- በዕርቀ ሰላም ሒደቱና መግለጫው ስለ በጋሻው ደሳለኝ የተጠቀሰ ነገር የለም
- የምእመናን ተወካዮች በጋሻው ይቅርታ እንዲጠይቅ የተሰጠውን ፈቃድ ተቃውመዋል
- በጋሻው ደሳለኝ ይቅርታ የመጠየቁን ፈቃድ እንዲያገኝ በፓትርያርኩና በቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤቱ ላይ የክልል እና ፌዴራል ግለሰብ ባለሥልጣናት ጫና መደረጉ ተጠቁሟል
በሊቃውንት ጉባኤው ለጥያቄ ተፈልጎ ያልተገኘውና በአቋራጭ ይቅርታ እንዲጠይቅ ‹የተፈቀደለት› በጋሻው ደሳለኝ
የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የሲዳማና ጉጂ ቦረና አህጉረ ስብከት ልኡክ ዛሬ፣ ኅዳር ፳፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. የዕርቀ ሰላም ስምምነት መግለጫ በሚያወጣበት በሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅ/ገብርኤል ገዳም በጋሻው ደሳለኝ ‹‹ሕዝቡን ይቅርታ ለመጠየቅ›› ፈቃድ ማግኘቱ ተሰማ፡፡
በጋሻው ደሳለኝ ይቅርታ የመጠየቅ ፈቃድ ማግኘቱ የታወቀው÷ የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የዕርቀ ሰላም ልኡኩ ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ትላንት፣ ከቀትር በኋላ ወደ ሐዋሳ ደ/ምሕ/ቅ/ገብርኤል ገዳም ምእመናን ተወካዮች ስልክ በመደወል፣ በመግለጫው ላይ በጋሻው ምእመኑን ይቅርታ መጠየቅ እንዳለበትና እንደተፈቀደለት፣ የምእመናን ተወካዮቹ በዚህ እንዲስማሙና የማይስማሙ ከኾነ እርሳቸውም እንደማይገኙ ባስታወቁ ጊዜ ነው፡፡
ዋነኛው የዕርቀ ሰላም ንግግር በተደረገበት ኅዳር ፭ እና ፮ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም በተያዘው ቃለ ጉባኤና በተዘጋጀው መግለጫ ላይ የበጋሻው ስም እንኳ እንዳልተነሣ የሚጠቅሱት የምእመናን ተወካዮች፣ የዕርቀ ሰላም ስምምነቱ የሐዋሳ ችግር ብቻ የተዘረዘረበትና የከተማውን ምእመናን ብቻ የሚመለከት እንደኾነ ለብፁዕ ዋና ጸሐፊው ለማስረዳት ቢሞክሩም ብፁዕነታቸው በአቋማቸው በመጽናታቸው ተቀባይነት እንዳላገኙ ተገልጦአል፡፡
የምእመናን ተወካዮቹ ተቃውሞ፣ ግለሰቡ በዕርቀ ሰላም ስምምነት ውስጥ አለመጠቀሱ ብቻ ሳይኾን የሐዋሳ ከተማ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ነዋሪ ምእመን አለመኾኑና ኦርቶዶክሳዊ ትምህርተ ሃይማኖትንና ክርስቲያናዊ ትውፊትን በመፃረር በተናገራቸውና በጻፋቸው ሕጸጾች የበደለው የሐዋሳን ብቻ ሳይኾን ቤተ ክርስቲያንንና በርካታ ኦርቶዶክሳውያን መኾኑን፣ ስለዚህም ከፍተኛ በደሉ በታኅሣሥ ወር ፳፻፬ ዓ.ም. በተቋቋመው የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ሊቃውንት ጉባኤ አባላት ጥምር ጉባኤ ጉዳዩ የተያዘ መኾኑን የሚጠቅስ ጭምር ነው፡፡