ደንብ ሽፋን በዜጎች ላይ የሚፈጽምን መዋቅራዊ ኢ-ፍትሐዊነትን (structural injustice)፣ ሙስናን፣ ብልሹ አስተዳደርንና ምግባረ ብልሹነትን ‹‹በሞራላዊና አባታዊ ሥልጣኑና ሓላፊነቱ ልክ›› በተባበረ አቋም ያለማመቻመች ሲገሥጽ፣ ለተጎዱትና ለተገፉት የፍትሕ ጠበቃ ሲኾንና ድምፁን ሲያሰማ አለመታየቱ በብርቱ የሚተችበት ጉዳይ ነው፡፡
በሌላ በኩል፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ÷ የየአብያተ እምነቶቹን መሪዎች በበላይ ጠባቂነት የያዘ ሲኾን ቤተ ክርስቲያናችን በሥራ አስፈጻሚው መዋቅር የሰብሳቢነት ሚና አላት፡፡ ይኹንና ቤተ ክህነታችን ለጉባኤው ጽ/ቤት የቤተ ክርስቲያናችንን ልኡካን የሚወክልበት መንገድና ልኡኮቻችን በየደረጃው ባሉ የጽ/ቤቱ መዋቅሮች ያላቸው የተሳትፎ ብቃት ሌላው የትችት መነሻ ነው፡፡
ይኸውም የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች አስተዳደርን ጨምሮ በዘጠኙም ብሔራዊ ክልሎች ተቋቁሞ በሚንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጽ/ቤቶች የሚላኩት ልኡኮቻችን ውክልና ጥቅማጥቅምን መነሻ ያደረገ፣ በእርስ በርስ ትውውቅና በፖሊቲካ አቋም አልፎ አልፎም በተወላጅነት ተዋፅኦ ላይ የታጠረ እንደኾነ ይነገራል፡፡
ይህም ኹለገብ ዕውቀትና ንቃት በሚጠይቁት የጽ/ቤቱ መርሐ ግብሮች (የምክክር መድረኰች፣ ዐውደ ጥናቶችና የኅትመት ውጤቶች) ያለን ተሳትፎ ጥቅመኝነት፣ አድርባይነትና የፖሊቲካ ቅኝት የሚጫነው እንዲኾን አድርጎታል በሚል ተተችቷል፤ ከቤተ ክርስቲያናችን ምሉዕነት አንጻር አጥጋቢ እንዳይኾንና በአገራዊ ጉዳዮች ድርሻችንን በበቂ እንዳንወጣ ውስንነት እንደፈጠረብን ተመልክቷል፤ በትምህርት ዝግጅት ይኹን በሞያ ብቃት ሌሎች አብያተ እምነቶች ከሚወክሏቸው ልኡካን ጋራ ለመድረኩ አጀንዳ የሚመጥኑ ልኡኮቻችንን ቁጥር እንዳሳነሰውም ተጠቁሟል፡፡
በዚኽ ረገድ እንደ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል (የቦርድ ሰብሳቢ) እና ሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገብረ ዐማኑኤል (የቦርድ አባል) ያሉት ተወካዮቻችን በጋራ ጉባኤው የተለያዩ መርሐ ግብሮች ላይ የሚያደርጓቸው ተሳትፎዎች ከሞላ ጎደል በምስጉንነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እንደዚኹም ኹሉ ለላካቸው አካል ተሳትፏቸውን የተመለከተ ኢንፎርሜሽንና አንዳችም ሪፖርት ሳያቀርቡ ዓመታትን ያስቆጠሩ የጋራ ጉባኤው የፌዴራል ይኹን የክልል ጽ/ቤቶች ተወካዮቻችን ኹኔታ መጤን ይገባዋል፤ ብቃት ባላቸው ልኡካንም መተካት ይኖርባቸዋል፡፡
ምንጭ: ሐራ ዘተዋሕዶየተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment